ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
(ስብከት ወተግሣጽ ለሚባለው መጽሐፌ መታሰቢያ የተጻፈ)
27/07/2003 ተጻፈ
ጌታ ሆይ አንተ የመንፈሳውያንና የምድራውያን ፍጥረታት ገዢ እንደሆንኽ በሰማይም በምድር ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ተገንዝበው ለአንተ እንደ ችሎታቸው መጠን በፍቅር በመሆን ምስጋናን ያቀርቡ ዘንድ ሰውን ሰማያዊና ምድራዊ አካል እንዲኖረው አድርገህ በመፍጠር የገዢነትህ ምልክት አደረግኸው ፡፡
ምድራውያን ለአንተ አርዓያና አምሳል ለሆነው ሰው ሲገዙለት ፤ አንተን የሚያገለግሉህ ሰማያውያን መላእክት ደግሞ በፍቅር አገለገሉት ፡፡ ለማይታየው አምላክ ፣ ምሳሌ በሆነው በአዳም ተፈጥሮ በኩል መላእክት አንተን አይተው ደስ ተሰኙ ፡፡ እነርሱ በላይ በሰማይ የአንተን ፍቅር እየተመገቡ ፍጹም በሆነ ደስታ ይኖራሉና አርዓያህና አምሳልህ የሆነውን አዳምን ባዩት ጊዜ በደስታ ዘመሩ ፡፡
መላእክት የፈጣሪነትህና የማንነትህ መለያ የሆነውን በአርዓያህና በአምሳልህ በተፈጠረው ሰው ባሕርይ ውስጥ አይተው ሦስትነትህንና አንድነትህን ተማሩ ፡፡ ጌታ ሆይ “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር” አልኽ ፡፡ “ወንድና ሴት አድርገህም ፈጠርካቸው”፡፡ በአካል የተገለጠው ግን አንድ አዳም ነበር ፡፡ ሔዋን ግን በአካሉ ውስጥ ነበረች ፡፡ በኋላም ከአዳም እርሱዋን በመለየት ገለጥካት፡፡
በዚህም አብ በመውለዱ፣ ወልድም በመወለዱ፣ ምክንያት በመካከላቸው መቀዳደም እንደሌለ አርዓያህና አምሳልህ በሆነው በሰው ተፈጥሮ በኩል ለመላእክት አስተማርካቸው ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከአብ ቢሰርጽም በአብም በወልድም ሕልው እንደሆነ እንዲሁ አዳምና ሔዋንም በአንድ አካል በነበሩበት ወቅት አንዲት ነፍስ ነበረቻቸው፡፡ በዚህም መላእክት መንፈስ ቅዱስ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው እንደሆነ ተረዱ ፡፡ ስለዚህም መላእክት ሥላሴን በምሳሌው አይተውታልና ሰውን የፈጠረውን እርሱን እጅግ ወደዱት ፡፡