Thursday, December 27, 2012

በዓለ ክብሩ ለቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/04/2005
ከዚህ በፊት በማኅበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ የተለቀቀ ጽሑፍ

ነቢዩ ዳንኤል “ዐይኖቼንም  አነሣሁ” ካለ በኋላ አስከትሎ “እነሆም በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ፡፡ አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፣ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፣ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ፡፡… ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ ኀይልም አጣሁ፡፡ የቃሉንም ድምፅ  ሰማሁ፤ የቃሉን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምደር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ” አለ፡፡(ዳን.10፡5-9)

ነቢዩ ዳንኤል እንዲህ ብሎ የተናገረው የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤልን አስፈሪ ግርማ በተመለከተ ጊዜ ነበር፡፡ የዚህ መልአክ ግርማ የአምላክን ግርማ ይመስላል፡፡ ይህን ለመረዳት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮቱ ለወንጌላዊው ዮሐንስ የተገለጠበትን መገለጥ መመልከት በቂ ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይ ስለተመለከተው የክርስቶስ ግርማ ሲናገር፡- “ከኋላዬም እንደ መለከት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅን ሰማሁ፡፡…የሰው ልጅ የሚመስልን አየሁ፤ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ የሚደርስ ልብስ የለበሰ ፣ ወገቡንም በወርቅ ዝናር የታጠቀ ነበር፡፡ ራሱና የራስ ጠጉሩም እንደ ነጭ የበግ ጠጉር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፤ ዐይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፡፡ እግሮቹም በእሳት የነጠረና የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፤ ድምፁም እንደ ብዙህ ውኃ ድምፅ ነበረ፡፡”… ባየሁትም ጊዜ ከእግሩ ሥር ወደቅሁ አንደ ሞተ ሰው ሆነሁ” አለ፡፡(ራእይ.1፡2-17) በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ቅዱስ ገብርኤል በግርማው አምላኩን እንደሚመስል አንረዳለን፡፡  የስሙም ትርጓሜ የሚያስዳው ይህን እውነታ ነው፡፡ ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ ማለት ነውና፡፡