Saturday, February 4, 2012

የቅዱስ ኤፍሬም ጸሎት



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
26/05/2004

ጌታ ሆይ አንተ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝና አፍህን  አስፋ እሞላዋለሁም” ብለህ ተናገርኽ፤
እነሆ የባሪያህ አፍ እንደተከፈተ ተመልከት የሕሊናውም ደጅ እንዲሁ፤
በእያንዳንዱ  እርምጃው መጠን  ስላንተ ይናገር ዘንድ፤
እንደፈቃድህ የሆነ ምስጋናን ላንተ ያቀርብ ዘንድ ጌታ ሆይ በጸጋህ ሙላው፤
እኔ ራሴን በአንተ ፊት አዋርዳለሁ ከእግርህም ሥር ተቀመጥኩ ጌታ ሆይ የቃልህን ወተት መግበኝ፡፡
ጌታ ሆይ  ልደትህ በዝምታ የታተመ ነው፤
ምን  አንደበት ነው ምስጋናን ለአንተ ማቅረብ የሚቻለው?
አንተ ባሕርይ አንድ ሲሆን ባሕርይህን የገለጥክባቸው መንገዶች  ግን ብዙዎች ናቸው፤
እኛ አንተ ራስህን የገለጥክባቸውን መንገዶችን ለመረዳት ሞከርን፤
እኔ ከአንተ የጥበብ ማዕድ ፍርፋሬ ለመመገብ ተመኘሁ፤
ጌታ ሆይ ያንተ ታላቅነት ከአባትህ ዘንድ የተሰወረ ነው፡፡
ካንተ ከሆነው ሀብት ጥቂቱን በገለጥክ ቁጥር መላእክት ይደነቃሉ፤
ስለአንተ የተነገሩ ጥቂት ቃላት፤
በምድር ላሉት የሰው ልጆች እንደፏፏቴ  የበዛ ስብከት ይሆንላቸዋል፡፡
ታላቁ መልእክተኛህ በታላቅ ድምፅ ስለአንተ፤
“ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል” አለ፤(ማር.፩፥፯)
ስለዚህም እኔ ከአንተ ዘንድ እንደ ኃጠአተኛዋ ሴት እርዳታህን እጠይቃለሁ፤
ጌታ ሆይ በሰውነትህ ጥላ ፈውሴ ይጀመር፤
አንተን እንደፈራችህ ነገር ግን ስለፈወስካት ድፍረትን ገንዘብዋ እንዳደረገችዋ ሴት፤
የልብሶችህን ዘርፍ ነክቼ ስለሰውነትህ በድፍረት እመሰክር ዘንድ፤
ድፍረቱን እንዳገኝ የልቤን ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ፈውስልኝ፤
እንደ ችሎታዬ መጠን ስላንተ እናገር ዘንድ አብቃኝ፡፡
ጌታ ሆይ  ልብስህ የመድኃኒት ምንጭ ነው፤
በሚታየው ልብስ ውስጥ በሕቡዕ ያለ ኃይል አለ፡፡


 ከአንተ አፍ የወጣች ጥቂት ምራቅ የእውሩን ዐይን በማብራት ታላቅ ተአምራት አደረገች፤
የዐይን ብርሃን ከሸክላ አፈር ተሠራ፡፡
ጌታ ሆይ በሕብስቱ ውስጥ የሚበላ መለኮታዊ እሳት ተሰውሮአል፤
በወይኑ ውስጥም ሊጠጣ  የሚችል እሳት አድሮአል፤
መንፈስ በሕብስት ውስጥ አለ እሳት ደግሞ በወይንህ ውስጥ፤
የሚደንቀው  ግን እኛ በአፋችን መቀበላችን ነው፡፡
ጌታችን ሙታን ወደሚኖሩባት ምድር በመምጣቱ ምክንያት፤
ምድራውያን  በአርሱ ሥራ አዲስ ፍጥረት በመሆን መላእክትን መሰሉ፤
ከዚህም የተነሣ በውስጣዊ ተፈጥሮአቸው እሳታውያንና መንፈሳውያን ሆኑ(፪ቆሮ.፭፥፲፲፯፤ገላ.፮፥፲፭)፡፡
ሱራፊ በእጁ ሊይዘው ነቢዩ ኢሳይያስም ሊመገበው ያልቻለውን፤
ጌታ ሆይ እኛ በእጃችን እንድንይዘውና ከዛም አልፈን እንድንመገበው ሰጠኸን፡፡
ሰዎች የሚመገቡትን ምግብ አብርሃም ለመላእክት አቀረበላቸው፤ (ዘፍ.፲፰፥፰-፱)
ከዚህ ይልቅ በጣም የሚደንቀው ግን ጌታችን ይመገቡ ዘንድ ለሰዎች የሰጣቸው ምግብ ነው፤
መንፈስንና እሳትን እንዲመገቡ ለሥጋ ለባሾች ሰጠኸቸው ፡፡

 ጥንት እሳት ከሰማይ ወርዶ ኃጢአተኞችን ይበላ ነበር፤(ዘፍ.፲፱፥፳፬)
አሁን ግን ሰዎችን ከማጥፋት ተከልክሎ የምሕረት እሳት ሆኖ ወረደ፤  
በሕብስት መልክ እሳቱን ተመገብነው፤ ከእርሱም ሕይወትን ተቀበልን፡፡
እሳት ከሰማይ ወድቆ የኤልያስን መሥዋዕት በላ፤(፩ነገሥ.፲፰፥፴፰)
የምሕረት እሳቱ ለእኛ ሕያው የሆነ መሥዋዕት ሆነን፤
በእሳት የኤልያስን መሥዋዕት ተቀበለ፤
ለእኛ ግን ጌታ ሆይ ያአንተ እሳት የአንተን መሥዋዕት ተቀበለ፤
“በእጆቹ እፍኝ ነፋስን የጨበጠ ከዚህ በፊት ታይቶ አይታወቅም” ያልከው ሰሎሞን ሆይ!   (ምሳ.፴፥፬)
ናና አባትህ የሚሠራውን ሥራ ተመልከት፤ (መዝ.፻፲፥፪)
እርሱ ከተፈጥሮአዊ ሥርዐት ውጪ እሳትና መንፈስ የሆነውን በሥጋ ሰውነት ውስጥ አኖረ፤
ይህንን በሐዋርያቱ እጅ በኩል ለደቀመዛሙርቱ አፈሰሰው፡፡
 “ውሃንም በልብሱ የቋጠረው ማን ነው?” ያልከው ሰሎሞን ሆይ(ማሳ.፴፥፬)፤
የውሃ ምንጭ የሆነው እርሱ እነሆ በድንግል ማርያም አቅፍ ውስጥ ሆኖ ተመልከት፤
የእርሱ አገልጋይ ባሪያው የሆነችው ድንግል በክንዶቹዋ አቀፈችው በልብሷም ጠቀለለችው፡፡
በመሠዊያው ታቦት ላይ በማህፈድ ተሰውሮ ያለ መንፈስ አለ፤
ይህም መንፈስ የማንም አእምሮ ሊረዳው የማይችለው በውስጡ ሰውሮ ይዟ ፤
 በዚህ የምሕረት ዙፋን ላይ ባለው ማህፈድ ይህ መንፈስ ረቦ ይታያል፤
 እሳትና መንፈስ የሆነው እርሱ በወለደችህ ማኅፀን ውስጥ እንደነበር እናስብ፤
እርሱ በተጠመቅባት ባሕረ ዮርዳኖስ ውስጥም  እሳትና መንፈስ እንደነበረ እናስተውል፤
በሕብስቱና በወይኑም ውስጥ እንዲሁ እሳትና መንፈስ እንዳለ ልብ እንበል፡፡
ጌታ ሆይ ሥጋህ በስስት እኛን ሕብስቱ አድርጎ ይመገበን የነበረውን ሞትን ገደለው፤
አንተን በላን አንተን ጠጣን ፤ የእኛ ትርፍ አንተን መመገባችን ግን አይደለም፤
ነገር ግን በአንተ ሥጋ በኩል ሕይወትን አገኘን ፡፡
ጌታ ሆይ የጫማህ ማሰሪያ ጠፍር አንዳች የሚያስፈራ ግርማ አለው፤
የልብስም ዘርፍ ለተረዱት አንዳች የሚያስደነግጥ ሞገስ አለው፤
ነገር ግን ይህ አላዋቂ ትውልድ  ላንተ በሚያቀርበው ጸሎቱ በኩል፤
ከአዲሱ የወይን ጠጅ  ጠጥቶ እንደ እብድ ሆነ ፡፡
 ጌታ ሆይ አንተ በውሃ ላይ በመሄድ ድንቅ ተአምራትን ፈጸምክ፤
ታላቁንም ባሕር ከእግርህ በታች አስገዛኸው ፤(ማር.፲፬፥፳፭)
ነገር ግን ራስህን ለትንሿ ወንዝ ዝቅ አደረግህ፤
በዚህች ወንዝ ውስጥም ሰውነትህን በመዝፈቅ ተጠመቅህ፤
ወንዟ ጌታን ባጠመቀው በዮሐንስ ትመሰላለች፤
በጌታችንና በባሪያው መካከል ያለውን መበላለጥንም ትሰብካለች፤
ጌታ ሆይ ለትንሿ ወንዝና ደካማ ባሕርይ ላለው አገልጋይህ፤
ገዢያቸው የሆንክ አንተ ግን ታዘዘክ ፡፡
ጌታዬ ሆይ  ከአንተ ማዕድ ከወደቀው ፍርፋሬ ተመግቤ ጉልበቶቼ እንደ ጸኑ ተመልከት፤
ስለዚህም በአቁማዳዬ ምንም ዐይነት እጥፋት የለም፤
ጌታ ሆይ እንደቸርነትህ  መጠን ስጦታህን በውስጤ አሳድር ፡፡
ለዘለዓለሙ አሜን!!

No comments:

Post a Comment