Thursday, December 5, 2019

ተዋሕዶ ይቺ ናት


ተዛማጅ ምስልየጌታችን ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ) ለቃል ድምፁ የሆነው ዮሐንስ መጥምቅ፡- “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡበማለት የቅድስት ድንግል እናታችን ምሳሌ በሆነች በንስሐ ማኅፀን ተወልደንመንግሥተ ሰማያትወደ ተባለች የጌታ አካሉ እንገባ ዘንድ ሰበከን፡፡ ለጌታ ድምፁ የሆንኽ ቅዱስ ዮሐንስ ሆይ! ለአንተ በጊዜው ያልተፈጸመልህን ለእኛ የሰበክውን ይህን ድንቅ ዜና ይዘህ ስለመጣኽልን ፍጹም ደስ አለን፡፡ ይልቁኑ የኃጢአት ሥርየትን የመስጠት ስልጣን ያለው እርሱ ጌታችንመንግሥተ ሰማያት ወደሆነች ሰውነቴ በጥምቀቴ ባርኬ በሰጠኋችሁ ጥምቀት ከጎኔ በፈሰሰው ውኃ ነጽታችሁ ከጎኔም የፈሰሰውን ደሜን ተቀብላችሁ በጦር በተዋጋው ጎኔ ሽንቁር ዓለማችሁ ወደ ሆነው ወደዚህ መለኮታዊ አካሌ ግቡ እያለ ሰበከን፡፡ 

 እኛም በዐርባና በሰማንያ ቀናችን ወደዚህ አካሉ በማየ ገቦው ተጠምቀን ሥጋውንና ደሙን በልተን ጠጥተን ገባን፡፡ ይህች ናት መንግሥተ ሰማያት፡፡ አሁን እኔና መሰል የተዋሕዶ ልጆች የራሳችን አይደለንም፡፡ የራሳችንም ሆነን ፍጥረታውያንን መስለን መኖርን አንሻም፡፡ ፍጥረታውያንም አይደለንም፡፡ ካልካድን በቀር ወደዚህ ወደተዋረደ ማንነት አንመለስም፡፡ መመለስም አንሻም፡፡ ይልቁኑ ከዚህ ፍጥረታዊ ሥርዓት የምንወጣበትን ሕይወትን ገንዘብ ለማድረግ ክርስቶስ በእኛ እስኪገለጥ ድረስ እለት እለት ወደ እርሱ ለማደግ እንደክማለን፡፡ 
እኛ ፀሐየ ቅዱሳን የሆነውን ጌታችንን ለብሰን መለኮታዊ ብርሃኑን ተጎናጽፈን ለዘለዓለም ከእርሱ ጋር ተዋሕደን ልንኖር እንጂ በምድራዊ አልባሳት ልናጌጥ ክርስቲያን አልሆንም፡፡ እኛ ዘለዓለማዊ ሕይወትን በሚሰጠን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ የኃጢአት አረማችን ተነቅሎና ተቃጥሎ መለኮታዊ እሳት በሚሰጠን ሕይወት እሳታውያንና መንፈሳውያን ልንሆን ተጠራን እንጂ በምድራዊ ኅብስትን ውኃ ሕልውናችንን ልንመሠርት ክርስቲያን አልሆንም፡፡ እኛ እርሱ የፍጥረት አስገኚና የዕውቀት ባለቤት የሆነው ጌታችንን በመንፈስ ቅዱስ ዕውቀታችን አድርገነው አዋቂዎች ልንሆን ተጠራን እንጂ በምድራዊ ጥበብ በእርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ድንቁርና በሆነ ዕውቀት አዋቂዎች ልንባል አልተጠራንም፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ከእርሱ ጋር ፍጹም የተዋሐድን እንደሆነ የፍጥረታውያን ዕውቀት ለእኛ የሚሳተን አይሆንም፡፡ ረቀቂ ከሆነ መለኮት ጋር ልንረቅ እንጂ በግዘፍ ልንመላለስ አልተጠራንም፡፡ የአብና የወልድ እስትንፋቸው የሆነው መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን ሕይወት እንጂ ፍጥረታዊት ነፍስ በምትሰጠን ሕይወት ልንኖር አልተጠመቅንም፡፡ ስለዚህ ግባችን የሚሆነው ክርስቶስን መመሰል ነው፡፡
ይህ ለእኛ ይቻለን ዘንድ ክርስቶስን መስለን በጥምቀት ተወልደናል፡፡ ይህ ግን ቀስ በቀስ የሚሆን እንጂ በአንዴ የሚፈጸም አይደለም፡፡ ጾም በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ሆነን መኖር የምንለማመድበት ቀስ በቀስም ከፍጥረታዊ ሥርዓት የምንወጣበት መንፈሳዊ ጎዳና ነው፡፡ ጸሎት ጣዕመ እግዘአብሔርን የምናውቅበት ነው፡፡ መጻሕፍት እንደ ነቢዩ ኤልያስ የአምላክን ፊት ለማየት ወደ ሰማየ ሰማያት የምንነጠቅባቸው የእሳት ሠረገላዎች ናቸው፡፡ ጽሙናና ተመስጦም ከጌታ ጋር ተዋሕዶ የመኖርን ትርጉም የምንረዳባቸውና ያለ ምግብ ያለመጠጥ ያለ አየር መኖር እንደሚቻለን የምናረጋግጥባቸው ናቸው፡፡ በዚህ መልክ ይህን ዓለም ቀስ በቀስ እየተውን አኗኗራችንን ከክርስቶስና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም ካሉ ቅዱሳን በሰማያዊ ሥፍራ ካሉ ቅዱሳን ነፍሳት ከቅዱሳን መላእክት ጋር እናደርጋለን፡፡ 
እዚህ መዓርግ ከደረስን በዚህ ምድር ሆነን የትሣኤን ሕይወት አጣጣምን ማለት ነው፡፡ ያኔ ወዳጆቼ ሆይ እኛ ላይ የተነሡ እኛ የማንጠላቸው እነርሱ ግን ጠላቶች ያደረጉን ሲዋጉን የእነርሱ ውጊያ ከጌታ ጋር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ከጌታ ጋር ተዋሐደን የእርሱ ገንዘብ ሆነናልና፡፡ ያኔ በእኛ ላይ በጠላትነት የተነሣ አካል ቁጥሩ ጌታችንን ከሰቀሉት ከአይሁድ ወገን ይሆናል፡፡ ስለዚህ እናጠፋችኋለን ሲሉ እነርሱ ይጠፋል፡፡ እንደመስሳችኋለን ሲሉ እነርሱ ይደመሰሳሉ፡፡ ስለዘህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ትምክህቱን በጌታ ላይ አድርጎ “… በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን፡፡ ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ" ማለቱ፡፡ ይህች ናት ተዋሕዶ፡፡ ስለዚህ ቅዱሳኑ ከአሕዛብ የሚደርስባቸውን መከራ በእቅፍ ውስጥ ባለ ሕፃን መዳፍ በጥፊ እንደመመታት አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ እንዲህም ስለሆነ ስለእነርሱ መዳን አልቅሰው ይለምናሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ፡- “… በሚጠሉኝም ላይ አትፍረድ፡፡ ነገር ግን የአንተ የሆነውን አውቀው ፈቃድህን ይፈጽሙ ዘንድ ጸጋህን አድላቸው”(ቅዱስ አፍሬም) በእውነት ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

1 comment:

  1. Girum Asetemehero newe. Memeher Ka'le Hiwote Ya'semalem.

    ReplyDelete