በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
28/06/2004
ጌታችን ሆይ! ዛሬ ወደ ኋላ ተመልሼ የአዳምና የሔዋን ቅድስናና ንጽሕና
ምን ይመስል እንደነበረ ለማስተዋል ሞከርኩ፡፡ ጌታ ሆይ! የኃጢአታችንን ታላቅነት እኛ በአንተ ላይ ባደረስነው መከራ ስንመለከተው፣ የጥንት ቅድስናችንንና ንጽሕናችንን በአንተ ሰው መሆን ውስጥ ተመለከትነው፡፡ አዎ ጌታችን ሆይ! በአንተ የቀደመው የቅድስና ሕይወታችን ምን ያህል ማራኪ እንደነበረ አስተዋልነው፡፡ አንተ በልብህ
ትሑትና የዋህ እንደሆንክ ነገር ግን የዋህነትህ ከእውቀት ጉድለት እንዳልሆነ እንዲሁ ከውድቀት በፊት የአዳም አባታችንና የሔዋን
እናታችን ትሕትናና የዋህነት በእውቀት የተሞላ ነበር፡፡
አንተ ፍጥረትህን ነፍስህን እስከ መስጠት ደርሰህ እንድትወድ እንዲሁ
አዳምና ሔዋንም ራሳቸውን እስከመስጠት ድረስ ደርሰው አንተንና ከሥራቸው ያስገዛህላቸውን ፍጥረታት ይወዱ እንደ ነበር አሳየኸን፡፡
ጌታ ሆይ! አዳምና ሔዋን እርስ እርሳቸውም ያላቸው ፍቅር በአንተና በአባትህ መካከል እንዳለው ዓይነት ፍቅር ይመስል ነበር፡፡ ቅድስናቸውም
አንተ “የሰማዩ አባቴ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ብለህ እንዳስተማረከን ዓይነት ሥላሴን አብነት ያደረገ ቅድስና ነበር፡፡
ይህ እንደ ሕፃን ቅዱስና ንጹሕ የሆነ የአዳምና የሔዋን ተፈጥሮ በአንተ ዘንድ እጅግ ተፈቃሪ ነበር፡፡ ስለዚህም አባታችን ያዕቆብ
ከልጆቹ ይልቅ የክርስቶስ ኢየሱስ አርአያ ያለውን ዮሴፍን እንዲወደው፣ አንተም ጌታ ሆይ! እኛን የሰው ልጆችን ከሌሎች ፍጥረታት
ሁሉ ይልቅ የአንተ አርአያ ይታይብናልና ትወደን ነበር፡፡
ዮሴፍ
በክፉ ወንድሞቹ ቅናት ለአውሬ እንደ ተሰጠ ያዕቆብ አባቱ በሰማ ጊዜ ኃዘኑ እጅግ ጽኑ እንደነበርና “ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ
እያዘንሁ እወርዳለሁ”ብሎ በእጅጉ እንዳዘነ(ዘፍ.37፡35) እንዲሁ አንተም አዳምና ሔዋን በክፉ ሰይጣን ተንኮል ስተው ከቅድስናቸው
በወጡ ጊዜ ሐዘንህ እንደሞት የበረታች ጽኑ ነበረች፡፡ ምክንያቱም እጅግ ታፈቅራቸው ነበርና፡፡
ነገር ግን በአባቱ ፊት እንዲያ ተወዳጅ እንደሆነው ዮሴፍ ተወዳጆች
የሆኑት አዳምና ሔዋን አንተን ሽተው ወደ አንተ በንስሐ በተመለሱ ጊዜ እነርሱን ለመገናኘት ልብህ ቸኮለ፡፡ እነርሱም እንዲሁ አንተን
አባታቸውን በእጅጉ ናፍቀዋልና አንተን ለመገናኘት ቸኮሉ፡፡ ነገር ግን አንተ ያሳዘኑበትን የገዛ ኃጢአታቸውን አሰቡት፡፡ ቢሆንም ዮሴፍ አባቱ ያዕቆብን እንደናፈቀው እነርሱም አንተን በእጅግ ናፍቀውሃል፡፡ ነገር ግን እንዴት ብለው ወደ አባታቸው እንደሚቀርቡ አሰቡ ፣ተጨነቁ፤ ተጠበቡ፤ አወጡ አወረዱ፡፡ በመጨረሻም በዚህች ምድር ከአባታቸው ርቀው በባርነት ከመኖርና በርሃብ ማቀው ከመሞት ይልቅ በእርሱ እጅ መውደቅን መረጡ፡፡
በንስሐ ወደ አባታቸው ለመሄድ ሲነሡም አባታቸው ለእነርሱ የነበረውን የቀድሞውን ፍቅር
እንዲያስብና ይቅር እንዲላቸው ሲሉ“አባት ሆይ በሰማይና በፊትህ በደልን ወደፊትህ ልጆችህ ልንባል አይገባንም ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ
አድርገን” ብለው እርሱን ለመማጸን ወሰኑ፡፡ እናም በንስሐ መንገድ ወደ አባታቸው አመሩ፤ እርሱም እጅግ ናፍቆአቸዋልና ከሩቅ በተመለከታቸው
ጊዜ ከዙፋኑ ወርዶ እጆቹን ዘርግቶ ተቀበላቸው፤ አንገታቸውንም አቅፎ ሳማቸው፡፡ ባሮቹንም እንዲህ አላቸው “ፈጥናቹህ የተሻለውን ልብስ አምጡና አልብሷቸው ለእጃቸውም
የቃል ኪዳን ቀለበቴን እሰሩላቸው፤ ለእግራቸውም የጽድቅን ጫማ አጫምቶአቸው፡፡ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁም እረዱት እንብላም ደስ
ይበለን፤ እነዚህ ልጆቼ ሞተው ነበርና ደግሞም ሕያዋን ሆነዋል፤ ጠፍተው ነበር ተገኝተዋልና”ብሎ በፍቅርና በናፍቆት እንዲሁም በታላቅ
ደስታ ተቀበላቸው፡፡ አባታቸው ሥላሴ እጅግ ደስ ብሎታልና በቅድስና ይኖሩ የነበሩትን ቅዱሳንን ሁሉ ወደ ልጆቹ ግብዣ ጠራቸው፡፡
መላእክትም ታላቅ የሆነን ደስታ በሰማያት አደረጉ፡፡
ጌታ ሆይ! በእጃችን ያጠለቅኸው ቀለበት እኛ በጥምቀት ለአንተ የታጨንበት
የእጮኝነታችን ቀለበት ነው፡፡ የተጫማናትም የጽድቅ ጫማችን በአንተ የተሰበከች ወንጌል ናት፡፡ ስለ እኛ የታረደውና እንበላው ዘንድ የቀረበለን የሰባው
ፍሪዳ ቅዱስ ሥጋህና ክቡር ደምህ ነው፡፡ ሕይወታችን ከሆንከው ካንተ ተለይተን ነበርንና ሞተን ነበር፡፡ አሁን ግን አንተን አግኝተናልና ሕያዋን ሆንን፡፡
ጌታ ሆይ እኛን እንዲህ ታፈቅረን ዘንድ እኛ ምንድን ነን? እኛ በራሳችን
ማስተዋል ተደግፈን እንደ አንተ አምላክ ለመሆን በመመኘት “ከአንተ ይልቅ እኛ ቅዱሳን ነንና ወደ እኛ አትቅረብ” ያልንህን እኛን ለማዳን ሰው በመሆን ወደ እኛ ቀረብክህ፡፡ በመስቀል ላይ ራስህን ስለእኛ መሥዋዕት አድርገህ በማቅረብ በሞትህ ሞታችንን አጥፍተህ ሕያዋን አደረግኸን፡፡
በኃጢአት ያደፈውን ልብሳችንን አውልቀህ ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችሁታል”(ገላ.3፡27)
እንዲል ራስህ ልብሳችን ሆንክ፡፡ በርሃቡ ጽናት ምክንያት ወይቦ የነበረውን ሥጋችንን፣ ከስታ የነበረችውን ነፍሳችንን ራስህን መብል አድረገህ
በማቅረብ እንደ ሙሴ ቁርበት ሰውነታችን እንድትበራ፣ ነፍሳችንም እንድትወፍር አደረግሃት፡፡ ለዚህ ቸር ስጦታ ጌታ ሆይ! እኛ ምን
ልንከፍልህ እንችላለን? ጌታ ሆይ! አንተ ለእኛ ያለህ ፍቅር እንዴት ግሩም ነው!
ጌታችን ሆይ! ቅዱስ ኤፍሬም እንዳለው ይህን ስለእኛ የተቀበልከውን ሕማም ዘወትር ማሰባችን
ለእኛ ማስተዋልን ሰጥቶ ከኃጢአት ይጠብቀናልና፤ ይህን ታላቅ የሆነውን ፍቅርህን ዳግም እንዳንበድል ዘወትር ስለእኛ የተቀበልከውን ሕማምና መከራ ማሰብን ስጠን፡፡ ስንተኛ በመኝታችን ውስጥ አንተን እንዳናሳዝን፣ ስንነቃም በማስተዋል ወደፊት ያለውን
ጊዜአችንን በጽድቅ እንድንመላለስበት፤ ስንበላ ጠግበን ስሜታችንን ተከትለን እንዳንበድልህ፤ ከቤታችን ስንወጣም ቢሆን ስንገባ በውጪም
ይሁን በቤታችን አንተን እንዳናሳዝን፤ በሥራ ገበታችንም ቢሆን በዕረፍት ሰዓታችን ፈቃድህን አስበን እርሱንም ለመፈጽም እንድንተጋ፤
ወደ ቤትህም በሄድን ጊዜ በፍርሃትና በመገዛት እንዲሁም በፍጹም ማስተዋል ሥርዐት እንዳለው ልጅ ሥጋዊ ፈቃዳችንን ከማድረግ ተቆጥበን ከአንተ ጋር ለመነጋገር እንድንበቃ፤ ጌታ
ሆይ ማማተብን ልማዳችን እንድናደርገው አለማምደን፡፡ ስናማትብ አንተ ለእኛ በመስቀል ላይ የተቀበልከውን አስበን በማስተዋል እንመላለስ
ዘንድ፡፡
ኦ! ክርስቶስ ሆይ እንዴት ግሩም! ነው አንተ ለኛ ያለህ ፍቅር አቤቱ እባክህን እንዲህ ያሉትን አንተ ስለኛ ያለህን ከእጹብ በለይ ያለውን ፍቅርህን ባአስተምሮታቸው የሚያሳዩን መምህራን አብዛልን ለሀገራችን ብሎም ለምድራችን ወንድማችን ጸጋውን ያብዛልህ ተተኪም የምታፈራ ሁን ቃለ ህይውት ያሰማልን።
ReplyDeleteAMEN KALE HIOWT YASEMALEN TESEFA MINGISETE SEMAYATEN YAWERSELEN YAGELGELOT ZEMENEN YAREZEMELEN !!!
ReplyDelete