Saturday, November 1, 2014

ተወዳጆች ሆይ



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/02/2007

ወገኖቼ ሆይ አንድ የልብ ምክር አለኝና አድምጡኝ፡፡ ወዳጄ የቤተሰብ ሓላፊ ከሆንህ - እኔ ለቤተሰቤ እንደ ኢዮብ ካህን ነኝ ስለዚህ በመንፈስ ሁል ጊዜ፤ በአካል ደግሞ እንደ ችሎታዬ መጠን ስለራሴ ምክንያቱም በመልካም ማስተዋል ቤተሰቤን እመራ ዘንድ ስለቤተሰቤ ምክንያቱም ቤተሰቤ በኃጢአት ምክንያት አእምሮው እንዳይቆሽሽ በራስ መተማመን እንዳያጣ በማስተዋልና እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲመላለሱ ስለሀገሬ ሰዎች ደግሞ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ ማስተዋልንና እርስ በእርስ መግባባትን እንዲሰጣቸው ፍቅር እንድትነግሥ ስለዓለሙ ሁሉ ደግሞፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁንእንድንል ጌታ እንዳስተማረን የምንኖርባት ዓለም ፈቃዱን ለማድረግ እንደሚተጉ መላእክት ለመልካም ሥራ እንዲበረቱ በጸሎት መትጋት አለብኝ ብለህ ለልብህ ንገረው፡፡

ለቤተሰባቸው እማወራ ለሆኑ እናቶችና ሚስቶች ደግሞ ለልባቸው እንዲህ ብለው ይንገሩ፡- እኔ ለቤተሰቤ አካሉ ነኝ፡፡ በእርግጥም ባለቤቴ ራሴ ነው እኔም አካሉ ነኝ ልጆቼም ከእኔ የወጡ የአካሌ ክፋዮች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ሳራንካንቺ ሕዝብና አሕዛብ ይወጣሉእንደተባለች ከእኔ ማኅበረሱ ተገኝቶአል ይገኛልም፡፡ እኔ ለማኅበረሰቡ እንደ ሀገር ለሚቆጠረው ሕዝብና ለዓለሙ ሁሉ እንደመሠረት ነኝ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስቡሆው ቅዱስ ከሆነ ሊጡም ቅዱስ ይሆናልእንዲል የእኔ ቅድስና ለእነርሱ ቅድስና መሠረት ነው፡፡ ይህን ሁሌም ላስበው ይገባል ትበል፡፡ ሁሌም ይህን አስቤ እንደተምሳሌቴ እንደ ቤተ ክርስቲያን ማስተዋልን ያድለኝ ዘንድ ስለሀገሬ ስለ ዓለሙ ሁሉ ሰላም በመንፈስ ሁልጊዜ ፤ በአካል እንደ ችሎታዬ መጠን በጸሎትና ራሴን በማስተዋል ለማነጽ ልተጋ ይገባኛል ትበል፡፡
ልጅም እንደ ክርስቶስ በመንፈስም በአካልም በጥበብም በእግዚአብሔርም በሰው ፊት ሊያድግ እንዲገባው ዘወትር ያስብ የእርሱ ወጣትነት ዘመን ክርስቶስ ዓለምን ለማስተማር በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተመላለሰበት ዘመን እንደሆነ ያስብ፡፡ ስለዚህም ሰውነቱንበኃጢአት ሳይተደደፍ ወጣትነቱን በንጽሕና ይጠብቃት ዘንድ ክርስቶስን ማወቅ ከቅዱሳን ጋር ማኅበርተኛ መሆንን ሊለማመድ እንደሚገባው ቆጥሮ በጸሎትም በምንባብም በተመስጦም ሊተጋ እንዲገባው ለልቡ ይንገረው፡፡ ሁሉ ነገር ከራስ ሲጀመር እጅግ መልካም ነው፡፡ የቅድስና መንገዱም ይህ ነው፡፡ ጌታስ ቢሆን ያስተማረው ይሄንኑ አይደለምን? አንተ ግብዝ አስቀድመህ በዓይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ በኋላ የወንድምህን ጉድፍ ማየት ይቻልሃልብሎ አላስተማረንምን? ወገኖቼ በጸሎት አንዳችን ለአንዳችን እንትጋ፡፡

2 comments: