Wednesday, August 22, 2012

ትንሣኤሃ ለቅድስት ድንግል ማርያም



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/12/2004
በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሲገለጥ በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ በማደር የምስክሩን ድንኳን በክብሩ ደመና ይከድነው ነበር፡፡(ዘጸአ.40፡34-38) ንጉሥ ሰሎሞንም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ሠርቶ ከፈጸመና የቃል ኪዳኗን ታቦት ካስገባ በኋላ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ላይ በማረፍ መቅደሱን በክብሩ ደመና ከድኖት ነበር፡፡(2ዜና.7፡2-4) እነዚህ የእናታችን የቅድሰት ድንግል ማርያምና የእኛ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ሰውን የሚወድ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ  በመተላለፉ ምክንያት ተሰነካክሎ ወድቆ እንዲቀር ስላልወደደ እግዚአብሔር ቃል በራሱና በአባቱ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጣ፡፡ ሰብእናችንንም በራሱ ቀድሶና አንጽቶ ከራሱ ጋር ለማዋሐድና እኛን ቤተመቅደሱ ለማሰኘት ቅድስት እናታችንን ማደሪያ ታቦቱ ትሆን ዘንድ መረጣት፡፡ ከእርሱዋም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ በመንሳት ተፀንሶ ተወለደ፡፡ በዚህም በነቢዩ አሞጽ አድሮ“በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ”(አሞ.9፡11) ብሎ የተናገረውን ቃል ከዳዊት ዘር ከሆነች ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድ ድንኳን የተባለችውን ሰብእናችንን አከበራት፡፡