Thursday, August 9, 2012

የቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና (የመጨረሻ ክፍል)



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/12/2004
ካለፈው የቀጠለ....
1.    በኩር (first born)
ሄልፊደስ እንደሚያስበው በኩር የሚለው ቃል ተከታዮች እንዳሉት የሚያሳይ ቃል ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን በኩር የሚለው ቃል ትርጉሙ የእናቱን ማኅፀን መጀመሪያ የከፈተ ማለት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ተከታይ ይኑረውም አይኑረውም የእናቱን ማኅፀን ለመጀመሪያ ጊዜ የከፈተ ሁሉ በኩር ይባላል ፡፡ ቃሉም ለዚህ ብቻ የሚያገለግል ነው እንጂ በኩር ለመባል የግድ ተከታይ ያስፈልገዋል የሚል ትርጉም የሚሰጠን አይደለም፡፡
ቅዱስ ጀሮም ለሄልፊደስ ሲመልስለት “Every only begotten son is a first born son, but not every first born is Only Begotten. But first born understood not only one who is succeeded by on others. By one who has had no predecessor” “ብቸኛ ልጅ ሁሉ የበኩር ልጅ ነው ፤ በኩር ሁሉ ግን ብቸኛ ልጅ ነው አንለውም ነገር ግን እኛ እንደምንረዳው በኩር የሚለው ቃል ተከታዮች ላሉት ብቻ ሳይሆን ተከታዮች ለሌሉትም የሚያገለግል ቃል ነው” ብሏል ፡፡ ለምሳሌ “ከሰው ወይም ከእንስሳ ቢሆን ለእግዚአብሔር ከሚያቀርቡት ሥጋ ሁሉ ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ ለአንተ ይሆናል ነገር ግን የሰውን በኩራት ፈጽሞ ትቤዠዋለህ” ዘኁ.18፥15-16 የሚለው ኃይለ ቃል የሚያስረዳን ማኅፀን የሚከፍት ሁሉ (ተከታዮች ይኑሩትም አይኑሩትም) ለአሮን እንደተሰጠ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በኩር ማለት እነ ሄልፊደስ እንደሚሉት ሳይሆን ለአንድ ለተወሰነ ድርጊት ብቻ የተሰጠ ቃል መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ እርሱም የእናቱን ማኅፀን መጀመሪያ የከፈተ ማለት ነው ፡፡ /ዘጸ.13፥2/
ከላይ ለማስረጃነት የጠቀስናቸው ጥቅሶች ስለበኩር የሚናገሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ሄልፊደስ አስተሳሰብ በኩር የተባሉት ተከታይ ያሏቸው ብቻ ናቸው የምንል ከሆነ ተከታይ የሌሏቸው በኩር አይባሉም እያለን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ታላቅ ስህተት ይመራናል ፡፡ ለምሳሌ  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድንግል ማርያም የበኩር ልጅ ነው፡፡ ነገር ግን በኩር ለመባልም ተከታይ አላስፈለገውም፡፡ ስለዚህም በስምንት ቀን ወደ ቤተ ግዝረት በአርባ ቀኑ ደግሞ “እንደ ሙሴ ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ በጌታ ሕግ የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደተጻፈ” ሉቃ.2፥22-24 እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተመቅደስ ይዛው ወስዳዋለች፡፡

 በተጨማሪም በኩር ማለት ከወንድሞቹና ከእኅቶቹ ታላቅ ማለት ከሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ የባሕርይው የበኩር ልጁ ነውና ስለዚህም ተከታዮች አሉት ማለታችን ነውን? እንዲህ ከሆነ ደግሞ ብዙ አማልክት አሉ ወደ ማለት ያመጣናል ፡፡ ይህ ደግሞ ፈጽሞ ክህደት ነው፡፡ በኩር የሚባለው ተከታዮች ያሉት ነው የምንል ከሆነ ስለጌታችን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” /ዮሐ.3፥16/ ብሎ የተናገረው ቃልን ውሸት እናሰኘዋለን ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “በኩርን ወደ ዓለም ሲያገባ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ” /ዕብ.2፥6/ ብሎ የመሰከረለትን ዋጋ ያሳጣዋል፡፡ ስለዚህም በኩር ስንል ሄልፊደስና ገብረአበሮቹ እንደሚሉት ሳይሆን የእናቱን ማኅፀን የከፈተ ሁሉ በኩር እንደሚባል መረዳት እንችላለን፡፡
 ቅዱስ ጀሮም ሄልፊደስንና ግብረአበሮቹን እንዲህ ይላቸዋል “እስቲ ንገሩኝ በአጥፊው የጠፉ እናንተ በኩር ያላችኋቸው ብቻ ናቸውን ወይስ ሌሎችንም ብቸኞችም  ይኖሩ ይሆን ? ወንድም ያላቸውን በኩራን ካልን ወንድም /ተከታይ/ የሌላቸው ተርፈዋል ማለት ነው፡፡ እውነታው ግን “እግዚአብሔር ከዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኩር ጀምሮ እስከ ውኃ ቀጇ ምርኮኛ በኩር ድረስ በግብፅ ምድር በኩራንን ሁሉ … መታ”/ዘጸ.12፥29/ የሚል ከሆነ ትእዛዝ ፈጻሚው መልአክ ተሳስቶአል ማለታችን ነው ፡፡ እንዲህ ካልሆነ ደግሞ መጽሐፍ እንደሚያስረዳን የበኩር ልጅ ማለት የእናቱን ማኅፀን መጀመሪያ የከፈተ ብቻ ማለት እንደሆነ ልንረዳው ይገባናል” ብሏል፡፡

2.   እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም
እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም የሚለውን ኃይለ ቃል በመያዝ ሄልፊደስ “እስከ” የሚለው ቃል የሚያሳየን የተወሰነ የተቆረጠ ሰዓትን ነው ፤ ስለዚህም ድንግል ማርያም ጌታን ከወለደች በኋላ ዮሴፍ አውቋታል ብሎ ይከራከራል፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ሄልፊደስ እንደሚለው ለተወሰነ ለተቆረጠ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ላለው ነገር ሁሉ ጭምር “እስከ” የሚለውን ቃል እንደሚጠቀም ከታች የተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫዎች መመልከት ይቻላል ፡፡

ሀ. “ከዐርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ ቁራንም ሰደደው እርሱም ወጣ ውኃም ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር፡፡ /ዘፍ.8፥6/ እንዲህ ሲባል ከደረቀ በኋላ ቁራው መብረሩን አቁሟል ማለት ነውን? አይደለም ፈጽሞ ወደ ኖኅ አልተመለሰም ለማለት ተፈልጎ እንዲህ ተባለ እንጂ፡፡
ለ. “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ አስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለው” /ኢሳ.46፥4/ሲል ከሽምግልና በኋላ እሱ ገዢአችን አይደለምን? ከሽምግልናስ በኋላ ሌላ አምላክ ይሸከመናልን ?  አይደለም ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው እንጂ፡፡
ሐ. “እነሆ የባሪያዎች ዐይኖች ወደ ጌታቸው እጅ እንደሆነ የባሪያቱም ዐይን ወደ እመቤቱ እጅ እንደሆነ እንዲሁ እስኪምረን ድረስ ዐይናችን ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ /መዝ.122፥2/ ማለቱ ምሕረትን ካገኘን በኋላ እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ እንተዋለን ማለት ነውን? አይደለም፤ “ዐይኖቼ ለማዳንህ ለጽድቅህ ቃል ፈዘዙ” እንዲል /መዝ.118፥123/  ምሕረትንም አግኝተን ዐይናችን ሁል ጊዜም ወደ እርሱ እናነሣለን ፡፡
መ. “በዘመኑ ጽድቅ ያብባል፥ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው” ሲል ጨረቃ ካለፈች በኋላ ጽድቁ አያብብም ሰላሙም አይበዛልንም ማለቱ ነውን ? አይደለም፤ ሰላሙም ጽድቁም ለዘለዓለም ያብባል ሲል ነው፡፡
ሠ. “እንግዲህ ሂዱና አህዛብ ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” /ማቴ.28፥19-20/ ሲል ከዓለም ፍፃሜ በኋላ ከእነርሱ ጋር አይደለም ማለት ነውን ? አይደለም፤ ይህም ፍፃሜ የሌለው እስከ ነው፡፡
ረ. “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋል” /1ኛ ቆሮ.15፥25/ሲል ጠላቶቹ ከተገዙለትስ በኋላ አይነግሥም ማለት ነውን? አይደለም ንግሥናው ፍፃሜ የለውም ነው ሲለን ነው እንጂ፡፡ /ዘዳ.34፥5-6፤ መዝ.109/ ስለዚህ ሌሎችም ጥቅሶች እንደሚያስረዱን “እስከ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜ ለሌለው ነገርም እንደሚያገለግል ነው/ዘዳ.34፥5-6፤ መዝ.109/ ፡፡ በዚህም መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ እስከምትውልድ ድረስ አላወቃትም ሲል ፍፃሜ የሌለው እስከ ማለቱ እንደሆነ መረዳት እንችላለን ፡፡ ይህ ማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን ከወለደችም በኋላ ቢሆን ዮሴፍ እሷን ከማገልገልና ከመጠበቅ ውጭ በሚስትነት እንዳላወቃት ያስረዳናል ፡፡

3.   አላወቃትም
ሄልፊደስ “አላወቃትም” የሚለውን ቃል አንድ ትርጉም ብቻ ሰጥቶት ያስተምራል ፡፡ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መተርጎም የሚገባቸው እንደ ዐረፍተ ነገሩ ይዘት ነው፡፡ ለምሳሌ “የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ እንደ በዓሉ ሥርዐት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ ቀኖቹንም ከፈፀሙ በኋላ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር ፤ ዮሴፍም እናቱም “አላወቁም” ነበር፡፡” /ሉቃ.2፥41-43/ የሚለው ቃል እንደ ሄልፊደስ ብንተረጉመው በቀጥታ ስህተት ውስጥ እንወድቃለን ፤ ነገር ግን እንደ ዐረፍተ ነገሩ ይዘት ከተረጎምነው ትክክለኛ ፍቺ ይሰጠናል፡፡ እንደዚሁ እስክትውልድ ድረስ አላውቃትም ማለቱ ድንግል ማርያም ጌታችንን ወልዳ የሰማይ መላእክት ሲያመሰግኑት፣ ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው ሲሰግዱለት፣ እረኞች የምሥራቹን ቃል ሰምተው ለምስጋና እስኪሲታደሙ ድረስ ዮሴፍ በነቢዩ የተነገረላት ድንግል እርሷ መሆኗን በቅጡ አልተረዳም ለማለት ፈልጎ ነው፡፡እንዲህም ሲል እምነቱ ፍጹም ሆነለት ማለቱ ነው፡፡ ከመስማት ማየት ይበልጣልና ስለዚህም ወንጌላዊው “አላወቃትም” አለ፡፡

7. የጌታ ወንድሞች
በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የታሪክ ጸሐፊ ሄግስፐስ የጌታ ወንድሞችና እኅቶች የተባሉት የድንግል ማርያም እኅት ለምትባለው ማርያም ልጆች እንደሆኑ በጽሑፉ አስፍሮ ይገኛል፡፡ ይህንን ቅዱስ ጀሮም፣ ቅዱስ ኦገስቲን እንዲሁም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተነሡ የፕሮቴስታንት መሥራቾች ሳይቀሩ የሚቀበሉት ነው ፡፡ በቅርቡ ማለትም በ18ኛው ክፍለ ዘመን የተነሡ የፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች ግን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆች አሉዋት መጽሐፍ ቅዱስም የጌታ ወንድሞችና እኅቶች ብሎ ጽፎልናል በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለእነዚህ ወገኖች ቅዱስ ጀሮምና ሌሎችም ቅዱሳን አባቶች የሰጡትን ትምህርት መሠረት በማድረግ መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ አስቀድመን ግን ሄልፊደስ ድንግል ማርያም ልጆች ነበሯት ብሎ የሚያነሣቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች እንመልከተው ፡፡  (ቅዱስ ጀሮም የጌታ ወንድሞች የተባሉት የዮሴፍ ልጆች ናቸው ብሎ አልጻፈም፤ ቀለዮጳ ለተባለው የእልፍዮስ ልጆች ናቸው ብሎ ያስረዳናል፡፡ ከታች የተሰጠውን ማብራሪያ በጥንቃቄ ያንብቡት)

ሀ. “ገና ለሕዝቡ ሲናገር አነሆ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር፡፡” /ማቴ.12፥46/
ለ. “ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፡፡” /ዮሐ.2፥12/
ሐ. “እንግዲህ ወንድሞቹ ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ…. ወንድሞቹስ እንኳ አላመኑበትም ነበር /ዮሐ.7፥3-5/
መ. “ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፡፡ እንዲህም አሉ ይህ ጥበብና ተአምራት ከወዴት አገኘው? ይህ የፀራቢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” /ማቴ.13፥54-55/
ሠ. “እነዚህ ሁሉ ከሴቶች እና ከኢየሱስ እናት ማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡” /ሐዋ.1፥14/
ረ. “ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በከሐዋርያት ሌላ አላገኘሁም” /ገላ.1፥19/
ሰ. “ልበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም እኅታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን?” የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃላትን ነው፡፡

ሄልፊደስ በተጨማሪም እነዚህ የጌታ ወንድሞች የተባሉት በትክክል የድንግል ማርያም ልጆች መሆናቸውን የሚያረጋግጡልን እነዚህ ናቸው ብሎ ከታች የተዘረዘሩትን ጥቅሶች ይጠቅሳል፡፡ እነዚህ ማርያም የያዕቆብና የዮሳ እናት እንደሆነች ይገልጻሉ ብሎ ይከራከራል፡፡

ሀ. “ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፡፡ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም የያዕቆብና የዮሶ እናት ማርያም የዘብዴዎስም ልጆች እናት ማርያም ነበሩ፡፡” /ማቴ.27፥55-56/
ለ. “ሴቶችም ደግሞ በሩቁ ሆነው ይመለከቱ ነበር ከእነርሱም በገሊላ ሳለ የከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት የታናሹ የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፡፡ /ማር.15፥40-41/
ሐ. “ይህንንም ለሐዋርያት የነገሯቸው መግደላዊት ማርያምና የዮሳና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱ ጋር ነበሩ፡፡” የሚሉትን ኃይለ ቃላት እንደማስረጃ ይጠቅሳል፡፡

ሄልፊደስ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸው ጥቅሶች መሠረት አድርጎ እንደሚለው ከሆነ ድንግል ማርያም በስቅለቱ ጊዜ ከነመግደላዊት ማርያም ጋር ነበረች፡፡ ወንጌላውያኑም እርሷን የያዕቆብና የዮሳ እናት ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህም ድንግል ማርያም ሌላ ልጅ እንዳላት ማርጋገጫ ነው ብሎ ይከራከራል፡፡ የሚገርመው ግን እርሱ የሚረታበትን ወንጌላዊው ዮሐንስ የጻፈውን ሊጠቅስ አለመውደዱ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉም “ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፣ የእናቱም እኅት የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፣ መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር” /ዮሐ.19፥25/ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጥቅስ ውስጥ ወንጌላዊው ድንግል ማርያምን እናቱ ብሎ ሲጠራት ከእርሷ ጋር ሌሎች ሴቶችም እንዳሉ ጠቅሶልናል፡፡ ከእነዚህም ሁለት ሴቶች መካከልም የድንግል ማርያም እኅት የምትባል የቀለዮጳ ሚስት የሆነች ማርያም የተባለች ሴት እንዳለች ገልጾልናል፡፡ ይህች ናት ታዲያ የያዕቆብ፣ የዮሳ፣ የይሁዳ እናት የተባለችው፡፡ ይህ ግልጽ እንዲሆንልን ከታች ያለውን ማብራሪያ በእርጋታ እናንብበው፡፡ 

ወንጌላዊው ማርቆስ የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብን ታናሹ ያዕቆብ ብሎ ይጠራዋል፡፡ /ማር.15፥40-41/ ይህም የዘብዴዎስ ልጅ ከሆነው ከዮሐንስ ወንድም ከሐዋርያው ያዕቆብ ለመለየት ብሎ የተጠቀመበት ቃል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ከሐዋርያት ጋር ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም በሄደ ጊዜ መጀመሪያ የተገናኘው ከታናሹ ያዕቆብ ጋር ነበር፡፡ ታላቁ ያዕቆብ ግን በጊዜው ሞቶ ነበር፤ ገዳዩም ሄሮድስ ነው፡፡ /የሐዋ.12፥2/
ቅዱስ ጳውሎስም “ከዚያ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቼ ከእነርሱ ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ሰነበትኩ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላገኘሁም፡፡” /ገላ.1፥19/ በማለት የጌታ ወንድም የተባለውንና በቅዱስ ማርቆስ ታናሹ ያዕቆብ የተባለውን ሐዋርያ ብሎ መጥራቱን እንመለከታለን፡፡ እርሱን ቅዱስ ጳውሎስ ከነጴጥሮስና ከነዮሐንስ ጋር አዕማድ ብሎ መጥራቱንም እናስተውላለን፡፡
 መጽሐፍ ቅዱስም ደግሞ ሁለት ያዕቆብ የሚባሉ ሐዋርያት እንዳሉ ገለጾ ጽፎልናል፡፡ /ማቴ.10፥3-5/ አንደኛው የዘብዴዎስ ልጅና የዮሐንስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ሌላ ያዕቆብ የሚባል ሐዋርያ የለም፡፡ ሦስተኛ አለ የምንል ከሆነ ግን ቅዱስ ማርቆስ የጌታ ወንድም የተባለውን ያዕቆብን ከዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ ለመለየት ሲል ታናሹ ያዕቆብ ማለት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ታናሽና ታላቅ የሚሉት ቃላት ለሁለት እንጂ ለሦስት ነገር መለያነት አንጠቀምባቸውም፡፡ ስለዚህም በሐዋርያት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ የተባለው(ገላ.1፡19) የያዕቆብ አባት እልፍዮስ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ "... የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፣.."(ማቴ.10፡3) በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ የጌታ ወንድም ለተባለው ያዕቆብ አባቱ እልፍዮስ ከሆነ የእመቤታችን እኅት የተባለችው፣ በመስቀሉም ሥር የነበረችው የያዕቆብና የዮሳ የይሁዳም እናት የሆነችው ማርያም የተባለችው ለያዕቆብ እናቱ ናት ማለት ነው፡፡/ማቴ.27፥55-56/ ወንጌላዊው ዮሐንስም ቀለዮጳ ያለው እልፍዮስን መሆኑን በዚህ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡  አንድን ሰው ሁለትና ከዚያም በላይ ስም ሰጥቶ መጥራት ደግሞ በዕብራውያን ዘንድ ልማድ  ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀለዮጳ የእልፍዮስ ሌላኛው ስሙ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ለምሳሌ፡-  

·       የሙሴ አማት የነበረው ራጉኤል ሌላ ጊዜ ዮቶር /ዘጸ.18፥6፣ ዘኁል. 10፥24/ ተብሎ ተጠርቶ እንመለከታለን፡፡
·       ንጉሥ ዖዝያን በሌላ ቦታ አዛርያስ ተብሎ ተጠርቷል፡፡
·       ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምዖንና ኬፋ ተብሎ ተጠርቷል፡፡
·       ቀናተኛው ይሁዳም ታዴዎስ ተብሎ ተጠርቷል፡፡

እነዚህን የመሰሉ ብዙ ምሳሌዎችን እንደማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ሄልፊደስ እንደሚለው ሳይሆን ብዙሃን እንደተስማሙበትና መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚያስረዳን የጌታ ወንድሞች የተባሉት የቀለዮጳ ወይም የእልፍዮስ እና የድንግል ማርያም እኅት የተባለችው ማርያም ልጆች ሲሆኑ ለጌታ ደግሞ የአክስት ልጆች እንደማለት ናቸው፡፡ የአክስት ልጅን ደግሞ በአይሁድ ወንድም ብሎ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ይህም የአይሁድ እምነት ተቀብላ በነበረች በአገራችን የሚታይ እውነት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ዐራት ዓይነት ወንድምነት እንዳለ ይገልጽልናል፡፡

ሀ.በመወለድ ወንድምነት
እንዲህ ዓይነት ወንድምነት ከአንድ እናትና አባት መወለድን በእናት ወይም በአባት አንድ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብና ኤሳው /ዘፍ.4፥1-2/ ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች /ዘፍ.34፥23/ ሐዋርያው እንድርያስና ሐዋርያው ጴጥሮስ /ዮሐ.1፥4/ ወዘተ….. መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለ. የወገን ወንድምነት
ይህ ዓይነት ወንድምነት በወገን አንድ መሆንን ይጠይቃል፡፡ አይሁድ ከአንድ ከአብርሃም ወገን ስለሆኑ ወንድማማቾች ተብለዋል፡፡ ለምሳሌ፡-
-      “አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግልህ” /ዘዳ.15፥12/
-      “የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል” /ዘዳ.15፥12/
-      “አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ ከወንድሞችህ መካከል የሆነውን በአንተ ላይ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም፡፡ /ዘዳ.17፥15/
-      “በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምኩ እንድሆን እጸልይ ነበር፡፡” /ሮሜ.9፥1-3/
ሐ. በሥጋ ዝምድና ወንድምነት
የቅርብ የሥጋ /የዘር/ ቁርኝት ካለ ወንድማማች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
-      ሎጥ የአብርሃም ወንድም ልጅ ነው፤ ማለትም አብርሃም ለሎጥ አጎቱ ነው፤ ነገር ግን ወንድሜ ብሎ ጠርቶታል፡፡ /ዘፍ.12፥3-5፣ 13፥8፣ 14፥14/
እንደዚሁ ሐዋርያው ታናሹ ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ ስምዖንና ዮሳ የእመቤታችን እኅት ለተባለችው ማርያም ልጆች በመሆናቸው ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ተባሉ ምክንያቱም የአክስት ልጆች ናቸው፡፡  



መ. የፍቅር ወንድምነት
የፍቅር ወንድምነት መንፈሳዊ አንድነትን የሚጠቁም ነው፡፡ ለምሳሌ “ወንድሞች በሕብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፡፡ እነሆም መልካም፣ ያማረ ነው፡፡” መዝ.132፥1 “ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁኝ ፡፡ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ” መዝ.22፥22/ “ኢየሱስም ገና ወደ አባቴ አላረኩም፤ አትንኪኝ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት” /ዮሐ.20፥1/ “አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣኦትን የሚያመልክ ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ” /1ኛ ቆሮ.5፥11/

ማጠቃለያ
ከላይ በዝርዝር ለመመልከት እንደሞከርነው እመቤታችን ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል ናት፡፡ ለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ሆኖናል፡፡ ይበልጡኑ ግን ብናስተውል ለምሳሌ ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር በሲና ተራራ ላይ ተመልክቶ ትዳሩን ትቶ በፍጹም እግዚአብሔርን እንደተከተለ ሐዋርያትም የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከጠራቸው በኋላ እነርሱም ጨርቄን ማቄን ትዳሬን ሳይሉ ስለለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳቸውን እስከ መስጠት ደርሰው ሁሉን ትተው ከተከተሉት እንዴት የዓለም መድኃኒት የሆነውን ስሙም ፍቅር የሆነ ቅዱሳንን በፍቅሩ ማርኮ ሁሉን ጥለው እንዲከተሉት ያደረገ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም እንዴት ወደ ሥጋዊ ግብር ተመለሰች ልንል እንችላለን? ዮሴፍስ የአምላክ ማደርያን፣ የቅዱሳን እናት፣ የመላእክት እኅት የሆነችውን ክብርት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለሌላ እንዴት ሲያስባት ይችላል? ይህንን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የገዛ ሕሊናችን የማይቀበለው አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም እኛ መጽሐፍ ቅዱስና የገዛ ሕሊናችን እንደሚመሰክርልን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል ናት ብለን እናምናለን፡፡  

3 comments:

  1. bewenet kale heywet yasemalen tsegawen yabzalhe bewente tero temhert new maweke yalebenen temhert new yawekenew egzyabher yimsegen bezu sew temerobatal amen amen amen

    ReplyDelete
  2. selze wendeme emebtachen dengel maryam lela lejoche yelatem gen wendem betley menafkan ensu alat eyalu new yemyaston malet new kal heywet yasemalen amen

    ReplyDelete
  3. kale hiwot yasenalin. Amen!

    ReplyDelete