Showing posts with label ተግሣጻትና ጸሎታት. Show all posts
Showing posts with label ተግሣጻትና ጸሎታት. Show all posts

Wednesday, January 23, 2019

በዓመፃ ገንዘባችሁ እወቁበት


በመ/ ሽመልስ መርጊያ
 14/05/2011
ልቡናችሁን መቅደሱ አድርጋችሁ በእርሱ ፍቅር ከብራችሁ የምትኖሩ በክርስቶስ ወንድሞቼና እኅቶቼ የሆናችሁ ወዳጆቼ ሆይ እንደው አንድ ሐሳብ ወደ ሕሊናዬ መጣና ሳወጣው ሳወርደው ለምን ከእነርሱ ጋር አብሬ አልጋራውም አልኩና እነሆ አልኳችሁ፡፡
ተወዳጆች ሆይ በእውን እንደ ሰው ምስኪንና የራሱ ያልሆነውን የእኔ ብሎ ዕውር ድንብሩን የሚጓዝ አለን ? የሚደንቀው ግን እርሱ በራሱ አርአያና አምሳል የፈጠረን አምላክ ባልፈጠርነውና የእኛ ባልሆነው ላይ አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ ሾመን፡፡ ይህም ባሕርይው በእኛ እንዲከብር ገዢነቱ በእኛ እንዲገለጥ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ፍጥረቱ ላይ እንዲህ እንድንሰለጥን ማድረጉ ለሰው ልጆች የሰጠው የመጨረሻው ስጦታው አይደለም፡፡ ይህ ዓለም ለሰው ልጆች እንደ ድርጎ የተሰጠ እንጂ መሠረታዊም አልነበረም፡፡ በአባታችን በአዳም በእናታችን በሔዋን ውስጥም እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አልነበረም፡፡ ያኔ በገነት ለማየትና ለመብላት መልካም ሆነው የተሰጡ አትክልትና አዝዕርት እንዲሁም እንስሳት ሁሉ ለመኖር አስፈላጊዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ በእነርሱ ላይ ይሰለጠኑ ዘንድ በተሰጣቸው ላይ የተንኮል ድሩን ማድራት አልፈቀደም፡፡ ነገር ግን እርሱ አፍቃሪያችን በጊዜ ሂደት እርሱ በፈቀደው ጊዜና ሰዓት እርሱን ወደ መመሰል አምጥቶ አማልክት እንደሚያደርገን በዲያብሎስ ዘንድ የታወቀ ነበር፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ ያለ ጊዜው አምላክ የመሆን ምኞትን አስቀድሞ በሔዋን ሲቀጥል በአዳም ልቡና ውስጥ አሳድሮ ከአምላክ ለያቸው፡፡ እኛም በእነርሱ ምክንያት ወደዚህች ድርጎው መሠረታዊ ነገር ወደ ሆነባትየእለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬብለን እንድንጸልይ ወደ ተገደድንባት ምድር ተጣልን፡፡

Monday, March 26, 2018

ቅዱሳን ሆይ ለምኑልን



  በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
መጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ.ም
ሰውነታችሁን በእውነት በጽድቅ ሕይወት ቤተ መቅደስ አድርጋችሁ እርሱ የሁሉ ጌታ የሆነ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስተ ቅዱሳን በሆነች ነፍሳችሁ መንገሡ የሚታወቃችሁና እርሱን አውቃችሁ እጅግ ትሑታን ሆናችሁ የምትመላለሱ ቅዱሳን ሆይ እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ የእናንተ ጭንቀት በሰውነታችሁ መቅደስ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ነግሦ ያለውን ጌታ አለማሳዘን የሆነ በሕሊናችሁ ውስጥ ስለምታሰላስሉት ሓሳብ እንኳ የምትጠነቀቁ ቅዱሳን ሆይ እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ እናንተ በሦስት አጥሮች ራሳችሁን አጥራችሁ ግርማውን እያያችሁ እንደ ቅዱሳን መላእክት በፍርሃትና በርዓድ ሆናችሁ በእርሱ ፊት ዘወትር የምትቆሙ ቅዱሳን ሆይ በእውነት እናንተ ንዑዳን ክቡራን ናችሁ፡፡ 

Monday, October 30, 2017

ጌታ ይባርክህ ማለት ለማን ነው?

በዲ/ ሽመልስ መርጊያ
21/02/2010


የሁሉ ፈጣሪ የሆነው የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ይህ ነው፡- በእውነት መዳንን ለሚሻ ወገን እንደ ኦሪቱ ጥላውን ሳይሆን ወይም አይሁድ በስደት ሳሉ በሙክራባቸው እንደሚፈጽሙት ዓይነት አምልኮ ሳይሆን በእውነት በእርሱ በክርስቶስ በጎውን ለማድረግ ተፈጥሮ፣ በእርሱ እረኝነት ሥር ሆኖ፣ ግልገል ጠቦት በግ ተሰኝቶ፣ ሰማያዊ ሥፍራ በተባለችው መንግሥቱ ውስጥ በእርሱ መለኮታዊ ብርሃን የቀን ልጅ ተብሎ ከጸጋው እየተመገበ እንዲኖር ነው ፈቃዱ፡፡
ይህች ዓለም ደግሞ ኢአማኒያን ዓሣትን ማጥመጃ ባሕር፤ ሰማያዊ ንግድን ነግደው የሚያተርፉባት ገበያ፣ በእግዚአብሔር እርሻ ውስጥ ንጹሕ ዘርን ዘርተው ሰላሣ ስልሳ መቶ ፍሬ የሚያፈሩባት ምድር ናት፡፡ ሁላችንም ኅብረታችን ከአንዱ እግዚአብሔር ጋር ነው ፍላጎታችንና መፈለጋችን ፈቃዳችንም እርሱ ነው፡፡ እምነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው ጉድፍ ጋር ኅብረት የለውም፡፡
ነገር ግን  የገነትን ጣዕም ያስረሱንን አዳምንና ሔዋንን ያሳተ ሰይጣን ከዚህች ረቂቅና ሰማያዊ ሥፍራ እኛን ለማስወጣን ይደክማል፡፡ ይህ የሚጠበቅ ነውና ጌታችን እኛን በሁሉ መስሎ ዲያብሎስን ድል በመንሣት ድል መንሣትን ለእኛ ሰጠን፡፡ የሚያሳዝነው ግን በምድር ያሉ ሁሉ የእርሱ ሲሆኑ እርሱ ቸሩ ፈጣሪ ለሰዎች ሲሰጣቸው ሰዎች ደግሞ የሰጣቸውን መልሰው ለዲያብሎስ በመስጠት ምንም ሳይኖረው ዲያብሎስን የዚህ ዓለም ገዢ ማድረጋቸው ነው፡፡ እርሱ ረቀቅ መንፈስ ነው፡፡ ምድር ደግሞ በዋነኝነት ለሰዎች የተሰጠች ናት፡፡ ምድር ለእኛና ለምድር ፍጥረታት የሚስማማ ተፈጥሮ እንጂ ለዲያብሎስ የሚስማማ ተፈጥሮ የላትም፡፡ ከምድር ፍሬ ዲያብሎስ ለመኖር ሲል አይበላም አይጠጣም አየሩም አያስፈልገውም፡፡ ድካምም የለበትም ዕረፍትም አያሰፈልገውም፡፡ ታዲያ ምን እንዲሆነው ነው የምድርን ገዢነት ለእርሱ የሰጡት?
ይበልጡኑ ግን ሰዎች በስሜ ይመጣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ እንዲል ጻድቃን መስለው የዲያብሎስ ባሪያዎች መሆናቸው ነው የሚያሳዝነው፡፡ ጌታ ብለው የሚሰብኩን ፍጡር ስለሆነው ወደ ፊት ስለሚመጣው እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስለሚለው ነው፡፡ ይህን ከፍሬአቸው ታውቃላችሁ፡፡ በዚህ ዘመን ለሃሳዊው መሲህ ነቢያትና መንገድ ጠራጊዎች የሆኑ ምድሪቱን ሞልተዋታል፡፡ ሁሉም ጌታ ኢየሱስ ስላለ እውነተኛውን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እየጠራ በእርሱም ስም እየባረከ አይደለም፡፡ ሰይጣንም እንዲሁ ያደርጋል የእርሱ ብራኬ ታዲያ ምን ያደርግልናል? በዚህ በምናባቸው በተፈጠረው ኢየሱስ ስም ወይም በሃሳዊው መሲህ ስም ቢባርኩንም ቢረግሙንም ያው አንድ ነው፡፡ ሁለቱም ለእኛ የማይጠቅምም የማይጎዳም ነው፡፡ በእኛ ላይ አንዳች ስልጣን የለውምና፡፡ ይልቁኑ እኛ በእርሱ ላይ ስልጣን አለን፡፡
የድንግል ልጅ ባልሆነው ኢየሱስ ስም መባረክ ማለት በእርግጥ እርግማን ነው፡፡ ርግማኑ ግን በራሳቸው ላይ እንጂ በእኛ ላይ አይደለም በጣዖት ስም እየባረኩና እየረገሙ ናቸውና፡፡ ለምን ብትሉኝ አንደኛ የጌታችንን ስም ለፍጡር ያውም ለእርሱ ተቃዋሚ በመስጠታቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ለዚህ ሃሳዊ መሲህ ልባቸውም አንደበታቸውም መገለገያ መሣሪያ ማድጋቸው ነው፡፡ በሦስተኛነት ደግሞ ጻደቅ መስለው ሌሎችን በመሸንገላቸውና ወደ ጥፋት በመጣላቸው ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ደግሞ የድንግል ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ከመልበስ፣ ከመመገብ፣ ከመጠጣት፣ በእርሱ ውስጥ ከመኖር በላይ ምን የተሻለ መባረክ አለና ነው ጌታ ይባርክህ የሚሉን? ነገር ግን በድንግል ማርያም ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብትባርኩን እሰማችሁ ይሆናል፡፡ እንዲያም ቢሆን ግን በበልዓም ሥፍራ ሆናችሁ ስለሆነ ለእናንተ በእጅጉ አዝናለሁ፡፡
በኋለኞቹ ዘመናት በስሜ ይመጣሉ የተባሉ እነዚያ ሃሳውያን የሰይጣን ሎሌዎች ለሰው ልጆችም ሆነ ለራሳቸው እንደ አባታቸው ዲያብሎስ ጭላጭ ፍቅር የላቸውም፡፡ ግን እኛ እነርሱ ለዲያብሎስ መሳሪያ በመሆናቸው ብናዝንም እንድንጠላቸው አልታዘዝንም፤ ጠላትህን ውደድ ማለት እንዲህ ነውና፡፡ እነርሱ በዲያብሎስ ታውረው ይጠሉናል እኛ ግን እንዲሁ እንወዳቸው ዘንድ ታዘናል፡፡ ሰይጣንንም ቢሆን በእግዚአብሔር ፍጥረትነቱ አንጠላውም፡፡ ነገር ግን ተግባሩን እንጠላለን፡፡
እርሱ የፍቅር ጠላት ነውና ፍቅር የቀዘቀዘው እርሱ የጥል አባት ስለሆነ መለያየትን በሰዎች ላይ በመዝራቱ ነው፡፡ ጌታችንም “አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥት ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን የእለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ በደላችንን ይቅር በለን እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል” እያልን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ እንድንጸልይ አዞናል፡፡ ይህ ጸሎት ልመናም ምልጃም ነው፡፡ ጸሎቱ፣ ምልጃውና ልመናው በምድር ላሉ ሁሉ ነው፡፡ “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” እንዲል፡፡
“የሚጠሉዋችሁን ብትጠሉ አሕዛብም ይኸንኑ ያደርጋሉና ምን ዋጋ አላችሁ?” እንዳለ ጌታችን መንግሥቱም በፍቅር የምትገለጥ ናት፡፡ እርስ በእርሳችሁ ብትዋደዱ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደሆናችሁ ሰው ሁሉ ያውቃል ይለናል፡፡ ግን እርስ በእርስ ብትነካከሱ የክርስቶስ አይደላችሁም፡፡ የክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ፍቅር አለ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ “አንድ እግዚአብሔር፣ አንድ ጌታ ፣አንዲት ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት፣ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ብሎ በአንድ አካል ያሉ እርስ በእርስ ፍጹም እንዲዋሐዱ ማድረጉ ስለምን ይመስላችኋል? እንዲህ አድርጎ ጌታችን እኛን በአዲስ ተፈጥሮ መፍጠሩ አምላክ መለያየትን በሚዘሩና ፍቅርን በሚያጠፉ ወገኖች ደስ እንደማይሰኝ ያሳየናል፡፡ በመስቀሉ አንድ ሊያደርገን ስለእኛ በመስቀል ላይ ዋለ፡፡ በስቅለቱም እኛን ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሳበን ከቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጉባኤ ደመረን፡፡ ምድር ሰማይ ሆነች ሰማያውያንም በምድር በክርስቶስ ካሉ ጋር ኅብረትን ፈጠሩ፡፡ ይህ የሆነው ስለ ፍቅር ነው፡፡ እናም ዘመዴ ጌታ ያደረግኸውን ሳታውቅና ሳትለይ ጌታ ይባርክህ አትበለን፡፡ እኛ በእርሱ ያጣነው የጎለብን አንዳች ነገር የለምና፡፡

Tuesday, May 2, 2017

የሕይወታችን ሁለቱ ጫፎች


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
25/08/2009

በሕይወታችን ጫፍና ጫፍ ያሉ ጊዜአትንና ተፈጥሮአዊ ባሕርያቸውን ሳስባቸው ግርም ድንቅ ይለኛል፡፡ መመሳሰላቸውንም ሳስብ ደግሞ ይበልጥ እደነቃለሁ፡፡ እነርሱም ሕፃንነትና አረጋዊነት ናቸው፡፡ ሁለቱም ከሌላ አካል አካላዊ ድጋፍን የሚሹ ናቸው፡፡ የሁለቱም ፆታ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ አንዱ በተፈጥሮ ስላልተዘጋጀ ሌላኛው ግን ተፈጥሮ ራሷ ከአገልግሎት ስላወጣችው ነው፡፡ እናም ሁለቱም በመላእክት ሥርዓት የሚኖሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም የእኛ ፈቃድ ሳይጠየቅ በአምላክ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ ነገር ግን አንዱ ወደዚህ ዓለም የሚያስገባ በር ሲሆን ሌላኛው ወደማታልፈው ዓለም የሚያሸጋግር መውጫ  ነው፡፡ ጎዳናቸው ግን አንድ ነው፡፡ አንተ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንዲል ከምድር አፈር ከተበጀ አካል ተወልደን ወደ ቀደምት የአያታችን ማኅጸን ወደ ሆነች ምድር እንገባለን፡፡ ከእርሷም በትንሣኤ ተወልደን ለፍርድ በአምላክ ፊት እንቆማለን፡፡ በሥጋ ከወላጆቻችን ተወልደን በየሰከንዷ በሞት ጎዳና እንጓዛለን፡፡ አንዱ ይቀበላል ሌላኛው ይሸኛል፡፡ አንዱ በባሕርይው ያልተዳደፈ ንጹሕ ሲሆን ሌላኛው ግን ንጽሕናውና ቅድስናው እንደ ግብሩ ይወሰናል፡፡ ዕድሜችንን ሙሉ መልካምን በመሥራት ካሳለፍን በንጽሕናና በክብር ከሕፃንነት እንበልጣለን፡፡ አንዱ ለአዲስ ሕይወት የተዘጋጀ ሲሆን ብዙ ፈተናዎች ከፊቱ ይጠብቁታል፡፡ ሌላኛው ግን በዚህ ዓለም መኖርን አስረጅቷት የሰማያዊውን ሕይወት ጣዕም ማጣጣም የሚጀምርባት ሲሆን የኖረባትም ምድር እርሱን ከአገልግሎት ጡረታ የምታወጣበት ዕድሜ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶ ለእርጅና ከበቃን  የሞትን ጣዕም በእርጅናችን ማጣጣም እንጀምራለን፡፡ ሞት በአካላችን ሥራውን መሥራት ስለሚጀምር ጉልበታችን ይከዳናል፤ ዓይናችን ይፈዛል፤ ጆሮችን ይደነግዛል፤ አካላችን ይቀዘቅዛል፤ ጠጉራችን ይሸብታል ወይም ይመለጣል፤ ቆዳችን ከአጥንታችን ጋር ይጣጋል፤ ወዛችን ይረግፋል፤ መዓዛችን ይለወጣል፡፡  ያኔ መልካምን ሠርተን እንደሆነ አምላክ ቶሎ ወደ እርሱ እንዲወስደን እንለምነዋለን፡፡ ካልሆነ ግን በነፍስም በሥጋም ስቃያችን ይጨምራል፡፡ ወገኖቼ በእርጅና ሲኦልን በሚመስል ሕይወት ውስጥ ከመኖር ይጠብቀን፡፡  

Sunday, March 26, 2017

ምጽአቱ ለክርስቶስ


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/07/2009


ወዮ ይህች ከእውነተኛ ጌታ የወጣች ትምህርት እንዴት ታስፈራለች ? እርሱ  ስለትንሣኤ ሕይወታችን በዐሥሩ ደናግላን መስሎ አስተማረን እንዲህም አለን፥-"በዚያን ጊዜ" ያላት ያችን የምታስፈራዋን የምጽአቱን ቀን ነው።  በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች" አለን። በአሥሩ ደናግላን የተመሰልነው እኛ በጥምቀት ለክርስቶስ የታጭነው ክርስቲያኖችን ነን። ስለሆነም ጌታችን ክርስቲያን መሆናችን ብቻ እንደማያድነን እምነትን ከምግባር፥ እምነትን ከፍቅር ጋር፥ እምነትን ከጦም ከጸሎት ከስግደት ከምጽዋት ጋር አብረን አስተባብረን ይዘን የብርሃን መላእክትን መስለን ራሳችንን ከኃጢአት ጠብቀን የጌታን መምጣት በናፍቆት እንጠብቅ ዘንድ እንዲገባን ሊያስተምረን እንዲህ አለን።

Sunday, February 19, 2017

የምትጠቅመዋ ኅዘን እናት



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
13/06/2009

ጠቢቡ ሰሎሞን በመክብቡ  " ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና"(መክ.7:3) ብሎ አስቀድሞ ጻፈልን።  ከሃዘን በኋላ ደስታ እንዳለ እንዲሁ ጌታችን  "የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና"(ማቴ.5.4) ብሎ አስተማረን።  መጽናናትንና ደስታን የሚሰጠው እንዴት ያለ ኅዘን ነው? ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ጳውሎስ ሲመልስ "እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል"(2ቆሮ.7:10) ብሎ አብራራልን። የዚህች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነች ኅዘን እናት ደግሞ ጦም ናት።
ጦም ራስን ወደ ማስተዋል የምታደርስ፥ በዚህም ምክንያት የራሳችንን ግንድ የሚያህል ኃጢአት ለማየት የምታበቃን፥ የሚያቃጥል የንስሐ እንባ እንድናነባ ምክንያት የምትሆነን፥ ራስን በአምላክ ፈቃድ ውስጥ ለማሳደር የምታስጨክን፥ ኅጢአትን አጥብቀን እንድንጸየፋትና ከምክንያቶቿ እንደ አቦ ሸማኔ በፍጥነት እንድንሽሽ የምታደርገን ናት። ይህች ጦም አስቀድመን እግዚአብሔርን መፍራት፥ እግዚአብሔርም መፍራት ንስሐን፥ ንስሐ ደግሞ መጽናናትንና የማይቀማ ደስታን፥ መጽናናትና ደስታ ደግሞ እግዚአብሔርን ማፍቀር እግዚአብሔርን ማፍቀር ፍጥረትን ሁሉ ወደ ማፍቀር የምታደርስ ጎዳና ናት።

Tuesday, January 24, 2017

ጸሎት በእንተ ሰንበት


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
16/05/2009


ኦ የዘለዓለም አምላክ ጌታችን ሆይ!!  የሰንበት ጌታዋ የሆንኽ፣  ሰንበታችንም የሆንኽ እባክህ እኛም የሚቀዋወመንን የሥጋ ፈቃድ ጸጥ አድርገን ልባችንን የቃልህ ጽላት፣ ሰውነታችንን ማደሪያ ቤተ መቅደስህ አድርገን፤ አንተ ግዛታችን ሆነህ እኛም በእውነት ርስትህ ሆነን እኛም ሰንበት እንባል፤ አንተም በሚታይና በተገለጠ ጌታችን ሁነን ያኔ እናርፋለን እረፍታችንም የማይወሰድ ይሆንልናል፡፡ እኛ ፈቃድህን ፈጻሚዎች አንተም በእኛ የምትገለጥ ሁንልን፡፡ ስለምን እሾህና አሜካላ ታብቅልብህ ተብላ በተረገመች ምድራዊ ሥርዓት ውስጥ ወላጅ እንደሌለው ሰው ሆነን ተጥለን እንቅበዘበዛለን፡፡ ጌታ ሆይ እኛን የአንተ ከማድረግህ በፊት በአንተ ከእናታችን መኅፀን ፈጠርኸን፤ ቅዱስ ጳውሎስ እኔ እተክላለሁ አጵሎስ ያጠጣል እግዚአብሔር ግን ያሳድጋል እንዲል ሁሌም ቢሆን አንተ ከሕዋሳታችን ጋር ነበርህ በአንተ ፈቃድ አደገን እንጂ ራሳችንን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን አይደለንም፡፡ ምርጫ ሰጠኸን ምርጫችን በወላጆቻችን እጅ በነበረበት ጊዜ እነርሱ ለአንተ ቀደሱን ልጆችህም አደረጉን፡፡ በራሳችን በቆምን ጊዜ የወላጆቻችን ምርጫ ትክክል እንደሆነ ገብቶን የወላጆቻችንን ምርጫ በምርጫችን አጸደቅነው፤ ለአንተም ሆንን፡፡  ምክንያቱም አንተ በእውነት ሰላማችን፣ እረፍታችን ሕይወታችን ነህና፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ ከዚህ ዘለዓለማዊ ከሆነ ሰላም፣ እርጋታ፣ ፍቅር፣ ሕይወትና እውነት እባክህ አታውጣን በእርሱ ያመነ ወደ እረፍቱ ገብቶአል ይላልና በተግባር አንተን በመምሰል በአንተ ጥላ ሥር እንመላለሰ ዘንድ እባክህ ፍቀድ፤ ጤናችንን መልስ ልጆቻችንን ባርክ እኛንም በዓለም ከመባከን ታደገን፣ ሥራችንን ባርክ፣ ጌታ ሆይ በሁሉ የሆነብንን ታውቃለህና እርዳን ለዘለዓለም አሜን፡፡

Tuesday, March 24, 2015

ተወዳጆች ሆይ ጦሙ እንዴት ይዙአችኋል?

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/07/2007

መቼም ጦምን ከጸሎት ጋር አስተባብሮ የያዘና ራሱን በእግዚአብሔር ፊት አቁሞ ስለ መተላለፉ በአምላኩ ፊት የሚያነባ ክርስቲያን የንስሐ እንባው የኃጢአት እድፉን ጠርጎ ስለሚያስወግድለት በሰዎች ላይ የማይፈርድ፥ እንደ ግብዝ ጦመኞች ልታይ ልታይ ማለት የሌለበት፥ ለሰው ልጅ ያለው ፍቅር የበዛለት፥ አንደበቱም ይሁን ልቡ ከጸሎትና ከልመና እንዲሁም ከምልጃ የማያርፍ ፥ ቃሉን ማንበብ የሚወድ፥ በቃሉ መመሰጥ የሆነለት፥ የራሱን እንጂ የሰዎችን ነውር ለማየት የማይፈቅድ፥ ስለራሱ ኃጢአት በአምላኩ ፊት በመንፈስ ሆኖ የሰማይን ፊት እንኳ ለማየት የማልበቃ ኃጢአተኛ ነኝ እያለ ደረቱን የሚደቃ ሰው መሆንን ገንዘቡ እንደሚያደርግ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። 

Saturday, November 1, 2014

ተወዳጆች ሆይ



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/02/2007

ወገኖቼ ሆይ አንድ የልብ ምክር አለኝና አድምጡኝ፡፡ ወዳጄ የቤተሰብ ሓላፊ ከሆንህ - እኔ ለቤተሰቤ እንደ ኢዮብ ካህን ነኝ ስለዚህ በመንፈስ ሁል ጊዜ፤ በአካል ደግሞ እንደ ችሎታዬ መጠን ስለራሴ ምክንያቱም በመልካም ማስተዋል ቤተሰቤን እመራ ዘንድ ስለቤተሰቤ ምክንያቱም ቤተሰቤ በኃጢአት ምክንያት አእምሮው እንዳይቆሽሽ በራስ መተማመን እንዳያጣ በማስተዋልና እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲመላለሱ ስለሀገሬ ሰዎች ደግሞ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ማስተዋልንና እርስ በእርስ መግባባትን እንዲሰጣቸው ፍቅር እንድትነግሥ ስለዓለሙ ሁሉ ደግሞፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁንእንድንል ጌታ እንዳስተማረን የምንኖርባት ዓለም ፈቃዱን ለማድረግ እንደሚተጉ መላእክት ለመልካም ሥራ እንዲበረቱ በጸሎት መትጋት አለብኝ ብለህ ለልብህ ንገረው፡፡

Sunday, October 19, 2014

ተወዳጆች ሆይ ዓይኖቻችሁ ከወዴት ናቸው?



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
9/02/2007
ተወዳጆች ሆይ ዓይኖቻችሁ ከወዴት ናቸው?ዓይንን ስናነሣ ግን ሰው ሁለት የነፍሰ ዓይኖች እንዳሉት ቅዱስ ይስሐቅ ወይም ማር ይስሐቅ ይናገራል፡፡ አንዱዋ የነፍሳችን ዐይን ፍጥረትን አፍ እንደተገጠመ ጆሮም ከመስማት እንደተከለከለ ሀሳብም ጌታ ጸጥ እንዳሰኘው የባሕር ማዕበል ከምድራዊ ፍላጎቶች ጸጥ ብላ የፍጥረታዊውን ዓለም ጥንተ ተፈጥሮውን ተመልክታ ፈጣሪዋን ስታደንቅና ግሩም ግብሩ ለእግዚአብሔር ብላ ስታመሰግን ሌላኛይቱ ዓይን ደግሞ በርቀት(በረቂቅነት) በሁሉ ሙሉ ሆኖ የሚኖረውን አምላክ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን በእምነት ተመልክታ ብርሃናዊውን የመላእክትን ምግብ እርሱም ፍቅሩን እየተመገበች ቅዱስ ዳዊት ዓይኖቼ አንተን በማየት ፈዘዙ እንዳለው በትንግርትና በመደመም ስትመለከተው ትኖራለች፡፡ ያልታደለችው ዓይን ግን ራሱዋን ሳትመለከት የሰውን ጉድለት እያየች ለአእምሮ ሐሜትን እየመገበች ሰውነትን ስታሳድፍ ትኖራለች፡፡

Saturday, May 25, 2013

አቤቱ ይህን አትንሣን!!!



17/09/2005
በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ሰው የሚድነው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው “በጸጋ ድናችኋልና” እንዲል፡፡ ክርስቶስ ዘለዓለማዊውን ጸጋውን ከሰጠን ቆየ ክርስትናም በክርስቶስ ከተመሠረተች እጅግ ቆየች ግን አሁንም ያው ነች ሰማያዊት ናትና የዘመን ቁጥር የላትም ሁሌም አዲስ ናት፡፡ ሰዎችን ዘመን ከማይቆጠርባት ሰማያዊት ሀገር ታፈልሳለች በዚያም ሰማያውያን ቅዱሳን መላእክትና ቅዱሳን ነፍሳት ከትመዋል፡፡ ሰው ልቡናው ከበራ የሚኖርባትን ዘመን የማይቆጠርላትን ሰማያዊቱን ዓለም ይረዳታል ጣዕሙዋንም ይቀምሳል፡፡ ጣዕሟን ማንም በቃላት ሊገልጣት አይችልም፡፡ ለዚህ ዓለም ቋንቋ ባዕድ ናት ሕይወቱዋም ልዩ ነው፡፡ ይህችን ጣዕም እየቀመሱ መኖር እንዴት መታደል ነው!!! ቢሆንም የሚወደን አምላክ እርሱዋን አልነሣንም ግቡም ይህ ነው የዚህች ሰማያዊት ስፍራን ጣዕም በሁለመናችን እንረዳትና በእርሱዋ ውስጥ ለዘለዓለም እንድንኖር ነው፡፡ ጌታ ሆይ ከዚህች ሥፍራ በመንፈስ እንዳንወጣ ሁሌም የዚህችን ሰማያዊት ሥፍራ እያጣጣምን እንድንኖር እርዳን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

Friday, December 21, 2012

አርምሞ (ለአንድ ወንድሜ የጻፈኩት)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊ
12/04/2005
አርምሞ ከራስ ጋር ለመሆን ጊዜን ከመስጠት የሚጀምር ነው፡፡ እንዲያው በባዶ ግን አይደለም፤ አስቀድሞ የግል ጊዜ ሊኖረን  ግድ ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ዐይን ውስጥ ትንሽ ብናኝ ብትገባ እንደምትረበሽና እንደምትታወክ ከዚያም በላይ አንደምታለቅስ እንዲሁ ሕሊናም ጥቃቅን በምንላቸው ኃጢአቶች መረበሹና መታወኩ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ሕሊናችን በኃጢአት ከተያዘ መረጋጋትን ገንዘባችን ማድረግ አይቻለንም፡፡
ነገር ግን ሕሊናችን ከኃጢአት ነጽቶ እርጋታን ገንዘቡ ሲያደርግ በጥሙና ሆነን ያለ አንዳች መደነቃቀፍ መንፈሳዊውን ዓለምና ምሥጢር ወደ መረዳት እንመጣለን፡፡ ስለዚህ ወደ ጥሙና ሕይወት ከመግባታችን በፊት አስቀድመን ለንስሐ ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን በኋላም ንስሐ መግባት፡፡ በንስሐ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጣችን ይቀጣጠላል፡፡ በዚህም ምክንያት ስለእግዚአብሔር በጥልቀት ለማወቅ እጅግ እንጓጓለን፡፡ በዚህ ሰዓት ነው እንግዲህ የምናነባቸውን ምንባባትና የምንጸልያቸውን ጸሎታት መምረጥ ያለብን፡፡ ያለበለዚያ ፈጽሞ አርምሞን ገንዘባችን ማድረግ አይቻለንም፡፡ ስለዚህ ሌላውን የሚነቅፉና ለጠላት ጥፋትን የሚለምኑ ምንባባትንና ጸሎታትን ከማንበብ መከልከል ተገቢ ነው፡፡

Tuesday, August 21, 2012

ጌታችን ሆይ ስማን!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/12/2004
ሞት ሞትን ስቦ እልቂትን እንዳያመጣብን አምላክ ሆይ ጠብቀን፡፡ ሥጋ ወዳዶች ለአንድ አጥንት እርሱም ሥጋ ላልተረፈው እርስ በእርሳቸው ተባልተው ይህን ምስኪን ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዳያባሉ ከላይ ከአርዓያም ያለህ አምላክ ሆይ ተቤዠን፡፡ ደምን ለተጠሙ ሞት የልብ ልብ ሰጥቶአቸው ሰይፋቸውን በልባችን ውስጥ እንዳይስጉ፣ የዘለዓለም ቤተመቅደስህ ላደረግኸው ለዚህ ሰውነትህ እና ለእናትህ ልጆች ጌታ ሆይ እራራልን፡፡ ሕዝቡን ከእልቂት ጠብቅ፤ ከውጭ እኛን ሊውጡ ከሚያገሡ ከውስጥ አጥንቶቻችንን ሊቆረጣጥሙ ካሴሩ ጌታ ሆይ ታደገን፡፡
 ለያዕቆብ በሴኬማውያን ፊት ሞገስና ፍርሃት እንደሆንከው ጌታ ሆይ ለእኛም እንዲሁ ሁነልን፡፡ እኛንና የዚህችን ሀገር ሕዝብ ከጥፋት አድን፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስማማ መሪን ስጠን፡፡ ጌታ ሆይ! ኃይላችን አንተ ነህና አንተን አርዓያ አድርገን እኛ በዚህች ምድር መጻተኞች የሆንና ሀገራችን በሰማይ ያደረግን እንደሆነ ተረድተው፣ ሞት ድል የሚነሣት የዚህች ዓለም ሰዎች በእኛ ላይ እንዳይከፉ ፈቃድህንና ፈቃዳችንን አስታውቃቸው፡፡ በላይ በአርያም ያለህ ፈጣሪያችን ሆይ! አሁን ንቃ መንጎችህንም ጠብቅ! ጊዜው ሥጋ የተጣለበት ጊዜ ነውና ሥጋ ናፋቂዎች እርስ በእርሳቸው ተባልተው ሲያበቁ በመርዘኛ ጥርሳቸው ጤናማውን ሕዝብ ነክሰው እንዳያሳብዱትና እርስ በእርሱ እንዳያነካክሱት መጠጊያችን ሆይ! ስምህን ታዛችን አድርገናልና በአንተ እንመካ እንጂ አንፈር፡፡ ክብር ላንተ ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን!!!   

Tuesday, July 3, 2012

ጸሎት ዘአረጋዊ ዮሐንስ



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/10/2004 
ከእኔ የተሰወርክና የተሸሸግህ ጌታዬ ሆይ! አንተነትህን ግለጥልኝ ፡፡ ከእኔ ውስጥ ያለውን ያንተን ውበት አሳየኝ ፡፡ ሰውነቴ ለአንተ ማደሪያ ቤተ መቅደስ ይሆን ዘንድ የሠራኸው ጌታዬ ሆይ! (፩ቆሮ.፫፥፲፮-፲፯፤፪ቆሮ.፮፥፲፮)የክብርህ ደመና ቤተ መቅደስህ የሆነውን ሰውነቴን ይክደነው፤ የመሠዊያህም አገልጋይ የሆነችው ነፍሴ በፍቅር በመሆን አንተን ቅዱስ እያሉ በአድንቆትና በአግርሞት፣ በፍጹም ትጋትና ቅድስና እንደሚያገለግሉህ ሕያዋንና መንፈሳውያን ኃይላት ታመሰግንህ ዘንድ እርዳት፡፡…
የይቅርታ ውቅያኖስ የሆንክ ክርስቶስ ሆይ! ካንተ የሆነውን ብርሃናዊ ልብስ ተጎናጽፌ እንዳንጸባርቅ ባንተ ውኃነት በኃጢአት ያደፈውን ሰውነቴን እንዳጥብ ፍቀድልኝ፡፡ ሕቡዕ በሆኑ ምሥጢራት የተሞላው የክብርህ ደመና(መንፈስ ቅዱስ) እኔን ይከድነኝ ዘንድ (በእኔ ያድር ዘንድ) በዐይኔ ከማላያቸው ጀምሬ ወደ አንተ ውበት የሚወስዱኝን የጽድቅ ጎዳናዎች አስተውል ዘንድና ባንተ ግርማ ተማርኬ ያለማቋረጥ ክብርህን አደንቅ ዘንድ እንዲሁም በዓለም ጉዳይ ዐይኖቼ ከመባከን ያርፉ ዘንድ ምንም ቢሆን ምን ከአንተ ፍቅር የሚለየኝ እንዳይኖር ከዚህ ይልቅ አንተን በመናፈቅ እንድኖር ያለማቋረጥ ፊትህን እመለከት ዘንድ የልቡናዬን ዐይኖች ግለጥልኝ የልቡናዬንም እርሻ  አለስልሰው ፡፡” 

Friday, April 27, 2012

አትንቀፍ እንዳትነቀፍ አትፍረድ እንዳ…”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/08/2004
ቅዱስ ይስሐቅ ሰው በክፉም ይሁን በደግ ዐይኖቹ መታወራቸው አይቀርም ይለናል፡፡ በኃጢአት ውስጥ ያለ ሰው ዐይኖች ጽድቅን ማየት ይሳናቸዋል፡፡እንደነዚህ ዐይነት ወገኖች የሰዎች ኃጢአት እንጂ የጽድቅ ሥራቸው ወይም መልካም የሆነው ተፈጥሮአቸው አይታያቸውም፡፡ ነገር ግን የጻድቅ ሰው ዐይኖች የሰዎችን ድክመትም ሆነ ነውር ወይም ኃጢአት አይመለከቱም፡፡ሁሉም በእነርሱ ዘንድ ብሩካን ናቸው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ኃጥእ ጽድቅን አያቃትም ማለት ሳይሆን ወደ ኃጢአት ፈቃድ ያደላል ሲለን ነው፡፡ እንዲሁ ጻድቅ ሰውም የሰዎች ጉድለትና ድክመት ወይም ኃጢአት ሳይሆን አስቀድሞ የሚታየው የእነርሱ መልካምነት ነው፡፡
ጻድቅ ሰው የሰውን ደካማ ጎን ሳይሆን ጠንካራውን ይመለከታል፤ ስለዚህም በዐይኑ ውስጥ የገባውን ጉድፍ ለማውጣት በወንድሙ ዘንድ የታመነ ነው፡፡ በጽድቅም ምክንያት ዐይኖቹ ብሩሃን ናቸውና በወንድሙ ዐይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ዐይኑን ሳይጎዳው ጉድፉን ብቻ ለይቶ ያወጣለታል፡፡ ወንድሙም ከሕመምና ከስቃይ ጤናማ ስለሚሆን እርሱም እንደ ጻድቅ ወንድሙ አጥርቶ ማየት ይጀምራል፡፡ እንዲህ ነው መልካም ወዳጅ፡፡ ጻድቅ ሰው እንዲህ ነው፡፡ አይነቅፍም፤ አይቆጣም የወንድሙን ነውር ወይም ድክመት በአደባባይ አያወራም፤ በወንድሙ ላይ አይታበይም፤ ወንድሙ ከእርሱ እንደሚሻል ይቆጥራል፤ ስለወንድሙ መዳን በአምላክ ፊት ያነባል፤ ወንድሙን ከስህተት መንገድ ለመመለስ  ነገሮችን ሁሉ በጥንቃቄ ይከውናል፡፡

Tuesday, April 10, 2012

የንስሐ ጸሎት (በቅዱስ ኤፍሬም)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/08/2004
ጌታዬ ሆይ! ይቅር በለኝ፤ ወደ አንተ በንስሐ እመለስ ዘንድም ብርታትን ስጠኝ፡፡ እንደ ቅዱስ ፈቃድህ በቅድስና እመላለስ ዘንድ ወደ አንተ መልሰኝ፡፡ የአጋንንት መኖሪያና ጎሬ የሆነውን ልቡናዬን እባክህ ቀድሰው፡፡
ጌታዬ ሆይ! እኔ ከአንተ ዘንድ ለራሴ ይቅርታን እጠይቅ ዘንድ የማይገባኝ ጎስቋላ ሰው ነኝ፡፡ በተደጋጋሚ ንስሐ ለመግባት ቃል እገባና ለራሴ የገባሁትን ቃል መጠበቅ ተስኖኝ ዋሾ ሆኜ እገኛለሁ፡፡ አንተ ከወደቅሁበት የኃጢአት አዘቅት በተደጋጋሚ ብታወጣኝም እኔ ግን በገዛ ፈቃዴ በደጋጋሚ በኃጢአት ተሰነካክዬ እወድቃለሁ፡፡ ስለዚህም ጌታዬ ሆይ! በራሴ ላይ እፈርዳለሁ፤ በመተላለፌ ከአንተ ዘንድ የሚመጣብኝን ቅጣት ሁሉ በጸጋ እቀበላለሁ፡፡ አምላኬ ሆይ! ስንቴ ጨለማ የወረሰውን ልቡናዬን በጸጋህ ብርሃንህ አበራኸው? እኔ ግን ተመልሼ ወደ ተናቀውና ከንቱ ወደሆነው አስተሳሰብ ተመለስሁ፡፡ ይህን ባሰብኩ ቁጥር ሰውነቴ በፍርሃት ይርዳል፡፡ ነገር ግን የኃጢአት ፈቃዴ አይሎ በኃጢአት አዘቅት ውስጥ በተደጋጋሚ እወድቃለሁ፡፡

Wednesday, March 7, 2012

ጌታችን ሆይ!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/06/2004
ጌታችን ሆይ! ዛሬ ወደ ኋላ ተመልሼ የአዳምና የሔዋን ቅድስናና ንጽሕና ምን ይመስል እንደነበረ ለማስተዋል ሞከርኩ፡፡ ጌታ ሆይ! የኃጢአታችንን ታላቅነት እኛ በአንተ ላይ ባደረስነው መከራ ስንመለከተው፣ የጥንት ቅድስናችንንና ንጽሕናችንን በአንተ ሰው መሆን ውስጥ ተመለከትነው፡፡ አዎ ጌታችን ሆይ! በአንተ የቀደመው የቅድስና ሕይወታችን ምን ያህል ማራኪ እንደነበረ አስተዋልነው፡፡ አንተ በልብህ ትሑትና የዋህ እንደሆንክ ነገር ግን የዋህነትህ ከእውቀት ጉድለት እንዳልሆነ እንዲሁ ከውድቀት በፊት የአዳም አባታችንና የሔዋን እናታችን ትሕትናና የዋህነት በእውቀት የተሞላ ነበር፡፡
አንተ ፍጥረትህን ነፍስህን እስከ መስጠት ደርሰህ እንድትወድ እንዲሁ አዳምና ሔዋንም ራሳቸውን እስከመስጠት ድረስ ደርሰው አንተንና ከሥራቸው ያስገዛህላቸውን ፍጥረታት ይወዱ እንደ ነበር አሳየኸን፡፡ ጌታ ሆይ! አዳምና ሔዋን እርስ እርሳቸውም ያላቸው ፍቅር በአንተና በአባትህ መካከል እንዳለው ዓይነት ፍቅር ይመስል ነበር፡፡ ቅድስናቸውም አንተ “የሰማዩ አባቴ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብለህ እንዳስተማረከን ዓይነት ሥላሴን አብነት ያደረገ ቅድስና ነበር፡፡ ይህ እንደ ሕፃን ቅዱስና ንጹሕ የሆነ የአዳምና የሔዋን ተፈጥሮ በአንተ ዘንድ እጅግ ተፈቃሪ ነበር፡፡ ስለዚህም አባታችን ያዕቆብ ከልጆቹ ይልቅ የክርስቶስ ኢየሱስ አርአያ ያለውን ዮሴፍን እንዲወደው፣ አንተም ጌታ ሆይ! እኛን የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ ይልቅ የአንተ አርአያ ይታይብናልና ትወደን ነበር፡፡

Monday, March 5, 2012

ተወዳጆች ሆይ እናንተ……ናችሁ!!(በአፍርሃት ሶርያዊ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/06/2004
"ተወዳጆችና የሰላም ልጆች እንዲሁም የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሆይ! እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ እናንተ የምድር ጨውና የሰውነት(የዓለም) ዓይኖች ናችሁ፡፡ እናንተ የሙሽራውና የመልካሙ ዘር እንዲሁም የሕይወት ውኃ ለሚፈልቅበትና የማዕዘን ራስ ለሆነው ሕያው ዓለት ክርስቶስ ሚዜዎች ናችሁ፤ እናንተ አጥልቃችሁ በመቆፈር ቤታችሁን በዓለት ላይ የምትሠሩ ብልህ አናጺዎች ናቸሁ፡፡
እናንተ የብዙ ብዙ የሆነ እህልን በጎተራችሁ የምታከማቹ ታታሪ የጽድቅ ገበሬዎች ናችሁ፡፡ እናንተ የተሰጣችሁን ጥሪት ብዙ እጥፍ አትርፋችሁ የተገኛችሁ ትጉሃን ነጋዴዎች ናቸሁ፡፡ እናንተ ዋጋችሁን ተቀብላችው ሌላ ይጨመርላችሁ ዘንድ ያልጠየቃችሁ ቅን ሠራተኞች ናችሁ፡፡


Saturday, February 18, 2012

ጸሎት ዘቅዱስ ኤፍሬም (በዐቢይ ጾም የሚጸለይ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/06/2004
“የሕይወቴ ገዢ የሆንክ ጌታዬ ሆይ! ከስልቹነትና ከተስፋ መቁረጥ መንፈስ እንዲሁም ከንቱ ከሆነ ልፍለፋ ጠብቀኝ፡፡ ከዚህ ይልቅ  መንፈሳዊ ሙላትን ፣ ትሕትናን ፣ ትእግሥትን ፣ ፍቅርን አድለኝ፡፡ ንጉሤና አምላኬ ሆይ በወንድሜ ላይ በከንቱ ከመፍረድ ተከልክዬ የራሴን ኃጢአት ብቻ የማስተውልበትን ጸጋህን አድለኝ፡፡ ለአንተ ክብር ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን !!  

Sunday, February 5, 2012

ከጾም የሚቀድመው ጉዳይ (በቅዱስ ኤፍሬም)


አንተ ሰው የበደለህን ይቅር ሳትል ወደ ጾም አትግባ፡፡ አንተን በበደለህ ሰው ላይ በቁጣ እያለህ የምትጾመው ጾም ከንቱ ነው፤ እግዚአብሔርም አይቀበለውም፡፡ ጾምህን በፍቅርና እርሱን ተስፋ በማድረግ በእምነት ካላደረግኸው አንተን ፈጽሞ ሊረዳህ አይችልም፡፡ በጠብ ሆኖና በውስጡ ጠላትነትን አንግሦ የሚጾም ጸዋሚ እግዚአብሔርን ይጠላዋል፤ ከመዳንም ፈጽሞ የራቀ ነው፡፡ (ቅዱስ ኤፍሬም)