Monday, March 16, 2015

መዝሙር 89 በቅዱስ ጀሮም

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
06/07/2007

በመዝሙሩ መግቢያ ላይ የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት የሚል ተጽፎ እናገኛለን፡፡  .....
“አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆነህልን” ብሎ መዝሙረኛው መዝሙሩን ይጀመራል፡፡ መጠጊያ የሚፈልግ ሰው ከሚግለበለብ እሳት ወይም ወላፈን ወይም ከክፉ አውሬ ወይም ነፍሱን ከሚፈላለጋት ጠላቱ ከሚታደገው ዘንድ ነው መጠጊያውን የሚያደርገው፡፡ እኛም እንዲሁ ከዚህ ዓለም የኃጢአት እሳትና ወላፈን ወይም ደግሞ እኛን ከሚያድነን  አውሬ ዲያብሎስ  ያደነን ዘንድ “የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ”(መዝ.73፡19) እያልን ወደ መጠጊያችን እግዚአብሔር  ዘወትር እናንጋጥጣለን፡፡ ጠላቶቻችን በእኛ ላይ በርትተውብናልና በክንፎችህ ጥላ ሰውረን ብለን እንማጸነዋለን ምክንያቱም እርሱ መጠጊያችን ነውና፡፡
አስከትሎ፥- “ለትውልድ ሁሉ” አለ። ላለፉትም ላለነውም ለወደፊቱም  ሲለን ነው፡፡ ወይም ደግሞ “በብሉይ ኪዳን ሕግ ይመላለሱ ከነበሩት ዕብራዊያን አንስቶ እስከ ክርስቲያኑ ማኅበረስብ ድረስ አንተ መጠጊያችን ነህ ሲለን ነው፡፡ 
አስከትሎም “ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ” አለን፡፡ ይህቺ ቃል ከሃዲያን የሆኑት መንፈስ ቅዱስ ካጻፈው ውስጥ እንደ ሰበዝ መዝዘው የራሳቸውን ክፉ ትምህርት ያወጁባት ቃል ናት፡፡ እንዲህ ይላሉ “እግዚአብሔር አምላክ ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ በፊት ለእኛ መጠጊያ ከሆነ"በማለት የቃሉን መልእክት በማዛባት ዓለም ሳይፈጠር በፊት ነፍሳት ነበሩ ይሉናል። ቃሉንም እንዲህ አድርገው ያጣምሙታል፡-“አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን ተራሮች ሳይወልዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ" ይላልና ይህም ከትውልድ በፊትም ነፍሳት ነበሩ ማለት ነው ብለው ይተረጉሙታል። እንዲህም ሊሉ ሲሹም ነው ሙሉውን የቃሉን ሃሳብ ሳይሆን ለራሳቸው የሚመቻቸውን መዘው መጠቀም መፈለጋቸው፡፡ እንዴት አድርገው ቃላትን በመገጣጠም የእነርሱን የልብ መሻት አቀናብረው እንደሚያዘጋጁት ልብ ብላችሁ  ተመልከቱ “ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ" ብለው ዓረፍተ ነገሩን ሳይጨርሱ ከላይ ከተነገረው ቃልን ቆርጠው በማምጣት " አንተ መጠጊያችን ነህ” በማለት ለራሳቸው የሚመቸውን ዓረፍተ ነገር ጻፉልን፡፡  ከዚህም ተነስተው እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በፊት መጠጊያችን ከሆነ ዓለማት ሳይፈጠሩ በፊት ነፍሳት ነበሩ ማለት ነው ይሉናል፡፡ 
እናንት ከሃዲያን ሆይ እንዴት የመጽሐፍ ቅዱስና ቃል ለገዛ ጥፋታችሁ መዛችሁ ደካማ የሆነ ምክንያትን እንዳቀረባቸው ትመለከታላችሁን? ስለምንም እንዲህ በማድረግ መንፈስ ቅዱስን ታሳዝኑታላችሁ ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በትክክል አሟልታችሁ መንፈስ ቅዱስ ሊል እንደፈለገው ስለምን መናገርን አልመረጣችሁም? ቃሉ ሊነበብ የሚገባው እንዲህ ነው፡- “አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን፡፡ ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ ከዘለዓለም አስከ ዘለዓለም ድረስ አንተ ነህ፡፡” (መዝ.89፡1-2) 
ከምንባቡ እንደምንረዳው “አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን" ብሎ በአራት ነጥብ ይዘጋና ሌላ ዐረፍተ ነገር ይጀምራል፡፡ አስከትሎም  “ተራሮች ሳይወለዱ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ድረስ አንተ ነህ” በማለት  በአራት ነጥብ ሃሳቡን ይቋጫል፡፡ ስለዚህ ቃሉ ከሃዲያኖቹ እንደሚያስቡት ሳይሆን እግዚአብሔር ከፍጥረት በፊት ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ያለና የሚኖር አምላክ መሆኑን የሚያስረዳ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 
“ሰውን ወደ ኀሳር አትመልሰም የሰው ልጆች ሆይ ተመለሱ ትላለህ “ይላል አስከትሎ  “ከዳተኞች ልጆች ሆይ ተመለሱ ከዳተኝነታችሁንም እፈውሰዋለሁ” ሲል ነው(ኤር.3፡22)
"ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን እንደ ሌሊትም ትጋት ናትና፡፡ በማለት ወደ ኀሳር አትመለሱ  እያልህ ታሳስባቸዋልህ፡፡ ለመሆኑ ስለምንድን ነው “እንደሌሊት ትጋት” ማለቱ? ሌሊት በአራት ትጋቶች(ክፍሎች) ይከፈላል፡፡ ይህን አስመልክቶ ወንጌላዊው “በሌሊቱም በአራተኛው ክፍል” (ማቴ.14፡25) ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ ይህም ዐሥራ ሁለቱ ሰዓታት በሦስት በሦስት ተከፋፍለው ሦስቱ እንደ አንድ ሰዓት መቆጠራቸውን እናስተውላለን፡፡ ወታደሮችም ሌሊቱን በአራት ሰዓታት ከፋፍለው ነው ለጥበቃ የሚቆሙት።
ይቀጥላል….

No comments:

Post a Comment