Monday, March 5, 2012

ተወዳጆች ሆይ እናንተ……ናችሁ!!(በአፍርሃት ሶርያዊ)


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/06/2004
"ተወዳጆችና የሰላም ልጆች እንዲሁም የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ሆይ! እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ እናንተ የምድር ጨውና የሰውነት(የዓለም) ዓይኖች ናችሁ፡፡ እናንተ የሙሽራውና የመልካሙ ዘር እንዲሁም የሕይወት ውኃ ለሚፈልቅበትና የማዕዘን ራስ ለሆነው ሕያው ዓለት ክርስቶስ ሚዜዎች ናችሁ፤ እናንተ አጥልቃችሁ በመቆፈር ቤታችሁን በዓለት ላይ የምትሠሩ ብልህ አናጺዎች ናቸሁ፡፡
እናንተ የብዙ ብዙ የሆነ እህልን በጎተራችሁ የምታከማቹ ታታሪ የጽድቅ ገበሬዎች ናችሁ፡፡ እናንተ የተሰጣችሁን ጥሪት ብዙ እጥፍ አትርፋችሁ የተገኛችሁ ትጉሃን ነጋዴዎች ናቸሁ፡፡ እናንተ ዋጋችሁን ተቀብላችው ሌላ ይጨመርላችሁ ዘንድ ያልጠየቃችሁ ቅን ሠራተኞች ናችሁ፡፡


 እናንተ የመንግሥቱን ቁልፍ የተቀበላችሁ የጽድቅ አምባሳደሮችና አዋጅ ነጋሪዎች ናችሁ፡፡ እናንተ የመርከቢቱ መሪዎችና ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎችን ለሌሎች የምታከፋፍሉ  የጸጋው መጋቢዎች ናችሁ፡፡ እናንተ የአዲሱ ወይን ማኖሪያ አዲሶቹ አቁማዳዎች ናችሁ፡፡ እናንተው የጸጋ ልብስ ናችሁ፡፡ እናንተ ሐዋርያትና በጽድቅ ለተጌጠችው ሙሽራ ወንድሞችና በጨለማ ላሉት ብርሃናቸው ናችሁ፡፡ እናንተ የሰላም ልጆችና የክርስቶስ ወንድሞች እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደሶች ናችሁ፡፡

እናንተ የጽድቅ አክሊልን ለመቀዳጀት የሮጣችሁና የድሉንም አክሊል የተቀዳጃችሁ ሯጮች ናችሁ፡፡ እናንተ በወይን እርሻ የተተከላችሁ የወይን ዛፎችና መቶ እጥፍ ፍሬን የምትሰጡ መልካሞቹ የስንዴ ቅንጣቶች ናችሁ፡፡ እናንተ መብራታችሁን አብርታችሁ በጽድቅ በመጽናታችሁ ምክንያት በጠበበችዉ የመንግሥተ ሰማያት በር ወደ ሰርጉ ቤት የገባችሁ ደናግላን ናችሁ፡፡
እናንተ በእውነተኛዋና ቀጭኑዋ ጎዳና ወደ መንግሥቱ በመግባት በእርሱ ቀኝ የቆማችሁ በጎቹ ናችሁ፡፡ እናንተ በመስቀሉ የዳናችሁ በክርስቶስ ሥጋና ደም ቤዛነትን ያገኛችሁ ናችሁ፡፡ እናንተ በአዲስ ልደት ነፍሳት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ  ዘንድ ወደ አንዲት ጥምቀት የምትጠሩ የክርስቶስ አምባሳደሮችና ሰባኪያን ናችሁ፡፡
እናንተ መዓዛው ከሩቅ የሚያውድ መልካሙ ሽቶ ናችሁ፡፡ እናንተ በውስጥ ምንም ዓይነት አሮጌ እርሾ የማይገኝባቸው አዲሶቹ  ቡሆዎች ናችሁ፡፡ እናንተ ለግብዣው የሚሆን የሰርግ ልብስን የለበሳቸሁ፤ ወደ ሙሽራው ደስታ ትገቡ ዘንድ የተጣራችሁ እንግዶች ናችሁ፡፡ እናንተ የክርስቶስን ቀንበር በመሸከም በትሕትና የምታገለግሉ ስለብዙዎች መዳን እስረኞች የሆናችሁ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ናችሁ፡፡" 
በእውን እኛ እንደተባለልን ሆነን ተገኝተናልን? ይህ ሁላችንም የምንመልሰው ጥያቄ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ሆይ እንዲህ ሆነን ለመገኘትና የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን እንትጋ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለዚህ እንድንበቃ ማስተዋሉን ያድለን አሜን!!!

No comments:

Post a Comment