Friday, February 22, 2019

ተዋሕዶ ኅትመት


 መ/ር ሽመልስ መርጊያ 

ቀን 14/06/2011 ዓ.ም

አምላክ በሕይወት ካቆየኝ አንድ በጎ እና ለቤተ ክርስቲያን ቅናቱ ያለው ሰው ይህን ሐሳብ ከግብ ሊያደርሰው ይችላል ብዬ በማመን  ይህን ሕልሜን ለአንባቢያን ላከፍለው ወደድሁ 
 ስያሜ፡- ተዋሕዶ ኅትመት
የስያሜው ምክንያት፡- ተዋሕዶ ማለት በሁለት አካላት መካከል የተደረገ ፍጹም የሆነ አንድነትን የሚገልጽ ቃል ሲሆን አንዱ አካል እና የአካሉ ባሕርይ የሌላኛውን አካልና ባሕርይ ሳያጠፋ፣ ሳይመጥ፣ ሳይቀይር፣ ሳይቀይጥ፣ ሳይለውጥ ነገር ግን አንዱ አካል ሌላኛውን አካል የራሱ አካልና ባሕርይ በማድረግ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን የሚገለጡበትን ምሥጢር ለማስረዳት ቤተ ክርስቲያናችን በብቸኝነት የምትጠቀምበት ቃል ነው፡፡ ይህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ሰው ሆኖ በመወለድ የገለጠው ምሥጢር ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ከአብ ጋር በመተካከል ሲኖር ሳለ ሰውን ለማዳን ሲል ከቅድስት ድንግል ማርያም በጽንሰት ሥርዓት ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ በመንሳት ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ በአንድ አካልና በአንድ ባሕርይ ለፍጥረት ሁሉ ተገልጦአል፡፡ ይህን የእግዚአብሔር ቃል ሰው የመሆን ምሥጢር ቤተ ክርስቲያናችን ተዋሕዶ ትለዋለች፡፡ ይህንንም ቃል የራሷ መገለጫ ስም አድርጋም ትጠቀምበታለች፡፡ ይህንንም መጠሪያ ስሟ አድርጋ በመጠቀሟም ከሌሎች የክርስትና የእምነት ተቋማት ሁሉ ትለያለች፡፡  ስለዚህ ተዋሕዶ ስንል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማለት እንደሆነ ማንም በቀላሉ ይገነዘበዋል፡፡ ለዚህም ነው ወደፊት እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንዲመሠረት ለምፈልገው የሕትመት ተቋም ተዋሕዶ ኅትመት የሚል ስያሜ መስጠቴ፡፡