Wednesday, December 20, 2017

ሕግ ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ምንድን ነው?

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
11/04/2010
ሕግ የእግዚአብሔር ባሕርይንና ፈቃድ የምንለይበት መሣሪያ ነው፡፡ ነገር ግን ሰው በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረ ፍጥረት ስለሆነ በባሕርይው የእግዚአብሔርን ባሕርይና ፈቃድ ያውቃል፡፡ ሰው ለባሕርይው አልታዘዝ ሲል የገዛ ተፈጥሮውን ወደ ማጥፋት ይመጣል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሰው በልቡናው ወይም በተፈጥሮ ውስጥ ያኖረውን ሕግ በማጥፋቱ ፈጽሞ ጠፍቶ እንዳይቀር በጽሑፍ ሕግን ሠራለት፡፡ ይህ በጽሑፍ የተዘጋጀው ሕግ የሚያስፈልገው ሕግን ላፈረሱ ኃጥአን እንጂ ለጻድቃን አልነበረም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ሲናገር “ሰው እንደሚገባ ቢሠራበት ሕግ መልካም  እንደሆነ እናውቃለን ይኸውም ለበደለኞች ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን ….ሁሉ እንደ ተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሠራ ሲያውቅ ነው ፡፡”(1ጢሞ.1፡8-11) ይላል፡፡ ስለዚህ የጽሑፉ ሕግ የተሰጠን ለእርሱም የአፈጻጸም ሥርዓታት የተሠሩት እኛ ከልቡና ሕግ በመውጣታች ነው፡፡ ጻድቃን ግን ሕግን ሳይጠብቁ ሕግን ይፈጽማሉ፡፡ ይህም እግዚአብሔርንና ባልጀሮቻቸውን ከማፍቀራቸው የተነሣ ነው፡፡ እነርሱ የሚተጉት በትሩፋት ሥራዎች ላይ ነው ፡፡ የትሩፋት ሥራዎች የሚባሉት በምጽዋት፣ ነፍስን በማዳን፣ በንጽሕና በመመላለስ፣ እና በመሳሰሉ ተግባራት ላይ ነው፡፡ ይህንን ከፍቅር ስለሆነ የሚተገብሩት ሕግን እየፈጸሙ እንደሆነ አያስተውሉትም ፡፡ ስለዚህም ጌታችን ቅዱሳንን በምጽአት ስራብ አብልታችሁኛል ስታሰር ጠይቃችሁኛል ብሎ ሲያመሰግናቸው ጌታ ሆይ መች ተርበህ አይተንህ አበላንህ  መች ተጠምተህ አይተንህ አጠጣንህይሉታል ፡፡(ማቴ.25፡35-40) ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ግቡ እግዚአብሔር አምላኩን መምሰል ነው ለዚህም ይተጋል እንደ ትጥቅም የሚታጠቀው ፍቅረ እግዚአብሔርንና ፍቅረ ቢጽን ነው፡፡ ሰው ለፍቅር ሲገዛ ሕግጋትን አሟልቶ መፈጸም  ይችለዋል፡፡ ሕግ ወደ ፍቅር የሚያደርስ መሠላል እንጂ በራሱ ፍጻሜ አይደለም ፍጻሜው ክብር ይግባውና በእርሱ አማልክት መሰኘት ነው፡፡

ለዚህ መረዳት እንዲጠቅመን “ከእንኋት ክርስትና መጽሐፌ ላይ የቀነጨብኳትን ጽሑፍ ተጋበዙልኝ፡፡
የፍቅር ትርጉም በአፍርሃት
“በእርግጥ ተወዳጆች ሆይ ሁሉም ሕግጋትና የነቢያት ቃል በሁለቱ ሕግጋት ውስጥ የተካተቱ  ናቸው ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሕግና ነቢያት እርሱን ደስ ለማሰኘት በቂ እንዳይደሉና እነዚህን የሚጠብቁ እርሱን ለመከተል የበቁ አለመሆናቸውን ገልጾልናል ፡፡
ስለዚህም ጌታችን ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፡- “እስራኤል ሆይ ስማ አምላካችን አንድ ጌታ ነው አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትለው ናት ፡፡ ፊተኛዬቱ ትእዛዝ እቺ ናት ፡፡ ሁለተኛይቱም፡-ባልጀራህን እንደራስህ ውደድ የምትል እርሱዋን የምትመስል ይህች ናት ፡፡ ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም ፡፡”አለን ፡፡ (ማር.፲፪፥፳፰-፴፩)
ሕግና ነቢያት በውስጡ የተካተቱበትን ይህን ሕግ በምትመረምርበት ጊዜ በልባችንና በሕሊናችን ተቀብለነው ልንፈጽመው የሚገባ  ሕግ መሆኑን ትረዳዋለህ ፡፡  ወይም ቅዱስ ጳውሎስ “ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሠራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን ይኸውም ለበደለኞችና ለማይታዘዙ ለዓመፀኞች ለኃጢአተኞች ቅድስና ለሌላቸውና ለርኩሳን… ሕግ እንደተሠራ እንጂ ለጻድቅ እንዳል ተሠራ ሲታወቅ ነው ፡፡”  (፩ጢሞ.፩፡፰ ) እንዳለው ሕግና ነቢያት አስፈላጊ ሕጎች እንዳልሆኑ እንረዳለን ፡፡ ስለኃጥአን ሲባል ግን ሕግ ተሠራ ፡፡ ስለዚህም ሰው በጽድቅ የተመላለሰ እንደሆነ ሕግ አያስፈልግውም ማለት ነው ፡፡
ሕግ ባይሠራ ደግሞ የእግዚአብሔር ሥልጣን በትውልዱና እርሱ ባደረጋቸው ምልክቶች ባልታወቀ ነበር ፡፡ በአዳም መተላለፍ ምክንያት ሞት በዓለም ላይ ሠለጠነ ፡፡ ሰው ሁሉ የሞትን ሕግ ጥሰው በመነሣታቸው ምክንያት የእግዚአብሔር ሥልጣን ለሁሉ ተገለጠ ፡፡ በኖህ ዘመን በተነሡት ኃጢአተኞች ምክንያት የእግዚአብሔር ሥልጣን በውኃ ሙላቱ ምክንያት ተገለጠ ፡፡ አብርሃምም ሕግ ሳትሰጥ በፊት በጽድቅ በመመላለሱ ምክንያት በእርሱ ጽድቅ ሥራ በሰዶም ንጉሥ ተማርኮ የነበረውን ሙርኮ ለመመለስ በተነሣበት ወቅት የእግዚአብሔር ኃይል በእርሱ ተገልጦ ነበር ፡፡
ከዚያም ቀን በኋላ “በራሴ ማልሁ ይላል ይህን ነገር አድርገሃልና … በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ” አለው (ዘፍ.፳፪፥፲፮-፲፯) ፡፡ እርሱ ሕግ ሳያስገድደው የሕግን ሥራ ፈጸመ ለእርሱ የጽድቅ ሕግ አላስፈለገውም ፡፡ ይህ በልጆቹ በይስሐቅም በያዕቆብም የታየ ነው ፡፡ ምንም እንኳ እግዚአብሔር ስለ አባታቸው “ጽድቅንና ፍርድን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ የሚነሡትን እንዲያዝ አውቃለሁና”ብሎ አንደመሰከረለት  ጽድቅና ፍርድን እንዲያደርጉ ልጆቹን እንዲያዛቸው አውቃለሁ” ቢልም ፡፡የጽድቅ ሕግ ሳይሰጣቸው ሕግን ይጠብቁ ነበር ፡፡
ዮሴፍ ለእመቤቱ ለጲጥፋራ ሚስት የኃጢአት ፈቃድ ባለመታዘዝ ጽድቅን ፈጸመ ፡፡ እርሱ “ እንዴት በእግዚአብሔር  ፊት ኃጢአትን እሠራለሁ”(ዘፍ.፴፱፥፲) አለ ፡፡ ሙሴም ሕግ ሳይሰጠው በሕግ የተሰጠውን ጽድቅ ስለጠበቀ የፈርዖን ልጅ መባልን እቢ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ሕግን ለሕዝቡ ይሰጥ ዘንድ በእግዚብሔር ዘንድ የተገባ ሆነ ፡፡
እነዚህ ሁሉ በሕግ የተሰጠው የጽድቅ ሕግ ሳያስገድዳቸው በራሳቸው ፈቃደኝነት ሕግን የፈጸሙ አባቶች ናቸው ፡፡…. ተወዳጆች ሆይ ይህን ልብ በሉ ሕግ እኛን ጽድቅን እንድንፈጽም የማስገደድ አቅም የለውም ብዬ ጽፌላችኋለሁና ፡፡ ጽድቅን በፈቃደኝነት የሚፈጽም ሰው እርሱ ከትእዛዛትና ከሕግ አንዲሁም ከነቢያት ቃል በላይ ሆነ ፡፡



ጌታችን መድኃኒታችን ያስተማረው “ከእነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲህ የሚያስተምር ማንም ቢሆን በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል…”(ማቴ.፭፥፲፯) ያለው ትምህርት ትክክለኛ ትምህርት ነው ነገር ግን እነዚህ ሕግጋት በሁለቱ የተካተቱ አድርጎአቸዋል ፤ ምክንያቱም ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ ፡፡…”

No comments:

Post a Comment