Thursday, March 1, 2012

ገነት በቅዱስ ኤፍሬም


ትርጉም ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
22/06/2004
በዚህ መዝሙር ቅዱስ ኤፍሬም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን ዓለት በማንሣት እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንዴት እንደፈጠራቸውና ስለገነት ያለውን አስተምህሮ እንመለከታለን፡፡

እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን አለትን አስታውሼ ዓለማትን የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልብ አልኩ፡፡ እንደ ታላቅ ወንዝ ለእነርሱ ከአለቱ ውስጥ የፈለቀው ውኃ በውስጡ ካለው የውኃ ቋት የተገኘ አልነበረም ፡፡ በአለቱ ውስጥ አንድም ጠብታ ውኃ የለም፤ ነገር ግን ልክ የእግዚአብሔር ቃል ፍጥረትን ከምንም እንዳስገኛቸው፤እንዲሁ ታላቅ የውኃ ጅረት ከደረቅ ድንጋይ ውስጥ ፈልቆ የተጠሙትን አረካቸው፡፡
ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ተፈጥሮ ገልጦ ጽፎልናል  ስለዚህም ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈጣሪ ምስክሮች ሆኑ፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለራሱ ጥቅም ሲገለገልባት እንደሚያውቃት እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በውስጡ የያዘውን መረዳት ይቻለናል እነዚህን ሁለቱን ምስክሮች በሁሉ ስፍራ እናገኛቸዋለን፡፡





እግዚአብሔር የለም የሚሉትን ኢአማንያንን ለማሳፈር እነዚህ ሁለቱ በሁሉም ጊዜና ሰዓት የሚገኙ የእግዚአብሔር ሕልውና አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው ፡፡ ጌታ ሆይ የመጽሐፍህን መግቢያ ባነበብኩ ጊዜ ልቤ በሃሴት ተሞላ፡፡ የምንባቡ ቁጥሮችና ኃይለ ቃላት እኔን ለመቀበል እጆቻቸውን ዘረጉ ይዘውኝም በፍቅር አቀፉኝ ሳሙኝም ወደ ወዳጃቸውም መርተው አደረሱኝ ፡፡ የገነት ታሪኩዋ እኔን ወደ ላይ ወደ ሰማይ እንድነጠቅና ወደ ውስጥ እንድገባ አሸጋገረኝ፡፡ከመጽሐፉ እቅፍ ወደ ገነት እቅፍ ተሸጋገርኩ፡፡ ዐይኔና ልቤ ቃሎቹ በሰፈሩበት መስመር ላይ ተጓዙ፤ በድልድይ እንደሚሸጋገር ሰው በገነት ታሪክ ወደ ላይ ተነጠቅሁ፡፡ በዚያን ጊዜ ዐይኖቼ  ምንባቡን  ሲያነቡ አእምሮዬ ያርፍ ነበር፡፡ አእምሮዬ በምሥጢር ሲነጠቅ ዐይኔ ደግሞ በተራው ከማንበብ ያርፋል፤ ከንባብ በኋላ ዐይኖቼ ሲያርፉ አእምሮዬ ምሥጢራትን በመመርመር ተጠመደ ፡፡ 

ወደ ገነት መሸጋገሪያ ድልድዩንና መግቢያ በሩን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አገኘሁት፤ ስለዚህም በድልድዩ ተሸጋግሬ በበሩ በኩል ወደ ውስጥ ዘልቄ ገባሁ፡፡  
በእርግጥ ዐይኖቼ በውጭ ነበሩ አእምሮዬ ግን ወደ ውስጥ ዘልቆ ገብቶአል፡፡ እናም በቃላት ሊገልጡት በማይችሉት አጸድ መካከል ቆሜ መደነቅ ሞላብኝ፡፡ ስፍራው ታላቅ ፣ ፀጥታ የሰፈነበት ፣ ፍጹም ንጹሕና ክቡር ስፍራ ነው፡፡
በረከቶች ሁሉ የሚገኙበትን ይህን ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ ኤደን ብሎ ይጠራዋል፡፡ በዚያም ለቅዱሳን የተዘጋጀ አጸድና የተንጣለለ ለምለም መስክ አለ፤  በላዩም መዓዛው እጅግ ማራኪ የሆነ ሽቱ ተርከፍክፎበታል፤
አጸዱም በፍራፍሬዎች የተጌጠ፣ የፈኩ አበቦቹም አክሊሎቹ የሆኑለት ነው፡፡ መስኩ ርስት ሆኖ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን የሚሰጥ ሲሆን፤ በጽድቅ ሕይወት ላልተጋው ውበቱ ማራኪ ያለሆነ ያልተጌጠም መስክ ይሰጠዋል፡፡ ለተጋው ግን ውበቱ ዐይንን ይዞ የሚያስቀር እጅግ ማራኪ የሆነ መስክ ይሰጠዋል፡፡ በገነት አጸድ ውስጥም ሳለሁ ገነት ለቅዱሳን ማረፊያነት ትበቃቸዋለችን? ብዬ ጠየቅሁ፤ መሠረቴን መጽሐፍ ቅዱስን አድርጌ በመጽሐፍ ውስጥ ያልሰፈሩትን ለመመርመር ሞከርኹ፡፡
ሌጌዎን የተባለው የአጋንንት ሠራዊት በአንድ ሰው ሰውነት ውስጥ ሰፍሮ እንደነበር አስተዋልሁ(ሉቃ.5፡9፤8፡30) ይህ የአጋንንት ሠራዊት በሠራዊቱ ቁጥሩ እጅግ ብዙ ቢሆንም ከርቀታቸው(ከረቂቅነታቸው)የተነሣ እንደ አንዲት ነፍስ እንኳ ጎልተው መታየት አልተቻላቸው ነበር፡፡ በአንድ አካል ውስጥ የአጋንንት ሠራዊት ቦታው ሰፍቶአቸው በርቀት እንዲኖሩ፤ እንዲሁ በትንሣኤ የተነሡ ቅዱሳንም በገነት መቶ ሺኽ ጊዜ ረቀው ይኖራሉ እንጂ ገነት አትጠባቸውም፡፡ 
ገነት በአእምሮ፤ ቅዱሳንም በአእምሮ የማሰብ አቅም ይመሰላሉ፡፡ አንድ ሰው እንደ ፈቃዱ በአሳቡ እጅግ ሊራቀቅና ሊመጥቅ ይችላል፡፡ ቢፈልግ ደግሞ አመለካከለቱን ሊያጠበውና በአንድ ነገር ላይ ብቻ ሊወስነው ይችላል፡፡ አንድ ሰው አመለካከቱን በቦታ ሊወስን ወይም ከቦታ ውጪ ሊያደርገው ይችላል፡፡
 መብራት ሲበራ እጅግ የብዙ ብዙ ሺኽ ጨረሮች በአንድ ቤት ውስጥ እንዲኖሩ ፤ ከብዛታቸው የተነሣ ማደሪያቸው እንዳይጠባቸው፤ እንዲሁም እጅግ ትንሽ በሆነችዋ አበባ ውስጥ አካባቢውን ሁሉ የሚያውድ  መዓዛ እንደሚገኝ፤ ለማዓዛዎቹ ማኖሪያ የሆነችው አበባ እንዳልጠበበቻቸው፤ እንዲሁ ገነት ለቅዱሳኑ ማደሪያነት አትጠባቸውም፡፡ ምንም እንኳ የብርሃኑ ጨረሮችና የአበባው መዓዛ በጠባብ ቦታ ላይ የተወሰኑ ቢሆኑም፤ የስፍራው ውሱንነት ግን እንደልባቸው እንዲዋኙ አልከለከላቸውም፤ ለቅዱሳንም ገነት እንዲሁ ናት፡፡ እንዲህም ስለሆነች ገነት በውስጡዋ በመንፈሳዊ ፍጥረታት የተሞላች ብትሆንም ፤ ወደ እርሱዋ የመጡትን ለማኖር ከበቂ በላይ የሆነ ሥፍራ አላት፡፡ 


በቁጥር እጅግ የበዙ አሳቦች በትንሹዋ የጭንቅላታችን ክፍል ውስጥ ይኖራሉ፤ ስፍራዋም አንዱን በአንዱ እንዲወሰን አላደረገውም፤ ወይም ስፍራዋ እነርሱን አልወሰነቻቸውም፤ ይህ እንዲህ ከሆነ እንዴት ገነት በመጠናቸው እጅግ ረቂቃን ለሆኑት ቅዱሳን ሰውነት የበቃች አትሆን!! የቅዱሳን ነፍሳት ርቀትም ከአእምሮአችን የመረዳት አቅም በላይ ነው፡፡
 በገነት መካከል ሆኜ እንደ ችሎታዬ መጠን ምስጋናዬን ለአምላኬ ላቀርብ ወደድኩ፤ ድንገትም በገነት ውስጥ እንደ ነጎድጓድ  የመሰለ ጥሙም የምስጋና ድምፅ ተሠማ፡፡ ድምፁም ልክ በአንድ የጦር ሰፈር እንደተሰማ የመለከት ድምፅ ይመስል ነበር፡፡ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሚል የምስጋና ዝማሬ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ተስተጋባ፡፡ ይህን ስሰማ  ከቅዱሳኖቹ ለአምላክ ምስጋና እየቀረበ እንደሆነ ተረዳሁ፤  እስከዛ ጊዜ ድረስ ግን ገነት ባዶ ትመስል ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ነጎድጓድ የሆነውን ይህን ድምፅ ስሰማ ቅዱሳን በዚያ ከትመው እንዳሉ ተረዳሁ፤ስለዚህም ገነት በጸጥታዋና በውበቱዋ እጅግ ማረከችኝ በሐሴትም ተሞላሁ፡፡ በውስጡዋ ያለው  የአጸዱ ውበት አንዳች እንከን የለበትም፡፡ በውስጡዋ ከሰፈነው ጸጥታ የተነሣ አንዳች ፍርሃት የለም፡፡ ይህችን ገነት ለመውረስ የተገባው ቅዱስ እንዴት ብፁዕ ሰው ነው! ይህችን ስፍራ በቅድስናችን ሳይሆን በእርሱ ጸጋ፤ በድካማችን ሳይሆን በእርሱ ቸርነት የምንወርሳት ስፍራ ናት፡፡
 የገነት ድንበሮችን አልፌ ወደ ውስጡዋ ስዘልቅ በውበቱዋ እጅግ ተደመምኩ፤ በዙሪያው ያሉትን የእግዚአብሔር ወዳጆችን ወደኋላዬ ትቼ በደኅንነት ወደሚኖርባት ገነት ዘለቅሁ፡፡ ነገር ግን የሾኽና የአሜካላ እናት ወደሆነችው ምድር ስመለስ፤ ልዩ ልዩ ዓይነት ሕማሞችንና ስቃዮችን ተቀበልኩ፡፡ ስለዚህም ምድርን ከገነት ጋር ሳነጻጽራት ልክ እንደ ወህኒ ቤት ሆና አገኘኋት፡፡ የሚደንቀው ግን በውስጡዋ ያሉ እስረኞች እርሱዋን ለቀው ሲወጡ ማንባታቸው ነው፡፡ ሕፃናት ከእናቶቻቸው ማኅፀን ሲወጡ ማልቀሳቸው ሁሌም ያስገርመኛል፡፡ የለቅሶአቸውም ምክንያት ከጨለማ ወደ ብርሃን መምጣታቸው ነበር፡፡ እነዚህ ሕፃናት ከተጨናነቀው ሥፍራ ወደ ሰፊይቱ ዓለም በመምጣቸው ያነባሉ፡፡ እኛም ልክ ከእናታችን ማኅፀን ስንወጣ የምናለቅሰውን ለቅሶ ዓይነት በሞት ከዚች ዓለም ስንለይ ምርር ብለን እናለቅሳለን፡፡ የሚደንቀው ግን ሰዎች የሚያነቡት እንባ የስቃይ እናት ከሆነችው ከዚህች ዓለም ተወልደው እጅግ ግሩም ወደ ሆነችው ገነት በመግባታቸው መሆኑ ነው፡፡


የገነት ጌታዋ የሆንኽ ቸሩ ፈጣሪያችን ሆይ ለእኛ ራራልን፤ ወደ ገነት ለመግባት ምናልባት የበቃን ባንሆንም በገነት ዙሪያ ባለው አጸድ እንድንሆን ፍቀድልን፡፡ ከአንተ ጋር ያሉ ቅዱሳን ከገነት ፍሬዎች ተመግበው ሲጠግቡ እኛ ኃጥአን በአንተ ቸርነት ከፍርፋሬአቸው ተመግበን ሕያዋን እንሆን ዘንድ ከውጭ ላለነው ኃጥአን ራራልን፡፡
እኔስ ይህን ስለቅዱስ ሥጋውና ስለክቡር ደሙ ነው እላለሁ፡፡  

1 comment:

  1. AMEN kale hiwot yasemaln tsegawn yabzalh minga dink tsuf new be ewnetu.endeniya aynetu andebete koltafam le genetn emiyabeka sera bay norogem kedegafu keberu endtal yargeg. ende kudus PAWLOS ye amlakachin kudus sefera emninafk yargen !!!

    ReplyDelete