Monday, February 25, 2019

ጸሎት በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትርጓሜ

በመ/ር ሽመልስ መርጊያ
18/06/2011 ዓ.ም  
ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እኔስ ቅዱሳን ብላቸው እመርጣለሁ በአንድነት የተስማሙባት አንዲት ደግ ትርጉም አለች እርሷንም በሕሊናዬ ሳደንቃት ሳወጣ ሳወርድ አረፈድኩ፡፡ እርሷም ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ናት የምትለዋ ትርጓሜ ናት፡፡ እሊህ ሊቃውንት በአንድ ድምፅ ጸሎት ማለት ልመና፣ ምልጃ ወይም ምስጋና ማለት ነው ብለው አልተረጎሙልንም ነገር ግን ጻድቁ አብርሃም አምላኩን ሥላሴን በእንግድነት ተቀብሎ ያነጋገረውን ንግግር ዓይነት፣ ሎጥ ወንድሙንና ቤተሰቡን እንዲያድንለት ከአምላኩ ጋር የተነጋገረውን መነጋገር ዓይነት፣ ያዕቆብ በጵንኤል ከአምላኩ ጋር ታግሎ ካልባረከኝ አልለቅህም ያለውን ዓይነት መነጋገር፣ ሙሴ በደብረ ሲና ተራራ ላይ ዐራባ ቀንና ሌሊት ከፈጣሪው ጋር የተነጋገረበትን ዓይነት እና ክብርህን አሳየኝና እርሱ ይበቃኛል ብሎ የተነጋገረውን መነጋገር ዓይነት፣ ኤልያስ እና ኤልሳዕ ከአምላካቸው ጋር የተነጋገሩበትን መነጋገር ዓይነት፣ ነቢያት ሁሉ ከአምላክ ጋር የተነጋገሩትን መነጋገር ዓይነት ናት አሉን ወዳጆቼ፡፡


በዚህ ከአምላክ ጋር በግልጽ እየተያዩ ልመናን ጸሎትን ምልጃን ምስጋናን ማቅረብ የእርሱንም መልስ መስማት ማድነቅ በክብሩ ተማርኮ መቅረት በቃ ይህ ነው የጸሎት ትርጉም አሉን፡፡ ለእሊህ ቅዱሳን ሊቃውንት የጸሎት መጻሕፍት እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ለማየት ላልበቃነው ለእኛ እንዴት መጸለይ እንዲገባን የሚያስተምሩንና በእነርሱ ድልድይነት አምላክን ወደማነጋገር ከፍታ የምንደርስባቸው ናቸው፡፡ አደነቅሁ አደነቅሁ ወዳጆቼ እሊህ ቅዱሳን ሲበሉም ሲጠጡም ሲሄዱም ሲቀመጡም ሲተኙም አምላክን ሲያነጋግሩ የሚውሉ ናቸው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ እሊህ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ሊቃውንት ለሰው የሚሰጡት ጊዜ ሳይቆጫቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ እረ እንደውም ለቅዱሳን መላእክት እንኳ የሚሰጡት ጊዜ የሚቆጫቸው ይመስለኛል፡፡

ለነገሩ መላእክት አኗኗራቸው እንደ እነርሱ አይደለምን እነርሱስ ቢሆኑ ከአምላክ ጋር ከመነጋገር በላይ ምን ደስ የሚያሰኛቸው ነገር አለ? እስቲ አስተውሉት ወዳጆቼ እሊህ ሊቃውንት እንደ ወንጌላዊው ዮሐንስ ዙፋን በሰማይ ቆሞ በዙፋኑ ላይ ተቀማጭ ኖሮ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ጌታ መልኩ የኢያስጲድና የሰርዲኖን ዕንቍ የመሰለ በመልኩ መረግድ የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ሆኖለት ሃያ ዐራት ካህናተ ሰማይ በዙሪያው ከበውት እያዩት በትሕትና ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ አስተውሉት፡፡ ወይም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ጌታቸው ከጎናቸው ሆኖ አይዞህ ጽና እኔ ከአንተ ጋር ነኝ ብሎ እንዳነጋገረው ዓይነት እነርሱንም ሲያነጋግራቸው አስተውሉት፡፡

ከአምላክ እናት ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋርማ እንደ ልጅ ሲነጋገሩ ማየት ምን ይደንቃል፡፡ ያመሰግኗታል እንዲህ ይሏታል ድንግል ቅድስት ብፅዕት ክብርት ልዕልት ሆይ ፍቅርሽ በልቡናዬ እንዳይጠፋ ተቀጣጥሎ ያለ እሳትን ይመስላል ከፍቅርሽ ጽናት የተነሣ እንቅልፍ እንኳ የለኝም፡፡ ቆሜ ሳመሰግሽ ውዬ ሳመሰግንሽ መሽቶ ይነጋል፡፡ እመቤቴ ሆይ የፍቅርሽ እሳት ቁርበቴን አበራው ነፍሴን በደስታ አፍነከነካት የእህል ርሃቡ የውሃ ጥማቱ ከዚህ ፍቅር እንዳያቋርጡኝ ሰጋሁኝ…. ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ትርጓሜ ጸሎት እንግዲህ እንዲህ ናት ተወዳጆች፡፡

2 comments:

  1. እድሜ ጠና ይስጥህ። ቡሩክ ሁን።

    ReplyDelete
  2. Casinos Near Me - Riverview Casino Resort - MapYRO
    Looking for Casinos Near Me 충청남도 출장마사지 in 김천 출장샵 Riverview? Find Casinos Near Me and 안양 출장안마 other Casino 광주 출장마사지 Destinations in MI. 고양 출장샵 See nearby casinos, restaurants,

    ReplyDelete