Thursday, February 2, 2012

“ኑ ቤተክርስቲያንን ማርያም እንበላት”(ቅዱስ ኤፍሬም)

   


ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ 
25/05/2004 


"ማርያም መግደላዊት ትንሣኤውን ትመለከት ዘንድ ጌታ ወደ እርሱ አቀረባት፡፡
ስለምን ግን ጌታ ትንሣኤውን እርሱዋ ቀድማ እንድትመለከት አደረጋት? ስለምን ወንዶቹ እንዲመለከቱ አልፈቀደላቸውም?
ምክንያቱም ቤተ-ክርስቲያንና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን የዝምድና ምስጢር ጌታችን ሊያሳየን በመፍቀዱ ነው፡፡
ጌታችን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ቅድስት ድንግል ማርያም እርሱን በመፅነስ ቀድማ ተቀበለችው፤
ሞትን ድል አድርጎ ሲነሣ ደግሞ ትንሣኤውን መግደላዊት ማርያም አስቀድማ እንድትመለከት አደረጋት፤
በመጀመሪያውና በፍጻሜው(በልደቱና በትንሣኤው) ክቡር የሆነው የእናቱ ስም በዚያ እንደነበር ጮኾ ተናገረ፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን በመፅነስ በተቀበለችው ጊዜ መልአኩ ከፊቱዋ ነበር፤            
መግደላዊት ማርያምም እንዲሁ እርሱ ሕያው ሆኖ ባገኘችው ጊዜ መልአክ ከፊቱዋ ነበር፤ 
ስለዚህም ማርያም በቤተክርስቲያን ትመሠላለች፤
ድንግል ማርያም በወንጌል ቃል የሁሉ በኩር የሆነውን ልጇን በመውለዱዋ ደስ ተሰኘች፤
መግደላዊት ማርያምም በቤተክርስቲያን ቦታ ሆና ትንሣኤውን ተመልክታለችና ደስ ተሰኘች፤
ስለዚህም ቤተክርስቲያንና ቅድስት እናቱን ደስ ያሰኘው ሕፃን እርሱ በእውነት የተመሰገነ ይሁን”
ኑ ቤተክርስቲያንን “ማርያም” ብለን እንጥራት፤
ቤተክርስቲያንና ማርያም የሚሉት ስሞች በእውነት ለእርሱዋ የተገቡ ናቸውና፡፡
ለቤተክርስቲያን የመሠረት ድንጋይ ከተባለው ከቅዱስ ስምዖን ጴጥሮስ ቀድማ ማርያም ከመቃብሩ ዘንድ ተገኘች፤
 ቤተክርስቲያንንም ወክላ ጌታ እንደተነሣ የምሥራቹን ዜና ለስምዖን አመጣችለት፤
 ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶአል ብላም ሰበከችለት፤
ማርያም ወደ ስምዖን ጴጥሮስ የትንሣኤውን ዜና ይዛ መምጣቱዋ አግባብነት ነበረው፤
ምክንያቱም እርሱ ለተመረጠችው ቤተ- ክርስቲያን አለትና መሠረት ነውና፡፡
… ኢሳይያስ “ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች”ብሎ የተናገረለሽ አማናይቱ ቤተክርስቲያን ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡
የልጅሽ ስም በራሱ ታላቅ የሆነ መልእክትን በውስጡ ይዞአል፤ ሁለት ስሞች በአንድ ላይ በመዋሐድ አማኑኤል የሚለውን ስም ሰጡ፤ ይህ ስም በቤተክርስቲያንና በክርስቶስ መካከል የሆነውን ተዋሕዶ የሚገለልጥ ስም ነው፤
እርሱ ካንቺ የነሣውን ሰብእና ገንዘቡ በማድረግ አንቺን ቤተክርስቲያን አሰኘሽ፡፡ እኛንም የአካሉ ክፍሎች በማድረግ ቤተክርቲያን አሰኘን፤ ስለዚህም "እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው" የሚለው የስሙ ትርጉም ባንቺና በእኛ እውን ሆነ፤
ከቅድስት እናቱ በነሣው ሰውነት በኩል እኛን ከራሱ ጋር በማዋሐድ ቤተክርስቲያን ላሰኘን ለእርሱ ለክርስቶስ ክብር ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

1 comment:

  1. qalehiyiwet yasemalin yageligilot zemonon yibarikilih rejim edima ketan gare wenidimachin

    ReplyDelete