Wednesday, December 11, 2019

ዳርዊን ቲዎሪውን ከየት አገኘው ?


በመ/ር ሽመልስ መርጊያ
ቀነን 01/04/2012


ወገኖቼ አንድ ነገር ልብ ብላችሁ አድምጡኝ፡፡ አንድ የካቶሊክ መነኩሴ ዳርዊን እርሱ የጻፈው ግልበጣ(ኩረጃ የራስ አስመስሎ ማቅረብ) መሆኑን ያስተዋለው ሰው ማን ነው? ከየት ብትሉኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ገልብጦ ብላችሁ ምን ትሉኛላችሁ? ግን እርሱ እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረውን የሰው ልጅ ገልብጦ ዝንጀሮ አድርጎ ሴኩላር ቀለም ቀባው፡፡ እስቲ አስተውሉ፤ አዳምን የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሔዋንን የዐሥራ አምስት ዓመት ኮረዳ አድርጎ የፈጠረ አምላክ ምድርና በውስጧ ያሉትን የቢልዮን ዓመታት ዕድሜ እንዲኖራቸው አድርጎ መፍጠር ይሳነዋል ብላችሁ ታስባላችሁን? እናም ወዳጆቼ ይህን ሐሳብ ከየት ስቦ እንዳመጣው ተገንዘቡ እርሱ መነኩሴ ነበር ማለት ስለመጽሐፍ ቅዱስ ጠንቅቆ ያውቃል ማለት ነው፡፡


ስለዚህ የአዳምንና የሔዋንን ከገነ መሰደድ ስታስቡት የዳርዊንን ቲዎሪ ምንጩን በቀላሉ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አዳምና ሔዋን በድለው ከገነት ወደዚህች ምድር ተጣሉ፡፡ ከመጣላቸው በፊት ግን እግዚአብሔር አምላክ ራርቶላቸውየቁርበት ልብስ አደረገላቸውየሚል እናነባለን፡፡(ዘፍ.321) ወዳጆቼ ለቁርበት ልብሱ ምንድን ነው? ከውድቀት በፊት ቁርበት ስላlልነበረን ርጥብ ሥጋችንን ነበርን ማለቱ ነበርን? ከቁርበታችን ውጭ ብንሆን ምን እንመስል እንደነበረ አስቡት እስቲ፡፡ ስለዚህ የቁርበት ልብስ ሲል ቁርበታችንን ሳይሆን ቁርበታችን ያለበሰው ጸጉር መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ስለዚህም ከውድቀት በኋላ ሰው ከቆዳ ወይም ከጥጥና ከዕፅዋት ልብስ ሠርቶ ከመልበሱ በፊት በጸጉር የተሸፈነ አካል እንደነበረውና ይህንንም የቁርበት ልብስ አድርጎ እግዚአብሔር እንደሰጠው ማስተዋል እንችላለን፡፡

እናም አጅሬው ዳርዊን ይህን አሰላስሎ ደርሶበት ወይም ተምሮት አግኝቶት አይታወቅም ለወጥ አድርጎ እግዚአብሔርን ክዶ ሰው ዝንጀሮ ከሚመስል ፍጥረት መጣ ብሎ ደፍሮ አስተማረ፡፡ ከዚያም በዋሻ ኖረ፣ ፍራፍሬ መመገብ፣ እንስሳት እያደነ መብላትና ቆዳቸውን መልበስ ቀስ በቀስም ወደ እርሻ መምጣቱን ያትታል፡፡ አስተውሉ አዳምና ሔዋን ከገነት በተባረሩ ጊዜ ጸጋቸው ተገፍፎ፣ ፍርሃት ነግሦባቸው፣ አራዊት በእነርሱ ላይ በጠላትነት ተነሥተውባቸው፣ በቀላሉ የሚጎዳ አካል ገንዘባቸው አድርገዋልና ቤት እሰኪሠሩ ድረስ ለመጠለያቸው ዋሻን ቢመርጡ፣ ሲርባቸው ከምድር ፍሬ ቢመገቡ፣ ፍራፍሬዎቹም ሲያልቁባቸው እንስሳትን እያደኑ ቢመገቡ፣ ቀስ በቀስ በቆዳቸው ልብስ ሠርተው መልበስ ቢጀምሩ፣ ከድንጋይና ከእንጨት የመገልገያና የጦር መሣሪያ ቢሠሩ ምን የሚደንቅ ነገር አለው? ስለዚህ ወዳጆቼ የዳርዊንን ብልጠት ተመልከቱልኝ፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ የዳርዊን ቲዎሪ በማለት ዩኒቨርስቲዎቻችን የሚያስተምሩን፡፡

2 comments: