Monday, June 5, 2023

የእግዚአብሔር ፍቅሩ

 ቀን/28/09/2015

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

ሰው እግዚአብሔርን መውደድ በውስጡ ከሌለ ሰውን መውደዱ ከራስ ወዳድነቱ የመነጨ ይሆንበታል፡፡ ራሱን የሚወድ ሰው ደግሞ የራሱ ነገር ሲነካ ሌላውን ወደ መጥላት ይመጣል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን ፍቅር ገንዘቡ ስለሚያደርግ ሚዛናዊ ሆኖ፣ ፍትሕ ሳያጓድል ሁሉን ይወዳል፡፡ ርኅራኄ ለሚያስፈልገው ርኅራኄውን፣ ትዕግሥት ለሚያስፈልገው ትዕግሥትን፣ ሊታዘንለት ለሚገባው ሐዘኔታን፣ እርሱ የሚያስተዳደረው ወይም ከእርሱ ሥር ከሆነ ደግሞ እየቀጣ ወደ ሰዋዊው ባሕርዩ ወይም ክርስቶስን ወደ መምሰል ይመልሰዋል፡፡ ይህም እግዚአብሔርን መምሰል ይባላል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ግን እግዚአብሔር ፍቅሩን አውቀን በፍቅሩ ኖረን ኃጢአትን ተጸይፈን እንደውም ከኅሊናችን ከነመታሰቡም ዘንግተን እንመላለስለት ዘንድ ይፈልጋል፡፡ ለእርሱ የሰው ጥፋቱ ሳይሆን መዳኑ ያስደስተዋል፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ልጆች እንዳሉት አባት ፍቅሩ የተከፋፈለ አይደለም፡፡ ለሁሉም አባት ነው፡፡

እርሱ እጅግ ጨካኝ ለሆነው የንስሐ ዕድሜን በመስጠት፣ በመታገሥ፣ በመቅጣት ፍቅሩን ሲያሳየው፣ ትሑታኑን ከደረቱ አስጠግቶ ምስጢሩን በመግለጥ ከቃሉ በመመገብ፣ መለኮታዊ ጠረኑንም በማሻተት፣ እንዲዳስሰው በመፍቀድ ፍቅሩን ይገልጥለታል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትሑት ሰው ፍቁረ እግዚእ ይባላል፡፡ እርሱ ለጨካኙም ለትሑትም ያለው ፍቅር ግን እኩል ነው፡፡ ፍቅሩን አበላልጦ አይሰጥም፡፡ አቀፈውም ቀጣውም፤ አደኸም አከበረም በሁሉም የሚገልጠውና የገለጠው ፍቅሩን ነው፡፡ የዚህን ፍቅር አጠቃቀም ማወቅ ግን ጥበብ ነው፡፡

ለእኛ ፍቅሩን በገለጠበት መንገድ እርሱን ማመስገን መቻላችን ማስተዋል ወይም ጥበብ ነው፡፡ በዚህ ማስተዋል ውስጥ ካለን ለእኛ ባሳየን ርኅራኄው የፍቅሩን ብርሃን አሳይቶናልና በፍቅሩ ለመኖሩ ፈቃዱን ፈቃዳችን ለማድረግ እንተጋለን፡፡ ከቀደመው የኃጢአት ምልልሳችን እንወጣለን፤ በፊቱም ራሳችንን አዋርደን የማንጠቅም  ሆነን ሳለ አንተ ግን ራራኅልን፣ ወደ አንተም ስበህ አቀረብከን እንለዋለን፤ ፍቅሩም በነፍሳችን እንደ እሳት ትቀጣጠላለች፡፡

እግዚአብሔር በባሕርዩ የማይለወጥ ነው የምንል ከሆነ ፍቅሩም አንዱ የባሕርዩ መገለጫ በመሆኑ ፍቅሩ ተለዋዋጭና አንዱን ከአንዱ የሚያበላልጥ ነው ብለን ልንገነዘብ አይገባንም፡፡  ምክንያቱም ወንጌላዊው እንዳለው እግዚአብሔር ፍቅር ነውና፡፡

እግዚአብሔር እኛን ከመውደዱ የተነሣ እንደሌሎች ፍጥረታት የክብሩና የሕልውናው መገለጫ አድርጎ ብቻ አልፈጠረንም፡፡ ማደሪያው መቅደሱ አድርጎ ፈጠረን እንጂ፡፡ እርሱን ፈጽሞ እንድንመስለውም ለሌሎች ፍጥረታት ያልሰጠውን ነፃ ፈቃድ ለእኛ ሰጠን፡፡ አዎን ለመላእክት ነፃ ፈቃድን ሰጥቶአቸዋል፡፡ አዋቂ አድርጎአቸዋልና ከእርሱም ከእርሱ ውጭ መኖርን ምርጫ አድርጎ ሰጥአቸዋል፡፡ ቢሆንም ቢወድቁ ሁለተኛ የንስሐ ዕድልን አልሰጣቸውም፡፡ ለሰው ልጆች ግን እንዲህ አይደለም፡፡ በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮታልና ሰው ፈቃዱን ይጠቀም ዘንድ አዋቂ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ እርሱም ከእግዚአብሔር መለየትን መረጠ፤ ይህም በሥጋው ላይ ድካምን ሕመምን አመጣበት ነፍሱም ለሰይጣን አጥር እንደሌለው ቤት ሆኖ ተመቸው፡፡

እንዲያም ሆኖ የሥጋው ውድቀቱ በገነት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ሕይወት ዋጋ አሳየው፤ ንስሐ ገባ፤ እግዚአብሔር ቃልም ሁለተኛው አዳም በመሆን በአዳም ላይ የፈረደውን የራሱን ፍርድ ተቀበሎ ከቀድሞው ይልቅ ረቂቅ ወደ ሆነው መቅደስ በሥጋው መጋረጃ በኩል አገባው፡፡ (ዕብ. 10:19-20) መቅደሱም እርሱ ነው፡፡ የገባነውም ወደ እርሱ ነው፤ እርሱን መዋሐድ ወደ መቅደሱ መግባት ነውና፡፡ በእርሱ ወደ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ስለምንገባ ቅድስተ ቅዱሳን እንሰኛለን፡፡ እርሱ በእኛ ውስጥ በመሆኑ ደግሞ ሰውነታችን መቅደስ እርሱ ቅድስተ ቅዱሳን ተሰኝቶአል፡፡ ይህ ተዋሕዶን ወደ መረዳት ስንመጣ የምንገነዘበው ነው፡፡ ስለዚህ ተዋሕዶ መናገርም ከመረዳት በላይ ነው፤ ቢሆንም ይህ የፍቅሩን መጠን አልባነት ያሳየናል፡፡ በዚህ መቅደስ ውስጥ ቅዱሳን ፍጥረታዊ ያልሆነውን ብርሃን ለብሰው ይኖራሉ፡፡ በክርስቶስ አንዱ የአንዱ የአካል ሕዋስ ሆኖአል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ዕውቀት እርስ በእርሳቸው ፍጹም ይተዋወቃሉ፡፡ ስለ እኛም ያላቸው ፍቅር የአምላክን ፍቅር ይመስላል፡፡ የጊዜና የቦታ ገደብ የለባቸውም፡፡ ስለእኛም ወደ አምላክ ይቃትታሉ፡፡ እኛ ግን ብናይ ሰውን ጣራችንም ሰው ሆኖአልና አንተን መመልከት ተከለክልን፡፡ በገዛ ፈቃዳችን እንደ እኛ ፍጡርና ፍጥረታዊ ለሆነ አስተሳሰብ ቦታ ሰጥተን በድንቁርና ጨለማ ውስጥ ወድቀን ተሰነካከልን፡፡ እንደ ጥንቱ ወደ አንተ ማንጋጠጥን ተውን፡፡

አቤቱ አምላካችን ሆይ ከዚህ ዕውር ድንብር ጉዞ የምታወጣን ግን መቼ ነው? አእምሮአችንንስ በመንፈስ ቅዱስ ብሩህ የምታደርገልንስ መቼ ነው? ኃይልህንስ የምታላብሰን መቼ ነው? ክፋትንና ጭካኔን ተላብሰው ጨለማውን ደርበው ጨለማም ወርሶአቸውና ተጭኖአቸው ከአውሬ ከፍተው ደምን እንደ ዲያብሎስ ተጠምተው የሚቅበዘበዙትን ወደ አእምሮአቸው የምትመልሳቸው መቼ  ነው? እባክህ አምላኬ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ተመልከት ራራልንም ፍቅርህም ወደ ድኅነት እንዲመራን ዓይነ ልቡናችንን አብራልን፤ ቢሆንም ግን ካንተ ፍቅር ጉድለት የለም፤ አቤቱ ስለ እኛ መዳን ስትል እባክህ ኃይልህን ግለጥ፤ ለእኛም ራራልን፤ ከአንተ በላይ ብርቱ ማን አለ? ፍጥረትን ከመኖር ወደ አለመኖር ያመጣኽ አንተ ነህና፤ በአንተ ዘንድ የሰው ልጅ ኃይሉ ምንድን ነው? ብርቱ የሆኑ መላእክትም በፊትህ የሚርዱ ናቸው፤ ሁሉም በአንተ ዘንድ እንደ ኢምንት ናቸው፡፡ ስለምን ታዲያህ ዘነጋኸን ለመከራም አሳልፈህ ሰጠኸን አቤቱ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን አስብ ራራልንም፡፡

Thursday, May 7, 2020

አማልክት ከምድር ሲወጡ አየን


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
29/08/2012
አዲስ አበባ
አምላኬ ሆይ ዛሬ ለጸሎቴ መልስን ስለሰጠኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ አውቃለሁ አንተ ርኅሩኅ አምላክ ነህ እንደ ፈቃድህ የሆነን ጸሎት የሚያቀርብን ሰው ትሰማዋለህ፡፡ ነገር ግን ጌታ ሆይ ዛሬ ምሽቱን በምንጣፌ ላይ ዕንቅልፍ ሳይጥለኝ ግን ጋደም ብዬ ወደ መቃብር ሥጋህ መውረዱን አሰብሁ፡፡ ነፍስ ከሥጋ መቃብር ከገባች ፈጥና ትወጣለች እንጂ ከእርሱ ጋር ምድራዊው መቃብር ውስጥ አትገባም፡፡ እንዲያ ቢሆን ግን ሰው ከነሕይወቱ ተቀብሮአል ይባላል እንጂ ነፍስ ወደ መቃብር ወረደች አትባልም፡፡ እንዲያም ቢሆን ሥጋ በነፍስ ኃይል በምድር ልብ ውስጥ መተንፈስ አትችልምና ነፍስ ፈጥና ሥጋን ትለያታለች፡፡ ነፍስም በዝግ መቃብር ሥጋን ተለይታ በአዳም ላይ የተፈረደውን ፍርድ ተቀብላ ወደ ሲኦል ትወርዳለች፡፡ እንዲህ ስል ከክርስቶስ ትንሣኤ በፊት ያለውን ጊዜ መናገሬ ነው፡፡  ጌታችን ግን ነፍሱን ከሥጋው በፈቃዱ ከለያት በኋላ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወረደ፡፡ በምድር በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት ተወስኖ በግዘፍ ሥጋ ለፍጥረት ሁሉ እንደተገለጠ በነፍሱም ወደ ሲኦል በመውረድ በመጠነ ነፍስ በሲኦል ለነበሩ ነፍሳት ሁሉ ተገለጠ፡፡  “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ በጌትነቱ ታያቸው፤ ነፍሳት ሁሉ በእርሱ አርአያና አምሳል ተፈጥረዋልና ጌታቸውን ለዩት “ከመንፈስህ ጋራ ብለው” እንደ ዮሐንስ መጥምቅ በደስታ ሰገዱለት፡፡ እነርሱም በቀኝ በኩል ከተሰቀለው ወንበዴ ጋር ወደ ገነት ከጌታ ጋር ገቡ፡፡

Monday, April 20, 2020

የልቡና ትንሣኤ - ወደ ነፍስ ትንሣኤ - የነፍስ ትንሣኤ - ወደ ሥጋና ለነፍስ ትንሣኤ

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
12/08/2012
የልቡና ትንሣኤ ስለ እርሱ ማወቅን፣ መረዳትን፣ ማመንንና መቀበልን ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት ከውኃና ከመንፈስ ተወልጄ የእግዚአብሔር ልጅነትን አግኝቻለሁ፤ አሁን የምኖረው ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣው ከክርስቶስ ጋር በተዋሕዶ ነው፤ አሁን ከሰማያውያን ጋር ኅብረትን ፈጥሬአለሁ፤ ከአእላፍት ቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳት ነፍሳት ጋር አንድ ጉባኤ  ሆኜአለሁ፤ ምንም እንኳ በምድር ብኖር በሰማያዊ ሥፍራ ነኝ ብሎ ማወቅ፣ መረዳት፣ ማመን፣ መቀበል ማለት ነው፡፡ ይህን ማወቁ፣ መረዳቱ፣ ማመኑና መቀበሉ ከሌለን ባልታደሰው በቀበርነው በአሮጌው ማንነታችን ዕውር ድንብራችንን መጓዛችን እንቀጥላለን፡፡ ያኔ የሥጋ ሞት ያስፈራናል፣ ዕለታዊው ነገር ያስጨንቀናል፣ ዘለዓለም የምኖር ይመስለናል፣ በመብል በመጠጥ ደስታን ለማግኘት እንተጋለን፣ የእግዚአብሔርን ሕልውና ትርክት ይመስለናል እንጂ አናምንበትም፡፡ እነዚህ የልቡናን ትንሣኤ በማጣታችን በእኛ ላይ የሚሰለጥኑብን ናቸው፡፡ ነገር ግን የልቡናን ትንሣኤ ገንዘብ ስናደርግ ያለፈው የጨለማ ጉዞ፣ ያለማወቅ ጉዞ፣ የሥጋ ባርነት ጉዞአችን ሁሉ ትዝ እያሉን ይቆጩናል፡፡ ከፊት ለፊታችን ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀን እንረዳለን፡፡ ገና መድረስ ካለብን ከፍታና መረዳት እንዳልደረስን፣ ሥጋችን የክርስቶስ ሥጋ ሆኖ በጥምቀት መለወጡን እንዳልተረዳነው ወደዚህም መረዳት ለመድረስ መትጋት እንዳለብን፣ ሕሊናችን ሁሌም ይህን  አሮጌውን ሰዋችንን ማለትም እንደ ሥጋ ፈቃድ መመላለሳችንን ገፍፈን እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንድንመላለስ እንዲያተጋን ማሳሰብን ገንዘብ እናደርጋለን፣ የክርስቶስ አካል የሆነውን ሥጋችንን ባሕርይ ለማወቅ እንተጋለን፡፡ በአጠቃላይ ወደ ነፍስ ትንሣኤ እንመጣለን፡፡