በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
17/07/2009
ወዮ ይህች ከእውነተኛ ጌታ የወጣች ትምህርት እንዴት ታስፈራለች ? እርሱ ስለትንሣኤ ሕይወታችን በዐሥሩ ደናግላን መስሎ አስተማረን እንዲህም አለን፥-"በዚያን ጊዜ" ያላት ያችን የምታስፈራዋን የምጽአቱን ቀን ነው። በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች" አለን። በአሥሩ ደናግላን የተመሰልነው እኛ በጥምቀት ለክርስቶስ የታጭነው ክርስቲያኖችን ነን። ስለሆነም ጌታችን ክርስቲያን መሆናችን ብቻ እንደማያድነን እምነትን ከምግባር፥ እምነትን ከፍቅር ጋር፥ እምነትን ከጦም ከጸሎት ከስግደት ከምጽዋት ጋር አብረን አስተባብረን ይዘን የብርሃን መላእክትን መስለን ራሳችንን ከኃጢአት ጠብቀን የጌታን መምጣት በናፍቆት እንጠብቅ ዘንድ እንዲገባን ሊያስተምረን እንዲህ አለን።