Wednesday, April 4, 2012

በመስቀሉ የተፈጸመው ጋብቻ (በቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ)



 ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/07/2004
ከእኛ ጌታ በቀር ለእጮኛው ራሱን አሳልፎ የሰጠ ሰው ማን ነው? ከቤተ ክርስቲያንስ በቀር የሞተ ሰው ለእርሱዋ ባልዋ ይሆን ዘንድ የምትሻ ሴትስ ማን ናት? ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ደሙን የጥሎሽ ስጦታ አድርጎ ያቀረበ ሰው ማን ነው? በመስቀል ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ  ከአንድዬ በቀር ጋብቻውን በሕማሙ ያተመ ሰው ማን ነው ? ከሞተ አካል መጽናናት ታገኝ ዘንድ በእቅፎቹዋ ይዛ በሰርግዋ በዓል ላይ የተገኘች ሙሽራ ከዚህ በፊት ታይታ አትታወቅም ? በየትኛውስ የሰርግ በዓል ላይ ነው ሙሽራውን ሥጋ በመቁረስ በሰርጉ ለታደሙት እንግዶች መብል ይሆን ዘንድ የተሰጠው?
ሚስት በባሏ ሞት ምክንያት ፍቺን ትፈጽማለች ፡፡ ይቺ ሚስት ግን በውድ ባሏ ሞት ምክንያት ከእርሱ ጋር ፍጹም ተዋሕዶን አደረገች፡፡ እርሱ በመስቀል ላይ ራሱን በመሠዋት ቅዱስ የሆነውን ሥጋውን ሁሌም ትመገበው ዘንድ  ክብርት ለሆነችው ሙሽራው መብል አድርጎ አቀረበላት ፡፡ ጉኑንም በመወጋት ቅዱስ ደሙን በጽዋው ሞልቶ ሰጣት ፡፡ በዚህም ምክንያት በልቡዋ ያኖረቻቸው ጣዖታት ሁሉ ተወገዱላት ፡፡ በእርሱም ቅዱስ ቅባት ከበረች ፤ እርሱንም በጥምቀት ውኃ ለበሰችው ፤ በሕብስት መልክ ተመገበችው ፤ እንደ ወይንም ጠጣችው ፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱ በፍጹም ተዋሐዱ  አንድ እንደሆኑ ዓለም ሁሉ አወቀ ፡፡