Friday, February 22, 2019

ተዋሕዶ ኅትመት


 መ/ር ሽመልስ መርጊያ 

ቀን 14/06/2011 ዓ.ም

አምላክ በሕይወት ካቆየኝ አንድ በጎ እና ለቤተ ክርስቲያን ቅናቱ ያለው ሰው ይህን ሐሳብ ከግብ ሊያደርሰው ይችላል ብዬ በማመን  ይህን ሕልሜን ለአንባቢያን ላከፍለው ወደድሁ 
 ስያሜ፡- ተዋሕዶ ኅትመት
የስያሜው ምክንያት፡- ተዋሕዶ ማለት በሁለት አካላት መካከል የተደረገ ፍጹም የሆነ አንድነትን የሚገልጽ ቃል ሲሆን አንዱ አካል እና የአካሉ ባሕርይ የሌላኛውን አካልና ባሕርይ ሳያጠፋ፣ ሳይመጥ፣ ሳይቀይር፣ ሳይቀይጥ፣ ሳይለውጥ ነገር ግን አንዱ አካል ሌላኛውን አካል የራሱ አካልና ባሕርይ በማድረግ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን የሚገለጡበትን ምሥጢር ለማስረዳት ቤተ ክርስቲያናችን በብቸኝነት የምትጠቀምበት ቃል ነው፡፡ ይህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ሰው ሆኖ በመወለድ የገለጠው ምሥጢር ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ቃል ከአብ ጋር በመተካከል ሲኖር ሳለ ሰውን ለማዳን ሲል ከቅድስት ድንግል ማርያም በጽንሰት ሥርዓት ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስ በመንሳት ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሆኖ በአንድ አካልና በአንድ ባሕርይ ለፍጥረት ሁሉ ተገልጦአል፡፡ ይህን የእግዚአብሔር ቃል ሰው የመሆን ምሥጢር ቤተ ክርስቲያናችን ተዋሕዶ ትለዋለች፡፡ ይህንንም ቃል የራሷ መገለጫ ስም አድርጋም ትጠቀምበታለች፡፡ ይህንንም መጠሪያ ስሟ አድርጋ በመጠቀሟም ከሌሎች የክርስትና የእምነት ተቋማት ሁሉ ትለያለች፡፡  ስለዚህ ተዋሕዶ ስንል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማለት እንደሆነ ማንም በቀላሉ ይገነዘበዋል፡፡ ለዚህም ነው ወደፊት እግዚአብሔር ቢፈቅድ እንዲመሠረት ለምፈልገው የሕትመት ተቋም ተዋሕዶ ኅትመት የሚል ስያሜ መስጠቴ፡፡   

ጭብጡ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዶግማ፣ ለሞራል ለሥርዓትና ለአገልግሎት አስተምህሮዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ እርሷ የምትቀበላቸውን የቅዱሳን አባቶች ድርሳናትንም መሠረት ታደርጋለች፡፡ ይህንን ለመረዳት ቤተ ክርስቲያን እስካሁን ዘመን ድረስ የምትገለገልባቸውን የትርጓሜ፣ የሥርዓትና የአገልግሎት መጻሕፍትን መመልከት በቂ ነው፡፡ በእነዚህ ትርጓሜና የሃይማኖት መጻሕፍት ላይ እንደምናስተውለው ቅዱስ እገሌ በዚህ ድርሳኑ እንዲህ ብሎ እንደጻፈልን የሚሉ አገላለጾችን ማግኘት የተለመደ ነው፡፡  በሥርዓትና በአገልግሎት መጻሕፍትም ላይ ለምሳሌ በፍትሐ ነገሥት፣ በቅዳሴ፣ በቁርባን፣ በጥምቀት፣ በቀንዲል፣ በተክሊል፣ በፍትሐት፣ በክህነት ስልጣን አሰጣጥ ሥርዓት ላይ የቅዱሳን አባቶች ድርሳናት ያልተጠቀሱበት ሥፍራ ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ እንደ ማስረጃ እንዲሆኑን የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ከሆኑት አንድምታ ወንጌል፣ ሃይማኖተ አበው፣ ግብረ ሕማማት የሚባሉ መጻሐፍትን መመልከት በቂ ነው፡፡ በእነዚህና በሌሎችም የቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት ላይ በዋቢነት የተጠቀሱትን ድርሳናትን አብዛኛዎቹን ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ ጠፍተዋል ወይም ድርሳናቱ ሰፊ ከመሆናቸው የተነሣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ከመጻፍ ፍሬ ፍሬ ሐሳቦቻቸውንና ዘመኑን የሚዋጁትን አስተምህሮዎች ብቻ አውጣጥተው  ወደ ግእዝ መልሰው ለእኛ ማቆየታቸውን ነው፡፡ ይህም ዋቢ ያደረጓቸው የቅዱሳን አባቶች ድርሳናት በእነርሱ ዘንድ በደንብ የታወቁ እንደነበሩ መገንዘብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ አብዛኛዎቹ የቅዱሳን አባቶች ድርሳናት  ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ በተሟላ መልኩ በሚባል ደረጃ ተመልሰው ተጽፈው እናገኛቸዋለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በግእዝ የተጻፉና ቀሪው ዓለም የማያውቃቸው ለቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ቁልፍ ሚና ያላቸው ድርሳናትም በስፋት በተለይ በገዳማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን መሠረት በማድረግ ከሌሎች የሥነ መለኮት ምሩቃን እና መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ጋር ልንሠራቸው የምችላቸው ሥራዎች፡-
1.      በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተጽፈው የሚገኙትን የቅዱሳን አባቶችን ድርሳናት የቤተ ክርስቲያንን የትርጓሜ ስልት በጠበቀ መልኩ ወደ አማርኛ ሲቀጥል ወደ ግእዝ በመመለስ ቤተ ክርስቲያን እንድትገለገልባቸው ማድረግ፡፡
2.     የቤተ ክርስቲያንኒቱን የዶግማ፣የቀኖና እና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሥራዎችን ከግእዝ ወደ አማርኛ እንዲሁም ወደ እንግሊዘኛ በመተርጎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በሥራቸው ከሚታወቁ ቅዱሳን አባቶች ሥራዎች ጋር በማዛመድ ቀሪው ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንንና የሊቃውንቶቿን አስተምህሮ እንዲረዳው ማድረግ ነው፡፡  
ጥቅሙ
-       በቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶች የተጻፉ ዋቢ መጻሕፍትን በራሳችን ቋንቋና የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና እንዲሁም ትውፊት  በጠበቀ መልኩ በብዛትና በጥራት እንዲገኙ ያስችላል፡፡
-       የጠፉትንና ያልተሟሉ የቅዱሳን አባቶች ድርሳናትን እንደ አዲስ እንዲተኩና የጎደሉትም እንዲሟሉ ይረዳል፡፡   
-       በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ የሥነ መለኮት የትምህርት ዘርፎች ላይ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት አስተምህሮ ለማስተዋወቅ ይረዳናል፡፡
ይህን ሥራ ለመሥራት ለዚህ ተብሎ አንድ የሕትመት ተቋም ቢመሠረት ሥራውን ይበልጥ ውጤታማና ዘለቂ ያደርገዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ቭላድሜር ሎስኪ የሚባል የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሕትመት ተቋም(St. Vladmirs Seminary Press) የምሥራቃውያኑን (Eastern Orthodox Churchs)የዶግማና ቀኖና እንዲሁም እነርሱ የሚቀበሏቸውን አባቶች ሥራዎች እያሳተመ በዓለም ዙሪያ እያዳረሰ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማግኘት በተጨማሪ የእምነት ተከታዮቻቸውንም ለማብዛት፣ ለማጽናት ረድቶአቸዋል፡፡ እኛም ይህን ተቋም አብነት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮንና የሊቃውንቶቿን ድርሳናት ለቀሪው ዓለም ለማስተዋወቅ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉ የእምነቷ ተከታዮች የቅዱሳን አባቶችን ድርሳናት በገዛ ቋንቋቸው በቀላሉ እንዲያገኟቸው በማድረግ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን ስለ እምነቱ የጠለቀ ግንዛቤ ኖሮት በሃይማኖቱ እንዲጸና እምነቷም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድትሰፋ ይረዳናል፡፡

No comments:

Post a Comment