Showing posts with label ኪን መንፈሳዊ. Show all posts
Showing posts with label ኪን መንፈሳዊ. Show all posts

Thursday, January 24, 2019

የመጥምቁ ዮሐንስ ቃል(ክፍል አንድ)



በመ/ር ሽመልስ  መርጊያ 

ቀን 17/05/2011 ዓ.ም

ጌታዬ ሆይ በኣቴ በሆነች በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ ሥራዬ አንተንና አንተን ማሰብ ብቻ ነበርና ወደ እኔ የምትመጣበትን ቀን በጉጉት እጠባበቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገና ስጸነስ ጀምሮ የአንተ ባሪያና መንገድ ጠራጊ እንድሆን አድርገህ ስለፈጠርኸኝ አንድ ቀን ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዳለህ አውቅ ነበርና፡፡ እናም ገና የስድስት ወር ጽንስ ሳለሁ አንተ የእለት ጽንስ ሆነህ በእንግድነት ከእናትህ ጋር ወደ እኔ ስትመጣ ስጠብቀው የነበረ ተፈጽሞአልና ሊነገር በማይችል ደስታ ውስጥ ሆኜ ተቀበልኩህ፡፡ ጌታ ሆይ በቅድስት እናትህ የሰላምታ ድምጽ እንዳንተ በማሕፀን ላለሁት ለእኔ ሰላምህን ሰጥተኸኛልና አንተን በማወቄ ዕውቀቴ ገና ከማሕፀን ሳልወጣ ፍጹም ሆነ፡፡ ምክንያቱም አንተ የዕውቀት ፍጻሜ ነህና፡፡ ስለዚህ ከአንተ ከአባትህ ከእግዚአብሔር አብ ከባሕርይ ሕይወትህ ከመንፈስ ቅዱስ ሌላ ሌላ መምህር አላስፈለገኝም፡፡

Monday, May 29, 2017

የነፍስ ወግ ካለፈው የቀጠለ….


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/09/2009



እናንተዬ እኔ ረቂቋ ነፍስ ይህን ሁሉ ሳስብ ሐዲስ ኪዳንን ዘንግቼ ብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለሁ መሰለኝ፡፡ ለመሆኑ በክርስቶስ ያለኝ ተስፋ ወዴት ሄደ? በርሱስ ያገኘሁት ሕይወት የት ደረሰ?? ክርስቶስን ሳስብ ሚስቴ የሆነችው የሥጋዬ በደል ፈጽሞ ይጠፋል ቀንበሯም ቀሊል ይሆንልኛል፡፡ እንደውም እርሷ ባትኖር ኖሮ እኔ ነፍስ እድን ነበርን? ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ እረ በፍጹም ሥጋዬ ባትኖር ኖሮ ከአምላክ የመለየትን ትርጉም በምን እረዳው ነበር? ለንስሐስ እንዴት እተጋ ነበረ? እንዴትስ አምላኬን አየው ነበረ? እኔ ብቻ ሳልሆን መላአክትስ ቢሆን ከነርሱ በእጅጉ የሚረቀውን አምላክ ለመመልከት የበቁት በማን  ሆነና?

Sunday, December 30, 2012

“ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/04/2005
ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፌ ነው፡፡
በዛሬው ቀን ዓለም ለመዳን የቅድስት ድንግል ማርያምን ይሁንታን የፈለገበት ቀን ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከምንም በላይ የሰውን ነጻ ፈቃድ ስለሚያከብር መልአኩን ቅዱስ ገብርኤልን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲልከው ፈቃዱዋን ይጠይቃት ዘንድ ነበር፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት መሰላችሁ “እነሆ በደጅህ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል”(ራእ.3፡20) እንዳለው ዓይነት ነው፡፡ ነገር ግን በይዘቱ የቅድስት እናታችን  ይሁንታ በጣም የተለየ ነው፡፡ ስለዚህም የዓለም መዳን በእርሱዋ ይሁንታ ላይ ነውና እግዚአብሔር በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በኩል የቅድስት ድንግል ማርያምን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ ለእርሱዋም በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አንደበት እግዚአብሔር ቃል ለሰው ልጆች መዳን ከእርሱዋ ተፀንሶ ለመወለድ ፈቃዱ እንደሆነ፣ እርሱዋንም የዘለዓለም እናቱና የሰው ልጆችን ፍጹም የመውደዱ ምልክት ሊያደርጋት እንደወደደ አበሰራት፡፡ ቅድስት እናታችንም ፍጹም ትወደውና ታመልከው የነበረው እግዚአብሔር ከእርሱዋ ተወልዶ ዓለምን ለማዳን መፍቀዱን ስትሰማ በፍጹም ደስታ ተሞልታ ግሩም በሆነ ትሕትና “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” “እንደቃልህ ይደረግልኝ” በማለት ዓለምን እፎይ አሰኘቻት፡፡ እስከዛች ጊዜ ድረስ ዓለም በጭንቀት ተውጣ የእርሱዋን መልስ በጉጉት ትጠባበቅ ነበር፡፡

Monday, September 17, 2012

ቅርብኝ ቅርብኝ


ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
07/01/2005

እናንተዬ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፈልጋት እንደው አሻጉሊት የሚሆን ራስ ነው እንዴ? ይህ እኔን እጅግ ያንገሸገሸኝ እኔን ብቻ ሳይሆን መላው ምእመናንን ያስመረረ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን እኛ የምንፈልገው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና የሰው ኃይል በአግባቡ ተጠቅሞ በመንፈሳዊውም በኢኮኖሚያዊም መስክ ክርስቲያኑን ማኅበረሰብ የሚያበቃ በሳል ሊቀጳጳስ ነው ነገር ግን አሁንም እንደቀድሞው አሻጉሊት የሆነ ራስ ራስ ሊሆን ከመጣ ራስነቱ ለራሱ ይሁን እኔ ግን ቅርብኝ ብያለሁ፡፡ በቃኝ

ቅርብኝ ቅርብኝ
ራስ እኔነቴን ካዋረደ፤
እፍረትን በእኔ ላይ ካንጓደደ፤
እኔስ እንዴት ላክብረው ራሴን?
ቁልቁል ከጣለው ማንነቴን?
እረ ወዲያ በቃኝ ራስነቱ ይቅርብኝ፤
ጡረተኛን ጣሪ አካል ካደረገኝ፤
ካልጠቀመኝ ራስነቱ፤
ካልረባን አክሊልነቱ፤
እረ ወዲያ ይቅርብኝ፤
ራሱ ገምቶ አካሌን አያግማው፤
ራሱ ያመጣውን ራሱ ይወጣው፤
በሕሊናዬም አይታሰብ ስም አጠራሩም አይታወስ፤
ሰላሜን አይንሳ ብስጭቴን አይቀስቅስ፡፡
ግና እግዚአብሔር በእርሱ ከነገሠ ፤
ነፍሱን ለጌታው ፈቃድ ካፈሰሰ፤
ይምጣ ይግባ ራስም ይሁነኝ፤
በርቶ ያድምቀኝ ሞቆ ያሙቀኝ፤
ሕያው ሆኖ ያኑረኝ ብርሃንን ያልብሰኝ፤
ያለበለዚያ ወዲያ ወዲያ ክላልኝ አትምጣብኝ፡፡
ጫንቃዬ ሰልችቶአል ጡረተኛን ማዘል፤
እሹሩሩ ማለት ጡጦ እየሰጡ ማባበል፡፡

Thursday, April 19, 2012

እናት



በወንድም ሸዋዓለም ፈቃዱ
12/08/2004

መነሻ ዳርቻ ፍጻሜ የሌለው፤
ጥንቱን የማላውቀው ፍጹም የማለየው፤
አለ አንዳች ስበት ከስሜት የጸዳ፤
ከእናት ያጣበቀ ከእናት የተቀዳ፡፡
እማዬ ፡- ያኔ… ያ…ኔ ክፉውን ከደጉ ያለየሁኝ ለታ፤
በቅጽበት ዐይን ያልተለየኝ ላፍታ፤
ከጡቶችሽ ምጌ ከልቤ ያኖርኩት፤
አንዳች ምሥጢር አለ እኔ ያልገለጽኩት፡፡
ካንቺ የሰረፀ ያ  ኃያሉ ፍቅርሽ ፤
ከየት ቋንቋ ላምጣ እንደምን ልግለጽሽ፡፡
እማ… እማዬ… እኔ ብቻ ሳልሆን እኔን የሚመስሉ፤
ሰው ሁነው ተፈጥረው በዓለም ዙሪያ ያሉ ፤
ስለእናት አዚመው ስለእናት ቢቀኙ፤
ዓለምን ቢዞሩ ገላጭ ቃል ቢያገኙ፤
አልሆነላቸውም ምንም ቢባዝኑ ፤
ምንም ቢፈትሹ የትም ቢኳትኑ፡፡
ስለዚህም መግለጫ ቃል ቢያጡ፤
በአንደነት በጋራ ዓለሜ ናት ብለው ለአንቺ ስም አወጡ፡፡
እኔስ የእኔ እናት፣ ውዴ የእኔ ሕይወት፣ ስላንቺ ምንም አልልም፤
ከቶም አልጽፍልሽም፤ ዝምታ እንጂ አንቺን ቃላት አይገልጽሽም፤
ስለአንቺ አላወራም አልዘምርልሽም፤
ፈጣሪ ሲፈጥርሽ አልፈጠረልሽም፤
በምድር የሚገኝ ገላጭ ቃል የለሽም፡፡

Wednesday, April 4, 2012

በመስቀሉ የተፈጸመው ጋብቻ (በቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ)



 ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/07/2004
ከእኛ ጌታ በቀር ለእጮኛው ራሱን አሳልፎ የሰጠ ሰው ማን ነው? ከቤተ ክርስቲያንስ በቀር የሞተ ሰው ለእርሱዋ ባልዋ ይሆን ዘንድ የምትሻ ሴትስ ማን ናት? ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ደሙን የጥሎሽ ስጦታ አድርጎ ያቀረበ ሰው ማን ነው? በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ  ከአንድዬ በቀር ጋብቻውን በሕማሙ ያተመ ሰው ማን ነው ? ከሞተ አካል መጽናናት ታገኝ ዘንድ በእቅፎቹዋ ይዛ በሰርግዋ በዓል ላይ የተገኘች ሙሽራ ከዚህ በፊት ታይታ አትታወቅም ? በየትኛውስ የሰርግ በዓል ላይ ነው ሙሽራውን ሥጋ በመቁረስ በሰርጉ ለታደሙት እንግዶች መብል ይሆን ዘንድ የተሰጠው?
ሚስት በባሏ ሞት ምክንያት ፍቺን ትፈጽማለች ፡፡ ይቺ ሚስት ግን በውድ ባሏ ሞት ምክንያት ከእርሱ ጋር ፍጹም ተዋሕዶን አደረገች፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ ራሱን በመሠዋት ቅዱስ የሆነውን ሥጋውን ሁሌም ትመገበው ዘንድ  ክብርት ለሆነችው ሙሽራው መብል አድርጎ አቀረበላት ፡፡ ጉኑንም በመወጋት ቅዱስ ደሙን በጽዋው ሞልቶ ሰጣት ፡፡ በዚህም ምክንያት በልቡዋ ያኖረቻቸው ጣዖታት ሁሉ ተወገዱላት ፡፡ በእርሱም ቅዱስ ቅባት ከበረች ፤ እርሱንም በጥምቀት ውኃ ለበሰችው ፤ በሕብስት መልክ ተመገበችው ፤ እንደ ወይንም ጠጣችው ፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱ በፍጹም ተዋሐዱ  አንድ እንደሆኑ ዓለም ሁሉ አወቀ ፡፡

Thursday, March 29, 2012

ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡-(በቅዱስ ኤፍሬም)




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/07/2004
“ቅድስት ድንግል ማርያም ስለልጁዋ ስለወዳጁዋ እንዲህ አለች፡-  እኔ የተሸከምኩት ሕፃን እርሱ እኔን የተሸከመኝ ነው ፡፡ እርሱ ክንፎቹን ዝቅ አድርጎ በእቅፎቹ ውስጥ አኖረኝ ፡፡ ከእርሱም ጋር ወደ ሰማየ ሰማያትም ተነጠቅኩ ፡፡ በዚያም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ ለልጄ እንዲሆን ቃል ኪዳን ተገባልኝ ፡፡
ልጄን መልአኩ ገብርኤል ጌታዬ ብሎ ሲጠራው ሰማሁ ፣ ሊቀ ካህኑና አገልጋዩም (ስምዖን አረጋዊ) እርሱን በእቅፉ ይዞ ስለእርሱ ትንቢትን ተናገረ ፡፡ ሰብአ ሰገል በፊቱ ወድቀው ሲሰግዱለት፤ ሄሮድስም ንግሥናዬን የሚቀማ ሌላ ንጉሥ ተነሣብኝ ብሎ ሲርድ ተመለከትኩ ፡፡
ሙሴን አገኘዋለሁ ብሎ የዕብራዊያንን ሕፃናት ያስፈጀ ሰይጣን እርሱን በመስቀሉ ጠርቆ የሚያስወግደውን ሕፃን ለመግደል ሽቶ ሄሮድስን መሳፈሪያው አድርጎ ሕፃናትን ለመግደል ተፋጠነ፡፡ ነገር ግን ጠላቶቹ የሆኑትን ሊያድናቸው የመጣው ጌታ ወደ ግብፅ ተሰደደ ፡፡
ቀዳማይቱ ሔዋን በድንግናዋ የእፍረት ልብስ ለበሰች፡፡ ያንተ እናት ግን በድንግልናዋ ለሁሉ የሚበቃውን የክብርን ልብስ ደረበች ፡፡ እርሱዋ ሁሉን የሚያለብሰውን ጌታ ውሱን የሆነውን ሥጋዋን አለበሰችው ፡፡

Saturday, March 17, 2012

"ከእባብም ክርስትናን እንማር፤ እንዴት?"

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
09/07/2004
ከአንድ የቅርብ ቅርብ ወዳጄ አንድ ታላቅ የሆነ ትምህርት ሰማሁ፡፡ ይህ ወዳጄ ነገር መሸፋፈን አይወድምና እንዲህ አለኝ “አንተዬ አንድ የአደባባይ ምስጢር ልንገርህ" ብሎ ይጀምርና በመቀጠል “ካበቁ ከበቃቁ ሰውነታቸውና አእምሮአቸው በኃጢአት ከድሃ ድሪቶ ይልቅ እጅግ ካደፈ በኋላ እንዲሁም ዓለሚቱን በኃጢአታቸው ከከደኗትና  ትውልዱን መንገድ አስተው የአጋንንት መጫወቻ ካደረጉ በኋላ ዓለም በቃኝ አሉ አሉ! እነ እማሆይ! እነ አባሆይ! ዋይ! ... ዋይ! .... ዋይ! ... እኒህ ጽድቅ በቆቤዎች ስለእኛ በመስቀል ላይ ስለተሠዋልን ስለአፍቃሪያችን ስለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳች ሳያስተምሩን እኛን ለሰይጣን  ዳርገውን ዓለም(ኃጢአት) በቃችኝ ብለው ቆብ አጠለቁ አሉ! ጉድ ነው! መቼም በኢትዮጵያችን ይህ የተለመደ የጽድቅ ማቋረጫ መንገድ ሆኗል ፤እድሜ ለምንኩስና!! መቼም ሰው ቆቡን ከየትም ያምጣው ከየት እርሱን አጥልቆ በአንዴው ጻድቅ ሆኖ ቁብ ይልብናል፡፡ እኽ ነው እንጂ ሌላ ምን ይባላል!! ግን ግን ልጆቻቸውን በሥርዐት ቀርጸው የሚያሳድጉና ለዓለም ብርሃን እንዲሆኑ የሚያበቁ እንዲሁም ክርስቶስ በእርሱዋ የሰው ልጅ መባልን ያላፈረባታን ቅድስት ድንግል ማርያምን በምግባራቸው የመሰሉ አንዳንድ ቅዱሳን ወላጆችም አይጠፉም፡፡

Wednesday, March 7, 2012

በዓለ እግዚእ በቅዱስ ኤፍሬም




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/06/2004 
ይህቺ ቀን ለቅዱሳን ነቢያት ነገሥታትና ካህናት የደስታቸው ቀን ናት፡፡ በዚህች ቀን በይሁዳ አውራጃ በቤተልሔም እንደ ተስፋ ቃሉ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ሊያድናቸው ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም አማኑኤል ተወለደ፡፡ እነሆ ድንግል አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች”(ኢሳ.7፡14)ብሎ የተነገረው የትንቢት ቃል እውን ሆነ፡፡ አሕዛብን ወደ እርሱ የሚያቀርባቸው በዚች ቀን ተወለደ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ስለእርሱ የተናገረው ትንቢት ዛሬ ተፈጸመ፡፡(መዝ.130፡1-7) ሚክያስ የተናገረው የትንቢት ቃልም እንዲሁ፡፡(ሚክ.5፡2) ጌታችን በኤፍራታ እረኛ የሆነው ክርስቶስ ተወለደ፡፡(ማቴ.2፡1-2) በበትሩም(በመስቀሉም) በእርሱ የታመኑትን ይጠብቃቸዋል፡፡ ከያዕቆብ ኮከብ ወጣ ከእስራኤልም ራስ የሆነው ተነሣ፡፡ በልዓም አስቀድሞ “አያለሁ አሁን ግን አይደለም እመለከታለሁ በቅርብ ግን አይደለም ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤልም በትር ይነሣል”ብሎ የተናገረው የትንቢት ቃል በዛሬዋ ቀን ተፈጸመ፡፡(ዘኁል.24፡17) በሕቡዕ የነበረው ብርሃን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታየ፡፡ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ብርሃን ዛሬ በቤተልሔም አበራ!(ዘካ.4፡1-3)

Thursday, March 1, 2012

ገነት በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/06/2004
በዚህ መዝሙር ቅዱስ ኤፍሬም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን ዓለት በማንሣት እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንዴት እንደፈጠራቸውና ስለገነት ያለውን አስተምህሮ እንመለከታለን፡፡

እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን አለትን አስታውሼ ዓለማትን የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልብ አልኩ፡፡ እንደ ታላቅ ወንዝ ለእነርሱ ከአለቱ ውስጥ የፈለቀው ውኃ በውስጡ ካለው የውኃ ቋት የተገኘ አልነበረም ፡፡ በአለቱ ውስጥ አንድም ጠብታ ውኃ የለም፤ ነገር ግን ልክ የእግዚአብሔር ቃል ፍጥረትን ከምንም እንዳስገኛቸው፤እንዲሁ ታላቅ የውኃ ጅረት ከደረቅ ድንጋይ ውስጥ ፈልቆ የተጠሙትን አረካቸው፡፡
ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ተፈጥሮ ገልጦ ጽፎልናል  ስለዚህም ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈጣሪ ምስክሮች ሆኑ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለራሱ ጥቅም ሲገለገልባት እንደሚያውቃት እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በውስጡ የያዘውን መረዳት ይቻለናል እነዚህን ሁለቱን ምስክሮች በሁሉ ስፍራ እናገኛቸዋለን፡፡





Wednesday, February 15, 2012

“እኔ በእርሱ እኔነት ውስጥ”



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
08/06/2004
ይገርማል!! እኔ እምላትን አካል የሥጋዬን ታኽል እንኳ ባለማወቄ ይደንቀኛል፡፡ እኛ  ቅዱስ ጳውሎስ “ዛሬስ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን” (1ቆሮ.13፡12) እንዳለው ያህል እንኳ ያላየናት እኔ የምንላት መንፈሳዊት ረቂቅ አካል  አለችን ፡፡ ነፍሴ ምን እንደምትመስል እንደማላቃት እንዲሁ እኔ የምላት አካሌን አለማወቄ እንዴት የሚያሳፍር ነገር ነው ጃል!! ነገር ግን እኔ ያመጣሁት ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ በድንቅ ቸርነቱ ከእኔ የሰወራት ናት፡፡ በዚህ ምድር በቅድስና ለመኖር ከተጋሁ በመንፈስ ቅዱስ መነጽርነት ልክ መላእክትን እንደማየት ላያትና ቅዱስ ጳውሎስ “በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን ዛሬ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁ”(1ቆሮ.13፡12) እንዳለው አያታለሁ!!
እኛ በቅድስና የተጋን እንደሆነ በዚህ ምድር ሳለን እንደ ቅዱስ ጳውሎስ እኔነታችንን በድንግዝግዝታ ልንመለከታት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ካልተጋን ልክ እንደባለ ጠጋው ነዌ በሲኦል ሳለን ማየታችን አይቀሬ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ እውቀቶች የተለያዩ እውቀቶች ናቸው፡፡ በቅድስና ተግተን በመኖራችን እኔነታችንን ማወቃችን ለእኛ ለክብር ሲሆን ላልተጉቱ ግን ለኩነኔ ነው፡፡ እነርሱ በዚያን ጊዜ የሚመለከቱት እኔ የሚሉዋት ረቅቅ አካላቸው ሰይጣንን መስላ ነው፡፡ እኛ ግን እኔነታችንን የምናገኛት ክብር ይግባውና ክርስቶስን መስላ ነው፡፡

Friday, February 10, 2012

ነፍስ ለሥጋ ያቀረበችው ምስጋና



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
02/06/2004 

ነፍስ እንዲህ ብላ ሥጋን አመሰገነቻት፡፡ ሥጋዬ ሆይ እኔ ብቻ ሳልሆን መላእክትም አንቺን እጅግ ያከብሩሻል ያፈቅሩሻል፡፡ ምክንያቱም ባንቺ ነውና እነርሱ እርሱን መመልከታቸው፡፡ አስቀድሞ ግን ምንም እንኳ እነርሱ ረቂቃን ቢሆኑ ረቂቅ የሆነውን  እግዚአብሔርን ለማየት  አልተቻላቸውም ነበር፡፡ ስለዚህም በሰው አምሳል ተገልጦ ይታያቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ከእናታችን የነሳውን ሰውነት ገንዘቡ አድርጎአልና እርሱን ለማየት በቁ፡፡ ስለዚህም ሥጋዬ ሆይ መላእክት አንቺን ያፈቅሩሻል ያመሰግኑሻል፡፡ እንደዲያማ ባይሆን እግዚአብሔርን እንዴት ሊያዩት ይችሉ ነበር? እኛም በእርሱ አባቱን ልንመለከት፣ መንፈስ ቅዱስም ሕይወታችን ሊሆን እንዴት ይችል ነበር? ሕመምተኞችስ እንዴት ወደ እርሱ ቀርበው የልብሱን ዘርፍ በመዳሰስ  ከሕመማቸው ይፈወሱ ነበር? እኛስ እንዴት የእርሱ የአካሉ ሕዋሳት ልንሆን እንችል ነበር? እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ባልተፈጸመልን ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ እሳት ልብሱም እሳት ነውና፡፡ እርሱ የማይጨበጥና የማይዳሰስ ረቂቅ እንዲሁም ማንም በማይደርስበት ብርሃን ውስጥ የሚኖር ነውና፡፡ ወደ እርሱስ መቅረብ የሚቻለው ማን ነበር? እርሱ  የሚባላ እሳት ነውና፡፡ 

Thursday, February 9, 2012

“አንዲት አጥንት”



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
01/06/2004
ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የተጻፈ 


 “ከአዳም የጎን አጥንት የተፈጠረችው ሴት ከራስ ቅሉ አጥንት አለመፈጠርዋ በእርሱ ላይ እንዳትሰለጥን ነው ከእግሩም አጥንት ከአንዱ አለመፈጠሯ እርሷን መበደልም ይሁን መጨቆን እንዳይገባው ለማስተማር ነው፡፡ ነገር ግን ከጎን አጥንቱ ፈጠራት በክብር እኩል መሆናቸውን ለማሳየት፡፡ ይህ የጎን አጥንት ከክርኑ አካባቢ መሆኑ ሚስቱን ከጥቃት ሁሉ ይጠብቃት ዘንድ የባል ሚና መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡ እንዲሁም ከልቡም አጠገብ መፈጠሩዋ እርሷን ከልቡ ሊያፈቅራት እንዲገባው ለማመልከት ነው፡፡”(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ)
ቅዱሳን እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ማዕከላዊ አድርጎ መፍጠሩ በዐይን የማይታዩትን መናፍስትንና የሚታዩ ፍጥረታትን ሁሉ እርሱ እንደፈጠረና ግዢያቸው እንደሆነ ምስክር እንዲሆነው ነው ይላሉ፡፡ ባጠቃላይ ሰው /Human beings/ የእግዚአብሔር የገዢነቱ ምልክት ነው፡፡
ስለዚህም አዳም በነፍስ ተፈጥሮው መልአካዊ ባሕርይ ሲኖርው በሥጋው ባሕርይው ደግሞ እንስሳዊ ባሕርይ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚህም መሠረት አዳም በሥጋው ባሕርይው ምክንያት ልክ እንደ እንስሳት ለመኖር መሠረታዊና አስፈላጊ ነገሮች የተባሉት ሁሉ ለእርሱ የተገቡ ሆኑ፡፡

Saturday, February 4, 2012

ለክርስቶስ የቀረበ የምስጋና ቅኔ(ከሶርያ ቅዱሳን አባቶች)

(ማኀልየ ማኅልይ ዘሶርያ)
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/05/2004

ከማር እንጀራ የማር ወለላ እንዲንጠባጠብ፤
ለልጅዋ ፍጹም ፍቅር ካላት እናት ጡት ወተቱ ሞልቶ አንዲፈስ፤
አምላኬ ሆይ ከአንተ ዘንድ የእኔ ናፍቆት ይህ ነው፡፡
የፏፏቴው ውኃ ድምፅ እያሰማ እንደሚወርድ፤
እንዲሁ ልቤ እንደ ፏፏቴ ለጌታዬ ምስጋናውን አፈሰሰ፤
ከንፈሮቼም ውዳሴህን አፈለቁ፡፡
አንደበቴም ከእርሱ ጋር በመነጋገሩ ጣፈጠ፤
ጉልበቶቼም ለእርሱ ባቀረብኩት ዝማሬ ጸኑ፤
ከእርሱ ባገኘሁት ታላቅ ደስታ ፊቴ  ፈካ፤
መንፈሴም እርሱ ለእኔ ባለው ፍቅር ሐሴትን አደረገ፤
በእርሱም ነፍሴ እንደ ፀሐይ ደምቃ አበራች፡፡
ጌታን የሚያከበርና የሚፈራ ሰው እርሱ ብርቱ ሰው ነው፤
መዳኑ የታወቀና የተረጋገጠ ነው፡፡
እርሱ ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያገኛል፤
በእርሱ አምኖ በምግባር ለመሰለው ሕይወትን ይሰጠዋል፤
ሃሌ ሉያ !!
አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር…..

Thursday, February 2, 2012

“ኑ ቤተክርስቲያንን ማርያም እንበላት”(ቅዱስ ኤፍሬም)

   


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ 
25/05/2004 


"ማርያም መግደላዊት ትንሣኤውን ትመለከት ዘንድ ጌታ ወደ እርሱ አቀረባት፡፡
ስለምን ግን ጌታ ትንሣኤውን እርሱዋ ቀድማ እንድትመለከት አደረጋት? ስለምን ወንዶቹ እንዲመለከቱ አልፈቀደላቸውም?
ምክንያቱም ቤተ-ክርስቲያንና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን የዝምድና ምስጢር ጌታችን ሊያሳየን በመፍቀዱ ነው፡፡
ጌታችን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ቅድስት ድንግል ማርያም እርሱን በመፅነስ ቀድማ ተቀበለችው፤
ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ደግሞ ትንሣኤውን መግደላዊት ማርያም አስቀድማ እንድትመለከት አደረጋት፤
በመጀመሪያውና በፍጻሜው(በልደቱና በትንሣኤው) ክቡር የሆነው የእናቱ ስም በዚያ እንደነበር ጮኾ ተናገረ፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን በመፅነስ በተቀበለችው ጊዜ መልአኩ ከፊቱዋ ነበር፤            
መግደላዊት ማርያምም እንዲሁ እርሱ ሕያው ሆኖ ባገኘችው ጊዜ መልአክ ከፊቱዋ ነበር፤ 
ስለዚህም ማርያም በቤተክርስቲያን ትመሠላለች፤
ድንግል ማርያም በወንጌል ቃል የሁሉ በኩር የሆነውን ልጇን በመውለዱዋ ደስ ተሰኘች፤
መግደላዊት ማርያምም በቤተክርስቲያን ቦታ ሆና ትንሣኤውን ተመልክታለችና ደስ ተሰኘች፤
ስለዚህም ቤተክርስቲያንና ቅድስት እናቱን ደስ ያሰኘው ሕፃን እርሱ በእውነት የተመሰገነ ይሁን”
ኑ ቤተክርስቲያንን “ማርያም” ብለን እንጥራት፤
ቤተክርስቲያንና ማርያም የሚሉት ስሞች በእውነት ለእርሱዋ የተገቡ ናቸውና፡፡
ለቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ከተባለው ከቅዱስ ስምዖን ጴጥሮስ ቀድማ ማርያም ከመቃብሩ ዘንድ ተገኘች፤
 ቤተክርስቲያንንም ወክላ ጌታ እንደተነሣ የምሥራቹን ዜና ለስምዖን አመጣችለት፤
 ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶአል ብላም ሰበከችለት፤
ማርያም ወደ ስምዖን ጴጥሮስ የትንሣኤውን ዜና ይዛ መምጣቱዋ አግባብነት ነበረው፤
ምክንያቱም እርሱ ለተመረጠችው ቤተ- ክርስቲያን አለትና መሠረት ነውና፡፡
… ኢሳይያስ “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች”ብሎ የተናገረለሽ አማናይቱ ቤተክርስቲያን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡
የልጅሽ ስም በራሱ ታላቅ የሆነ መልእክትን በውስጡ ይዞአል፤ ሁለት ስሞች በአንድ ላይ በመዋሐድ አማኑኤል የሚለውን ስም ሰጡ፤ ይህ ስም በቤተክርስቲያንና በክርስቶስ መካከል የሆነውን ተዋሕዶ የሚገለልጥ ስም ነው፤
እርሱ ካንቺ የነሣውን ሰብእና ገንዘቡ በማድረግ አንቺን ቤተክርስቲያን አሰኘሽ፡፡ እኛንም የአካሉ ክፍሎች በማድረግ ቤተክርቲያን አሰኘን፤ ስለዚህም "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው" የሚለው የስሙ ትርጉም ባንቺና በእኛ እውን ሆነ፤
ከቅድስት እናቱ በነሣው ሰውነት በኩል እኛን ከራሱ ጋር በማዋሐድ ቤተክርስቲያን ላሰኘን ለእርሱ ለክርስቶስ ክብር ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

Wednesday, February 1, 2012

ቤተክርስቲያን (በቅዱስ ቶማስ)

ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/05/2004
ቤተክስቲያኔ ብርሃን ለሆነው ጌታ ሴት ልጁ፤
ንጉሡ በመለኮታዊ ብርሃኑ የከደናት፤
ማስተዋልዋ ደስ የሚያሰኝና መራኪ፤
በመልካም ሥነ ምግባርም ሁሉ የተጌጠች፤
ልብሶቹዋ መልካም መዓዛ እንዳላቸው ውብ አበቦች የሆኑላት ናት፡፡
ከእርሱዋ በላይ ንጉሥ ተቀምጦባታል፤ ከሥሩ ያሉትንም ይመግባቸዋል፤
እውነት ከራሱዋ በላይ ነው ደስታንም ተጫምታለች፡፡
ከንፈሮቹዋም ለጌታ ምስጋናን ያወጡ ዘንድ ተከፍተዋል፤      
የልጁ አሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ሰባ ሁለቱ አርድእትም በዙሪያዎቹዋ ናቸው፤
አንደበቱዋም ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ገልጦአት እንደሚገባባት መጋረጃ ናት፤
አንገቱዋ በጌታ ወደ ታነጸችው ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም መወጣጫ ድልድይ ናት፤
እልፍኙዋ በወይን ጠጅና መልካም መዓዛ ባለው የድኅነት ሽቱ የተሞላች ናት፤                                         
በመካከሉዋ ሁሉን ደስ የሚያሰኝ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር የተጨመሩበት ጽና አለ፤
በውስጡዋም ትሑታን እርሱዋን ለማገልገል በትጋት ይፋጠኑበታል፤
ወደ ጌታ ሰርግ የጠራቻቸው እንግዶቹዋም በዙሪያዋ ታድመዋል፤
ሕያዋን የሆኑ አገልጋዮቹዋም ከፊቱዋ ቀድመው የሙሽራውን መምጣት በጉጉት ይጠባበቃሉ፤                           
አሳላፊዎቹ በጌታቸው ፊት ለመቆም እንዲበቁ በሙሽራው የክብሩ ብርሃን የተሸለሙ ናቸው፡፡

Monday, January 30, 2012

“ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጁዋ ከወዳጇ ጋር ያወጋችው ወግ” (ከቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
21/05/2004
ልጄ ሆይ አንተ የእኔ ስትሆን ሌሎች የእኛም ነው በማለታቸው እኔ እናትህ ቅናት አይሰማኝም ፡፡ ለአንተ ኃጢአቱን ለሚናዘዝ ሰው ሁሉ አምላኩ ሁነው ፤ አንተንም ለማገልገል ለሚተጋውም ጌታ ሁነው፤  ሁሉ የሚሹህ ልጄ ሆይ አንተን ያፈቀሩህ ሁሉ ወንድሞችህ ይሁኑ ፡፡
ልጄ ሆይ አንተ ከእኔ ማኅፀን ውስጥ በነበርክበት ወቅት እንዲሁ በውጪም በዓለም ነበርኽ፡፡ አንተ ከእኔ በሥጋ በመወለድ ከእኔ ሆድ ብትወጣም በሕቡዕ ግን ከእኔ ውስጥ ነበርህ ፡፡ኦ ! እኔን እናትህን በእጅጉ ያስገረምኽ ልጅ ሆይ አንተ ከእኔም ጋር ነህ በዓለምም ሙሉ ነህ፡፡
 ቅዱስ የሆንኽ ልጄ ሆይ በአካል የተገለጠውን አንተነትህን በሥጋዊ ዐይኖቼ  ስመለከት በነፍስ ዐይኖቼ ደግሞ  በሕቡዕ በውስጤ ያለውን ማንነትህን እስተውላለሁ፡፡ በአካል በተገለጠው ማንነትህ በኩል አዳምን ስመለከት ሕቡዕ በሆነው ማንነትህ በኩል ደግሞ ከአንተ ጋር አንድ ባሕርይ የሆነውን አባትህን እመለከታለሁ፡፡
ልጄ ሆይ! እንዲህ እጹብና ድንቅ የሆነውን ሁለት ዓይነት ገጽታዎች ያለውን ማንነትህን እኔ ብቻ ተመለከትኩትን? ልጄ ሆይ ይህን ሕቡዕ የሆነ ማንነትህን በሕብስቱ ውስጥ እንዲያዩት ፍቀድ፡፡ ሥጋህን በሚመገበው ሰው ሕሊና ውስጥ አንተነትህ ግለጥ፡፡ ልጄ ሆይ በግልጽም  ይሁን በሕቡዕ አንተነትህን  ያንተ ለሆነችው ቤተክርስቲያንህ እና ለእኔ ለእናትህ ዘወትር ግለጥልን፡፡

Monday, January 23, 2012

ከሕግ በላይ የሆነው የደስታና የነጻነት ሥፍራ (ጋብቻ)



ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
15/05/2004
  ድሮ ድሮ ያኔ በገነት አንድ ሔዋን የምትባል ሴት ነበረች፤ እርሱዋም ዓለሙዋ በሆነ በአዳም ሰውነት ውስጥ ትኖር ነበር፡፡  አንድ ወቅት ባልዋ አዳም በውስጡ እየተመላለሰች ደስ ታሰኘው የነበረችውን ይህቺን ሴት በአካል ተገለጣ ሊያያት ፈለገ፡፡ ነገር ግን በውስጡ ተሰውራለችና ሊያያት አልተቻለውም፡፡ ስለዚህም የደስታ መፍሰሻ በሆነችው ገነት እጅግ ታላቅ በሆነ ትካዜ ተዋጠ ተከዘ አዘነ፡፡ ገነትም ገነት አልመሰለችውም፡፡ ነገር ግን ልብ ያሰበውን ኩላሊት ያመላለሰውን የሚያውቅ እግዚአብሔር የአዳምን ጽኑ ኀዘን ተመለከተ፡፡ ስለዚህም ጽኑ እንቅልፍ በእርሱ ላይ ጣለበት፡፡ ይህንን ቅዱሳን አባቶች በተለይ አምብሮስ ተመስጦ ይለዋል፡፡ በዚያ ጊዜ ነፍስ በሥጋ ሰውነቱዋ ላይ እግዚአብሔር የሚያከናውነውን ትመለከት ዘንድ ወደ አምላኩዋ ተነጠቀች፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከሥጋዋ ከግራ ጎኑ፣ ከልቧ አጠገብ ሔዋንን  ለይቶ ገለጣት፡፡




Sunday, January 15, 2012

የአምላክ እናትነት




ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን 4/06/2003 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ጌታ ሆይ የእጅህ ሥራ ስለሆንኩ እጅግ ግሩምና ድንቅ ነኝ፡፡ ስለኃጢአቴ ራሴን ብወቅስም አንተ ግሩምና ድንቅ አድርገህ የፈጠርከውን ሰውነቴን በኃጢአቴ ምክንያት የተዋረደ ነው አልለውም፡፡ ይህ ሰውነት በአንተ ንጹሐን እጆች የተበጁ ናቸውና፡፡

እናቴ ሆይ ንገሪኝ አንቺ ትሆኝ ከሆድሽ ሳለሁ ሰው እንድሆን ዐይንና ጆሮ አፍንጫንና ግንባርን የሠራሽልኝ፣ ወይስ አንቺ ትሆኚ ሥጋዬን ከአጥንቴ ጋር አዛምደሽ ያበጃጀሻቸው? ወይስ በሥጋዬ ውስጥ ደምሥሮቼንና ጅማቶቼን አንዲሁም ልብና ኩላሊቴን ሌሎችንም ውስብስብ የሆኑ የሰውነት ሥርዐቶችን የሠራሻቸው? አንቺ ከሆንሽ በምን እውቀትሽ? እንዲህ ከሆነ ከእናቴስ በላይ አዋቂ ማን አለ? ከእናቴስ በላይ ሁሉን ቻይ ማን አለ? ነገር ግን እናቴ ዐይኖቹዋን በፍቅር ወደ አምላኩዋ አቅንታ “አንተን ከእኔ እኔንም ከእናቴ ማኅፀን ያበጀኝ እርሱ እግዚአብሔር ነው” ብላ አመላከተችኝ፡፡ ከልቡዋም ሆና እርሱዋን ሠርቶ በእርሷ ልጆቹዋን የፈጠራቸውን አምላኩዋን ዐይኖቹዋ የፍቅርን እንባ አንዳጋቱ ሲጋ እየተናነቃት ወደ እርሱ አንጋጠጠች፤ ተንበርክካም ስለቸር ስጦታው አመሰገነችው፡፡ በግንባሩዋም ተደፍታ ሁሉን እንዲህ ላከናወነው ለእርሱ ሰገደችለት፡፡ ከሰጊዱዋም ቀና ስትል ጉንጮቹዋ በእንባ ረጥበው ነበር፡፡ ዐይኖቿንም አቅንታ ክርስቶስ ከሥጋዋ ከፍሎ ወደ ፈጠራቸው ልጆቹዋ ተመለከተች፡፡ ነገር ግን እንባዋ ከጉንጮቹዋ መጉረፉን አላቋረጠም ፡፡ ምክንያቱም ጌታ ሆይ የአንተ እጅ ሥራ ናቸውና፡፡

ኦ ክርሰቶስ!!!


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ
05/04/2004 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኦ ክርስቶስ ስላንተ ሴቶች ወንዶችን ተከትለው ሄዱ፡፡(ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል የሚለውን ቃል ሽረው) ዘፍ.2፡24 ፡፡መበለት የነበረችው ትዕማር እርሱን(የባሎቿን አባት የአባታችን የያዕቆብ ልጅ ይሁዳን) ተመኘችው ፡፡ሩት ስለአንተ በእድሜ ያረጀውን ሰው ወደደችው፡፡ አዎን ሰዎችን በዝሙቷ የምትማርከው ረዓብ ባንተ ተማረከች፡፡ ትዕማር ጨለማን ለብሳ በጨለማ ወጣች ብርሃንንም ሰረቀች፡፡ ንጹሕ ባልሆነ መንገድ ንጹሕ የሆነውን ሰረቀች፡፡ ሰውነቷን በማራቆት አንተን ለመስረቅ ተጓዘች፡፡ንጹሕ ካልሆነው ንጹሕ የሆነውን የምታስገኝ አምላካችን ሆይ! ሰይጣን እርሷን አይቶ ተንቀጠቀጠ፤እናም እርሷን ለማሸበር ተፋጠነ፤ በእርሷ አእምሮ ውስጥ ፍርድን አስገባ፤ ነገር ግን እርሷ አልተሸበረችም፡፡ ስለአንተ በድንጋይ መወገርና በሰይፍ መቀላት አላስደነገጣትም፡፡ ይሁዳን ለማጥመድ ዘማውያንን መሰለች ከእዛ በኋላ ግን ልትዘሙት አልወጣችም፤ ምክንያቱም ዝሙትን የማይፈቅደውን ጌታ ሽታ ነውና የወጣችው፡፡ (ቅ/ ኤፍሬም ዘሶሪያ)