Wednesday, January 17, 2018

በዓለ ጥምቀት


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ጥር ፲ ቀን ፳፻፲

 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ለመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሙሉ እንኳን ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል በሰላም አደረሰችሁ!!

የጌታችን አካሉ የሆነች የፍቅር እናት ቤተ ክርስቲያን በዛሬው እለት የእግዚአብሔር አብ ልጅ ለሆነው ለእግዚአብሔር ወልድ የታጨችበት የሙሽርነቷን ጊዜ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በድምቀት ታከብራለች፡፡ ይህች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማሕፀንና ማየ ገቦው ባደረጋት የጥምቀት ውኃ በጌታዋ ያመኑትንና የመንጎቿን ልጆችን በ፵ እና በ፹ ቀናቸው በማጥመቅ የጌታዋ የአካሉ ሕዋስ በማድረግ ከሕያዋን ቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነፍሳት፣ ከበኩራት ማኅበር ጋር ማኅበርተኛ ታደርጋቸዋለች፡፡ ይህንን ከጌታዋ በሐዋርያቶቿ በኩል ተቀበለች ፡፡ በእነርሱ ስልጣንም ሰማያውያን ደናግላንን እለት እለት በኅቱም ድንግልና ትወልዳለች፡፡ ከንጉሡም ማዕድ ስሙ በሰፈረበት በምሕረት ኪዳኑ ወይም መሠዊያው ታቦቱ ላይ የተፈተተውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ትመግባቸዋለች፡፡

ግሩም የሆነው ግን ወዳጆቼ አምላክ በሦስትነቱና በአንድነቱ ሲኖር ሳለ ለእኛ ለፍጥረቱ ይህን ሕቡዕ ምሥጢር ዕውቀት እንዲሆነን ብቻ ሊገልጥልን አለመውደዱ ነው፡፡ ስለዚህ በአርያውና በአምሳሉ የፈጠረውን የሰውን ልጅ የመውደዱን ከፍታ ሊገለጥ  እግዚአብሔር አብ የሚወደውን ልጁን በፈቃዱ በሥጋ ተወልዶ የእኛ ዘመድ እንዲሆን አደረገው፡፡  በልጁም ጽንሰት የእርሱ የአብና የመንፈስ ቅዱስ ተሳትፎ ነበር፡፡ ይህ ለድንግል እናቱና ለዮሴፍ የተገለጠ ለሁሉ ይፋ ሆኖ ያልተገለጠ መገለጥ ነበር፡፡ ጌታችን ፴ ዓመት ሲሞላው ግን የብሉዩን የልጅነትና የጥምቀት ጥላዎችን ሽሮ በመንፈስ ቅዱስ የታደሰ ሰብእና በመስጠት ራሱን አካላችን ፣ ለአብ የጸጋ ልጆች በማድረግ ሁሉን ወራሽ እንድንሆን ሊያበቃን በዕደ ዮሐንስ ሊጠመቅ በባሕረ ዮርዳኖስ ተገኘ፡፡ በዚያ ሦስትነቱንና አንድነቱን ገለጠልን፡፡ በዚህ መገለጥ ውስጥም ውኃ ሕያዋንን የምትወልድ ማሕፀን ትሆን ዘንድ ከጎኑ ከፈሰሰው ውኃው ጋር አንድ አደረጋት፡፡ በእርሱ እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሕያው ሆነው እንዲኖር ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ አካሉን አካላችን በማድረግ ሰውነታችንን የአብና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ቤተመቅደስ አደረገው፡፡ እናም አስቀድሞ በጌታ ልደት ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለዮሴፍ የተገለጠው ሥላሴ በእኛም ልደት የመለኮቱ ባሕርይ ተሳታፊዎች በማድረግ በባሕረ ዮርዳኖስ ተገለጠ ሰውነታችንም የሥላሴ ቤተ መቅደሱ ሆነ፡፡ የእግዚአብሔር አንድነቱና ሦስትነቱ በባሕረ ዮርዳኖስም በእኛም ዳግም ልደት ገሃድ ሆነ፡፡ ይህ ምሥጢር በእውነት ድንቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለዕውቀት ሳይሆን ለጥቅም እግዚአብሔር ለእኛ ለሰው ልጆች በባሕረ ዮርዳኖስ ሦስትነቱና አንድነቱን መግለጡ፡፡
ስለዚህ ሥላሴ ሆይ እንወድሃለን እናከብርሃለን እናመልክሃለን ከአንተ ሌላ ሌላ አምላክ የለንም፡፡ እንዲህ እኛን ትወድደን ዘንድ እኛ ማን ነን? እንዲሁ ያለ አንዳች ምክንያት እኛን የሰው ልጆችን በመውደድህና ላትተወን ሰውነታችንን ቤተ መቅደስህ አድርገህ ስላከበርከን ሥላሴ ሆይ ዘወትር ለአንተ ባሮችህ እንሆናለን፡፡ እባክህ አምላካችን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ስምህ በእኛ ይክበርና ይመስገን ዘንድ አንተን ዘወትር ማሰብን ስጠን፤ እንደ ሴት ልጆች በመላእክት ሥርዓት እንኖርና ይህችን ዓለም ፈቃድህን ፈጻሚ እንድትሆን እናበቃት ዘንድ ኃይል ሁነን፡፡ ስም በእኛ ይመስገን መንግሥት በእኛ በልጆችህ ትገለጥ፡፡ ለዘለዐለሙ አሜን፡፡

ወገኖቼ ሆይ ከሁሉ በላይ የእርሱ መገልገያ በመሆን እኛን ለዚህ ታላቅ ክብር ያበቁንን ካህናት አባቶቻችንን እናስብ። የሥላሴን ልጅነት ሰጥተውን ከማዕዱም አቀብለውንና አክብረውን ሳለ ዘንግተናቸዋልና፡፡ ድካማቸውን ማሰብ አልተቻለንም፣ ረስተናቸዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ በጥምቀት በዓላችን አገልጋይ ካህናቱን ዲያቆናቱን የምንመለከትበት እነርሱን የምናግዝበት እንዲሆንልን ተመኘሁ፡፡
መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ ወገኖቼ

No comments:

Post a Comment