Wednesday, January 17, 2018

በዓለ ጥምቀት


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ጥር ፲ ቀን ፳፻፲

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሰችሁ!!

የጌታችን አካሉ የሆነች የፍቅር እናት ቤተ ክርስቲያን በዛሬው እለት የእግዚአብሔር አብ ልጅ ለሆነው ለእግዚአብሔር ወልድ የታጨችበት የሙሽርነቷን ጊዜ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በድምቀት ታከብራለች፡፡ ይህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማሕፀንና ማየ ገቦው ባደረጋት የጥምቀት ውኃ በጌታዋ ያመኑትንና የመንጎቿን ልጆችን በ፵ እና በ፹ ቀናቸው በማጥመቅ የጌታዋ የአካሉ ሕዋስ በማድረግ ከሕያዋን ቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነፍሳት፣ ከበኩራት ማኅበር ጋር ማኅበርተኛ ታደርጋቸዋለች፡፡ ይህንን ከጌታዋ በሐዋርያቶቿ በኩል ተቀበለች ፡፡ በእነርሱ ስልጣንም ሰማያውያን ደናግላንን እለት እለት በኅቱም ድንግልና ትወልዳለች፡፡ ከንጉሡም ማዕድ ስሙ በሰፈረበት በምሕረት ኪዳኑ ወይም መሠዊያው ታቦቱ ላይ የተፈተተውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ትመግባቸዋለች፡፡