ከምዕራፍ አንድ ላይ የተቀነጨቡ
ምሥጢረ ጥምቀትና ምሥጢረ ቁርባንን አስመልክቶ በሶርያ ቅዱሳን አባቶች በጥቂቱ
እነዚህ የሶርያ ቅዱሳን አባቶች ይህን ፅንሰ አሳብ በማዳበር ብዙ የጻፉ ሲሆኑ ባለራዕይው ዮሴፍ የተባለው ቅዱስ አንድ ክርስቲያን በውስጡ ላደረው መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ሲታዘዝ በሰውነቱ የሚከሰቱ ለውጦችን ደረጃ በደረጃ ጽፎልን እናገኛለን ፡፡
……..“አንድ ክርስቲያን በሰውነቱ ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ ሥራ መጀመሩን የሚረዳው በልቡ ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር እንደ እሳት መቀጣጠል ሲጀምር ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ዓለማትን እንደ ፈጠረ ወደ ማስተዋል ይመጣል፡፡ ከዚህም ስለእግዚአብሔር ፍቅር ሲባል ለእግዚአብሔር መለየትና የትህርምት ሕይወትን ወደ መምረጥ ይመጣል፡፡ እነዚህ ሁለቱ የመልካም ሥነምግባራት እናቶች ናቸው፡፡ ወንድሜ ሆይ ሁለተኛው መንፈስ ቅዱስ በአንተ ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምትገነዘበው እውነተኛ የሆነው ትሕትና በአንተ ሲወለድ ነው፡፡ እንዲህ ስልህ ለታይታይ በሥጋ የሚገለጠውን ትሕትና ማለቴ ግን አይደለም ፡፡ በእኛ ባደረው መንፈስ ቅዱስ ድንቅ የሆነ ሥራ እየተፈጸመ ነገር ግን ራሳችንን እንደትቢያና አመድ የተናቅን አድርገን የምንቆጥርና ከሰው ተርታ የማንመደብ አድርገን የምንመለከት ከሆነ በእርግጥ እውነተኛይቱትሕትና በእኛ ውስጥ ተወልዳለች ፡፡ (መዝ.፳፩፥፮) ይህ ትሕትና ራስን በእግዚአብሔር ፊት በመመልከት የሚወለድ ትሕትና ነው፡፡
በዚህ ዓይነት ትሕትና ውስጥ የሚገኝ ሰው ሰዎች ሁሉ ቅዱሳንና ከእርሱ ይልቅ የከበሩ እንደሆኑ አድርጎ ያስባል፡፡ በእርሱ አእምሮ ውስጥ እገሌ መጥፎ ነው እገሌ ደግሞ ደግ ነው የሚል አስተሳሰብ የለም፡፡ ይህ ፍትሐዊ ነው ያ ግን ፍትሐዊ ውሳኔ አይደለም ብሎ በማንም ላይ ጣቱን አይቀስርም፡፡ ይህን ከመሰለ ትሕትናም ሰላማዊነት፣ የዋሃት፣ትዕግሥት ይወለዳሉ ፡፡
ሦስተኛው መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሥራ የመሥራቱ ምልክቱ የእግዚአብሔር አርዓያ ላለው ለሰው ልጅ ሁሉ እጅግ ርኅሩኃን መሆንን ገንዘባችን ያደረግን ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህም ለእነርሱ ካለን ፍቅርና አዘኔታ የተነሣ እንባችን ጉንጫችንን ሞልቶ ይፈሳል፡፡ የሰው ፍቅር በውስጣችን በመቀጣጠሉ ምክንያት ሰውን ሁሉ እቅፍ አድርገን ጉንጩን እንስመው ዘንድ እንወዳለን፡፡ ሰዎችን ባሰብናቸው ቁጥር ለእነርሱ ያለህ ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ ይበልጥ ተቀጣጥሎ ይንቀለቀላል፡፡ ከዚህም ለሰዎች በጎ ማሰብንና ተቆርቋሪት ይወለዳል ፡፡ ስለዚህም ሰውን በንግግር ላለማሳዘን ቃልን መርጦ መጠቀምን እንጀምራለን ፡፡ በልባችን እንኳ ስለሰው ልጆች ክፉ ማሰብን አንፈቅድም፡፡ ነገር ግን ለሰው ሁሉ በልባችንም በተግባራችንም መልካምን ለማድረግ እንተጋለን ፡፡
መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምናረጋግጥበት ዐራተኛው ምልክት እውነተኛው እግዚአብሔርን መውደድ በሕሊናችን ያደረ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት እግዚአብሔርን ከማሰብ አንዲት ቅጽበት እንኳ ማቋረጥ አይቻለንም፡፡ ይህ የውስጠኛውን የልባችንን በር የሚከፍተው ቁልፍ ነው፡፡ በዚያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ እልፍኙም ግሩም በሆነው መለኮታዊ ብርሃን ተሞልቶ ከገጽታውም የክብሩ ብርሃን ሲፈልቅ እናያለን፡፡ እግዚአብሔርን ከመውደድ የማይታየውን አምላክ የምናይበት እምነት ይወለዳል፡፡ ይህ እምነት ከአእምሮአችን በላይ የሆነ መረዳትን ስለሚሰጠን በወረቀት ላይ ማስፈር ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ዓይነት እምነትን ቅዱስ ጳውሎስ “ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ብሎ ይገልጸዋል፡፡ ይህ እምነት በሥጋ ዐይናችን የማንረዳው ነገር ግን ለነፍሳችን ዐይኖች በግልጽ የሚታወቅና የሚረዳ ነው፡፡
አምስተኛው መንፈስ ቅዱስ በእኛ ሰውነት ውስጥ ሥራ መሥራቱን የምንረዳው አእምሮአችን ፍጹም ብሩህ በሆነ የማስተዋል ብርሃን ሲሞላ ነው ፡፡ በልባችን ጠፈር ላይ የሰንጴር ድንጋይን የመሰለ ሰማይ ተዘርግቶ ልዩ ልዩ ሕብረ ቀለማት ያሉዋቸው ብርሃናት ሲፍለቀለቁ ይታዩናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ማራኪ የሆኑ ብርሃናት በልቡናችን የሚፍለቀለቁት ሥላሴ በልቡናችን የባሕርይ የሆነውን ብርሃን ሲኦያበራልን ነው(እውቀቱን ሲገልጥልን ነው) ፡፡
በሥላሴ ብርሃን እርዳታ የሚኖረን ማስተዋል ፍጥረታዊውን ዓለም በጥልቀት እንድናውቀውና እንድንረዳው የሚያደርገን ሲሆን ከዚህ አልፈን መንፈሳዊውን ዓለምንም በጥልቀት እንድንፈትሸው ያበቃናል፡፡ በመቀጠልም ስለእግዚአብሔር ቅን ፍርድና መግቦት ወደ ማወቅ እንመጣለን፡፡ ይህ በሂደት ከፍ ከፍ እንድንል በማድርግ ከክርስቶስ የክብሩ ብርሃን(መንፈስ ቅዱስን ልብ ማድረግ)ተካፋዮች እንድንሆን ያበቃናል፡፡ ከዚህ ቅዱስና ግሩም ከሆነው እይታ ስትደርስ እጅግ ውብ አድርጎ በፈጠራቸው ዓለማት መደነቅ እንጀምራለን፡፡
ከእነርሱ የምታገኘው ማስተዋል እጅግ ታላቅ ይሆንልሃል ፡፡ በዚህ ድንቅ ከሆነው ከፍታ ላይ ስለሁለቱም ዓለማት መንፈሳዊው እውቀት እንደ ጅረት ከአንደበትህ ይፈሳል ፤ የሚመጣውን ዓለም በዚህ ዓለም ሳለን ማጣጣም ትጀምራለህ ፡፡ እጅግ ውብ የሆነውን ከመላአክት ማስተዋል የሚልቀውን ማስተዋል ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡ የመላእክትን ደስታቸውን፣ ምስጋናቸውን ፣ ክብራቸውን ፣ ዝማሬአቸውን ቅኔአቸውን እንሰማለን፡፡ መላእክትን ከእነማዕረጋቸው፣ እርስ በእርሳቸውም ስላላቸው ኅብረት ወደ ማወቅ እንመጣለን፡፡ ቅዱሳን ነፍሳትን ለመመልከት እንበቃለን ፣ ገነትን(ክርስቶስን) ማየት ከሕይወት ዛፍ መመገብን(በፍቅሩ መኖርን) ፣ ከቅዱሳን ነፍሳትና መላእክት ጋር መነጋገርንና ከእነዚህም በላይ የሆኑ ሰማያዊ ትዕይንቶችን መመለከትን ገንዘባችን እናደርጋለን፡፡”
ከላይ የጠቀስናቸው ምልክቶች በጥምቀት በሰውነታችን ያደረው መንፈስ ቅዱስ ሥራ እየሠራ ስለመሆኑ የምናረጋግጥባቸው ምልክቶች ናቸው ፡፡……
ስለ ቅዱስ ቁርባን የሶርያ ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ
…..በሥጋ ዐይናችን ስንመለከታቸው ሕብስትና ወይን ሆነው ነው፤ ነገር ግን በመረዳት ስንመለከታቸው የአምላክ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ክርስቶስን በመረዳት ሳይሆን በሥጋ ዐይናቸው አይሁድ በመመልከታቸው ምክንያት ሰው መሆኑ እንጂ አምላክ መሆኑን እንዳልተረዱት እንዲሁ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በሥጋዊ ዐይናችን ስንመለከተው ሕብስትና ወይን ሆኖ ይታየናል ፤ ነገር ግን በመረዳት ስንመለከተው አማናዊው የእርሱ ሥጋና ደም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሕብስቱንና ወይኑን ቅዱስ ሥጋውና ቅዱስ ደሙ በማድረጉ የተነሣ የመንፈስ ቅዱስ ሥጋና ደም ነው እንደማንል እንዲሁ በቅድስት ድንግል ማርያምም የሆነው ይህ ነው፡፡ ምንም እንኳ እናታችን ጌታችንን መድኃኒታችንን በሥጋ ስትፀንሰው በመንፈስ ቅዱስ ግብር ቢሆንም በእርሱዋ ሰው የሆነው ግን እግዚአብሔር ቃል ነበር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡” እንዲል መንፈስ ቅዱስ ለፅንሰቱ ምክንያት ቢሆንም ሥጋን ተዋሕዶ የተወለደው ግን እግዚአብሔር ቃል ነው ፡፡ ስለዚህም በቅድስት ድንግል ማርያም እንደተፈጸመው እንዲሁ በሕብስቱና በወይኑ ሆኖአል ፡፡ ምንም እንኳ ይህን ምሥጢር በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አብ የተሰጠን ቢሆንም በሥርዐተ ቅዳሴ ጊዜ ሕብስቱን በመጸለል የጌታ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙ የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው ፡፡”….
https://www.amazon.com/Enehwatkirstina-Amharic-Shemelis-Mergia/dp/1981444610/ref=sr_1_5?s=baby-products&ie=UTF8&qid=1513612355&sr=8-5&keywords=Mergia
ይህን መፅሀፍህን በአንዱ የአሜሪካ ከተማ በሚገኘው የማህበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መጻሕፍት መሸጫ ሱቅ ገዝቼ አነበብኩት። እጅግ ድንቅ የሆነ የእለት ተእለት የሕይወት መመሪያዬ ከሆነ ቆዬ። መምህር ሽመልስ ቅዱስ እግዚአብሔር ፀጋውን አብዝቶ ይስጥህ።
ReplyDeleteውድ ወንድሜ አንብበህ አስተያየትህን ስለሰጠኸኝ ስለጻፍክልኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ ይቅርታህን ዘግይቼ መልስ በመስጠቴ ወንድሜ
ReplyDelete