Wednesday, March 7, 2012

በዓለ እግዚእ በቅዱስ ኤፍሬም




ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/06/2004 
ይህቺ ቀን ለቅዱሳን ነቢያት ነገሥታትና ካህናት የደስታቸው ቀን ናት፡፡ በዚህች ቀን በይሁዳ አውራጃ በቤተልሔም እንደ ተስፋ ቃሉ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ሊያድናቸው ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም አማኑኤል ተወለደ፡፡ እነሆ ድንግል አስቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች”(ኢሳ.7፡14)ብሎ የተነገረው የትንቢት ቃል እውን ሆነ፡፡ አሕዛብን ወደ እርሱ የሚያቀርባቸው በዚች ቀን ተወለደ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ስለእርሱ የተናገረው ትንቢት ዛሬ ተፈጸመ፡፡(መዝ.130፡1-7) ሚክያስ የተናገረው የትንቢት ቃልም እንዲሁ፡፡(ሚክ.5፡2) ጌታችን በኤፍራታ እረኛ የሆነው ክርስቶስ ተወለደ፡፡(ማቴ.2፡1-2) በበትሩም(በመስቀሉም) በእርሱ የታመኑትን ይጠብቃቸዋል፡፡ ከያዕቆብ ኮከብ ወጣ ከእስራኤልም ራስ የሆነው ተነሣ፡፡ በልዓም አስቀድሞ “አያለሁ አሁን ግን አይደለም እመለከታለሁ በቅርብ ግን አይደለም ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤልም በትር ይነሣል”ብሎ የተናገረው የትንቢት ቃል በዛሬዋ ቀን ተፈጸመ፡፡(ዘኁል.24፡17) በሕቡዕ የነበረው ብርሃን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታየ፡፡ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ብርሃን ዛሬ በቤተልሔም አበራ!(ዘካ.4፡1-3)

መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በምሳሌ ያናገረው በዛሬዋ ዕለት ተፈጸመ፡፡ ሥር ምድሪቱን አጥብቆ እንዲይዝ እንዲሁ ምሳሌው ለዋናው አስረጂ እንዲሆን አስቀድሞ ተነገረ፡፡ ትዕማር በይሁዳ ጉልበት ንጉሥ ክርስቶስ እንዳለ አስተዋለች፤ ስለዚህም ከእርሱ አብራክ  የሁሉ መድኀኒት የሆነው ክርስቶስን ሰረቀችው፡፡(ዘፍ.38፡15-16) ሩትም በሕቡዕ የነበረውን የንጉሡን ውበት ተመለከተች፡፡ የሕይወት መድኀኒት የሆነው ክርስቶስን በቦዔዝ ጉልበት እንዳለ ስለተረዳች በእግርጌው ተኛች፡፡(ሩት.3፡8-10)እነሆ ሩት ምኞቱዋ ተፈጸመ፤ ሕመምተኞችን የሚያድን ከእርሱዋ ዘር ተወልዶአልና፡፡
አዳም ከጎኑ በተገኘችው ሔዋን ምክንያት መከራን ቢቀበልም በዛሬዋ ቀን ግን በእርሱ ላይ ከመጣበት መከራ ዳግማዊቱ ሔዋን ታደገችው፡፡ ከእርሱዋም ወገን ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም መድኀኒት የሆነው ክርስቶስ ተወልደ፡፡ እናታችን ሔዋን ከኅቱም ገቦ ተወለደች፤ እንዴት ታዲያ የሔዋን ልጅ የሆነችው ድንግል ያለወንድ ዘር በድንግልና ልጅ መውለዱዋ የማይታመን ይሆናል! ድንግል የሆነች ምድር ገዢዋ የሆነውን አዳምን ወለደችው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምም ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ፤ የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስን ወለደችልን፡፡ የአሮን በትር ለምልማና ፍሬ አፍርታ ተገኘች፤ ይህች በትር ክርስቶስ ኢየሱስ በድንግልና የመወለዱ ምሳሌ ነበረች፡፡…
…ጌታ ሆይ ግምጃ ቤትህ ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ተሰውረው የነበሩ ምሥጠራት መገለጥ ጀመሩ፡፡ ያንተን ልደት አስቀድመው የተናገሩትን የነቢያት ቃል ፈጸምህ፡፡ ወንድሙ ቃየን በገደለው በአቤል ምትክ የተወለደው ሴት የክርስቶስ ምሳሌ ነበር፡፡ እርሱ የቃየን ክፋት ለዓለም እንዲገለጥ ምክንያት ሆነ፡፡ አቤል ለክርስቶስ የሞቱ፣ ሴት ደግሞ የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡  ኖህም የእግዚአብሔር ልጆች በዝሙት ሲተዳደፉ ተመለከተ፡፡ ስለዚህም በዝሙት የረከሱት ንጹሐን የሚሆኑበትን የእግዚአብሔር ልጅን ሻተ፡፡ እርሱ ሰክሮ እርቃኑን ሆኖ ሳለ በልብሳቸው እርቃኑን በከደኑት በሴትና በያፌት ምሳሌውን ተመለከተ፤ በዚህም በትዕቢት ሰክሮ የተራቆተውን የአዳምን ነውር ይከድን ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲመጣ አስተዋለ፡፡ ብሩክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእነርሱ ከነዓንን ከኃጢአት ባርነት ነፃ እንደሚያወጣው ተመልክቶአልና እነርሱን ባረካቸው፡፡
የአሮን በትር እባቦችን እንደዋጣቸው እንዲሁ መስቀሉ አዳምንና ሔዋንን የዋጠውን የቀድሞውን እባብ ዋጠው፡፡ ሙሴ የነዝር እባብ የነደፋቸው ወገኖቹ ከነሐስ የተሠራውን እባብ በተመለከቱ ጊዜ እንደተፈወሱ ተመለከተ፤ በምሳሌውም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ተወልዶ የቀደመው እባብ(ሰይጣን) የነደፋቸውን አዳምንና ሔዋንን እንዲፈውሳቸው አስተዋለ፡፡ ሙሴ ከእግዚአብሔር ዘንድ የጸጋ ብርሃንን እንደተቀበለ ተመለከተ፡፡ በእርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ወደ እዚህ ዓለም በመምጣት በትምህርቱ በጸጋ አማልክት የሆኑትን እንደሚያበዛቸው አስተዋለ፡፡ የነዌ ልጅ የሆነው ኢያሱ (ኢያሱ ማለት መድኀኒት ማለት ነው) በስሙ ታላላቅ ተአምራትን አደረገ፡፡ እርሱ እንዲህ ካደረገ የስሙ ባለቤት የሆነው ወልደ እግዚአብሔር እንዴት ታላላቅ ተአምራትን አያደርግ?... ስለዚህም ስለልደቱ ለመስማት የቀረቡ ጆሮዎች ወደ ቃሉ ያዘንብሉ፣ እርሱን የሚያዩ ዐይኖችም ንጹሐን ይሁኑ፡፡ ልባችንም በተመስጦ በምስጋና ይትጋ፡፡ አንደበታችንም የታረመ ይሁን፡፡ በዛሬዋ ቀን ቅድስት እናታችን ከአብርሃም ዘር የሆነውን ሕብስት እንድንቀበለውና ሰውነታችን የእርሱ ማደሪያ ቤተመቅደሱ እንዲሆን ምክንያት ሆናልናለችና እናመስግናት፡፡
 ዛሬ የወይን አቁማዳችን ቅዱስ ከሆነው ከዳዊት ቤት ተሞልቶልናል፡፡ ስለዚህም ዳዊት ለሚያሳድደው ሳኦል ምሕረትን እንዳደረገ፤ እንዲሁ እኛም ለሚያሳድዱን ምሕረትን እናድረግ፡፡ ሰውና አምላክ ፍጹም እርቅን በፈጸሙባት በዚህች ዕለት ማንም በወንድሙ ላይ አይቆጣ፤ ክርስቶስንም ይዞ ተስፋ አይቁረጥ፡፡ ይህች ዕለት አፍቃሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ዕለት ናትና፡፡ ይህቺን ዕለት አስበው ገዢዎች ሕዝቡን ማስመረራቸውን ይተዉ፡፡ ይህች ዕለት የዋህና ትሑት የሆነው ጌታችን የተወለደባት ዕለት ናትና መራርነትንና አልከኝነትን ከእኛ እናርቅ፡፡
 በዚህች ዕለት እግዚአብሔር ወደ ኃጢአተኞች መጣ፤ ስለዚህ ጻድቁ በኃጥኡ ላይ አይታበይ፡፡ በዚህች ቀን የሁሉ ጌታ የሆነው እርሱ ወደ ባሮቹ መጣ፤ እናንተ ጌቶች ሆይ እንደ ጌታችን ለአገልጋዮቻችሁ ቸርነትን አድርጉላቸው፡፡ በዚህች ቀን ባለጠጋ የሆነው እርሱ ስለእኛ ሲል ደሃ ሆነ፡፡ እናንተ ባለጠጎችም ሆይ በማዕዳችሁ ደሃው ይገኝ፡፡ በዚህች ቀን እኛ ያላሰብነውን ስጦታ ከጌታ ዘንድ ተቀበልን፤ እኛም ምጽዋትን ላልጠየቁን ድሆች እናድርግ፡፡ ከእኛ ይቅርታን ሽተው የመጡትን ይቅር እንበላቸው፡፡ በዛሬዋ ቀን የፍጥረት ጌታ የሆነው እርሱ ከባሕርይው ውጪ የሰውን ተፈጥሮ ገንዘቡ አድርጎ በሥጋ ተገልጦአልና፣ እኛም ወደ ክፉ ፈቃድ የሚወስደንን አመፃን ከእኛ ዘንድ አርቀን በአዲስና እርሱ በሰጠን መንፈሳዊ ተፈጥሮ እንመላለስ፡፡… እኛ አማልክት እንድንሰኝ አምላክ የሆነው እርሱ ሰው ሆኖአልና …(ሰው አምላክ ሆነ አምላክ ሰው ሆነ ማለት ነው)….
   በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይሉንና የማይታይ ባሕርይውን በሚታይ አካል ለገለጠልን ለእርሱ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ይሁን፡፡ በሥጋ ዐይናችንና በሕሊናችን እነሆ ልጁን በግርግም እንስሳት አስትንፋሳቸውን እያሟሟቁት ተመለከትነው፡፡… ስለዚህም እኛም እንደመላእክት ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ” እያልን ዘመርን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር፡፡
  

1 comment:

  1. kale hiwot yasemal edmi ena tina yistot yagelglot zemnotn yarzmlin Egziabhir yistiln .Amlak sew hono dhnetn lesete ke hatiyat barnet netsa lawetan ytemesegene yihun.

    ReplyDelete