Tuesday, July 3, 2012

ስለድንግል ምልጃ ከመነገሩ በፊት የሚቀድመው ቁም ነገር!!!



በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
27/10/2004
ቅድስት ድንግል ማርያም ነጻ ፈቃዷን ተጠቅማ “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” በማለት ለመዳናችን ምክንያት የሆነችን እናት ናት፡፡ እርሱዋ በአንደበቱዋ “ነፍሴ በእግዚአብሔር ደስ ይላታል መንፈሴም በአምላኬ በመድኀኒቴ ሃሴትን ታደርጋለች” ብላ እንደገለጠችልን ሥጋዋን ብቻ ሳይሆን  ነፍሱዋንና ሕሊናዋን ለጌታ ማደሪያ በማድረግ ለእኛ ክርስቲያኖች አብነት የሆነች የመጀመሪያይቱ ክርስቲያንና  አማናዊቱ ቤተክርስቲያን ናት፡፡
እኛም ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በሥጋችን ቤተ መቅደስ፤ ሕጉንና ፈቃዱን እንዲሁም መንፈሱን በነፍሳችንና በሕሊናችን ማኅደር በማሳደር እርሱዋን እንመስላታለን፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ስለእርሱዋና ስለእኛ በአንድነት ሲናገር“እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁ”አለን(2ቆሮ.12፡2)

 ክርስትናን ከቅድስት ድንግል ማርያም፤ ቅድስት ድንግል ማርያምን ከክርስትና ነጣጥሎ ማስቀመጥ የማይቻል ነው፡፡ አማኑኤል፣ ኢየሱስ፣ ክርስቶስ፣ መድኃኒዓለም፣ መባሉ በድንግል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ስሞች የሥጋዌው ስሞቹ ናቸው፡፡ መዳንን ያገኘነው በሥጋዌው በፈጸመልን የድኅነት ሥራዎቹ ነው፡፡ መታመም፣ መገረፍ፣ መራቡ፣ መጠማት፣ መሰቀል፣ መሞት የሥጋ ባሕርያት ናቸው፡፡ እነዚህ ለእኛ መዳን ምክንያቶች ናቸው፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞትን በሞቱ ድል ባይነሣልን ኖሮ ፈጽሞ ባልዳንን ነበር፡፡ ትንሣኤው በኃጢአት ምክንያት ለወደቀችው ድንኳን ለተባለችው ሥጋችን ትንሣኤዋ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር ቃል ከእናታችን በነሣው ሰብእና ነው፡፡ ስለዚህ ክርስትናን ከቅድስት ድንግል ማርያም፤ ቅድስት ድንግል ማርያምን ከክርስትና ነጣጥለን መመልከት አይቻለንም፡፡ እነዚህ ከማማለድ በላይ በእርሱዋ “ይሁንታ” የተጠቀምንባቸው የድኅነታችን ምክንያቶች ናቸው፡፡
እናም ክርስቲያን እርሱዋን መስሎ በሕሊናውም በሥጋውም የአምላክ ማደሪያ ይሆን ዘንድ ተጠራ እንጂ ኃጢአትን አፍቅሮ በኃጢአት የሚገኘውን ደስታ ሽቶ እየኖረ መንግሥተ ሰማያትም እንዳትቀርበት በድንግል ምልጃ ተደግፎ እንዲኖር አይደለም፡፡ አዎ! የእርሱዋ ጸሎት በጽድቅ መንገድ ላሉትና ከዘርዋ የተቆጠሩትን ይታደጋቸዋል ያግዛቸዋል፡፡ የሐዋርያትና የነቢያት እንዲሁም በምድር በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው እግዚአብሔር አምላክ ይሰማው ዘንድ የክህነትን ስልጣን የሰጠውን የካህኑ ምልጃና ጸሎት እኛን ወደ መንግሥቱ እንድንገባ ያግዘናል፡፡ ነገር ግን ሊስተዋል የሚገባው ቁም ነገር ምንድነው? በጽድቅ መንገድ ካልሆንን በ1ቀር የቅድስት እናታችን፣ የሐዋርያትና የነቢያት እንዲሁም የካህናት ጸሎት ለእኛ ምንም የሚፈይድልን ነገር አለመኖሩን ነው፡፡
ወገኖች ሆይ! ቅድስት እናታችን ታማልደናለች ብቻ በማለት አንመላለስ፤ ይልቁኑ እርሱዋን ለመምሰል እንትጋ እንጂ፡፡ እርሱዋ ለእኛ መዳን ምክንያት የሆነችበት ዋናው ምክንያት ሰውነቱዋን ከኃጢአት ጠብቃ በመገኘቱዋ ነው፡፡ እኛም ሰውነታችንን እርሱዋን አብነት አድርገን ከኃጢአት ጠብቀን የተመላለስን እንደሆነ ልመናዋና ጸሎቱዋ እንዲሁም ምልጃዋ ሲያግዘን እናኘዋለን፡፡ የእኛም ቅድስና በራሱ ለቤተሰቦቻችንና ለወገኖቻችን እንዲሁም ለዓለም በመትረፍ ለብዙዎች መዳን ምክንያት ይሆንልናል፡፡ ነገር ግን እንደው ዝም ብሎ ያለምንም በጎ ሥራ በምለጃዋ ላይ ብቻ በመንጠልጠል የምንድን እንዳይመስለን እንጠንቀቅ፡፡ ዘርዋ የሆነውን ክርስቶስን በተግባራዊ ምልልሳችን እንምሰለው፡፡ እንዲያ ከሆነ ብቻ ነው ጸሎቱዋና ልመናዋ እኛን ሲያግዘንና ሲረዳን የምናገኘው፡፡
 እባካችሁ ክርስቲያኖች ከሌሎች ጋር በጠብ ለመፋጠጥ ስንል ይህን ቃል መጠቀምን አንምረጥ፡፡ አስቀድመን ራሳችንን በቅድስና ሕይወት ለማኖር እንድከም በዚህም ራሳችንን በቀጭኗ ጎዳና እናመላልስ፡፡ በዚያችም ጎዳና የቀደሙንን ቅዱሳንን፣ የሚራዱንን ቅዱሳን መላእክትንና ቅዱሳን ነፍሳትን እናገኛቸዋለን፡፡ ለሚጠይቁንም እንደሚገባቸው አድርገን በቀላሉ በሕይወታችን የተረዳነውን በቃላችን ወይም ለእኛ በተሰጠን ጸጋ በኩል መልሱን በመስጠት እነርሱን ወደ እምነት ልናመጣቸው እንችላለን፡፡ ስለምልጃዋ ከመናገራችን በፊት መቅደም ያለበት ግን ራሳችንን በጽድቅ ሕይወት ማቆም ነው፡፡ በመቀጠልም በእርሱዋ የምናገኘውን እርዳታ ተስፋ ማድረግ ይሆናል፡፡
 እንዲያ ካደረግን ብቻ ነው የእርሱዋ ጸሎትና ልመና እኛን እንደተራዳን አፋችንን ሞልተን መናገር የሚቻለን፡፡ነገር ግን እኛ በኃጢአት ጭቃ ውስጥ ተዘፍቀን ከፍቅር ርቀን እየኖርን ድንግል ታማልዳለች ብንል ማን ሊያምነን ይችላል? ስለዚህም አስቀድመን በሕይወታችን እርሱዋን ለመመሰል እንትጋ፡፡ እንዲህ ካደረግን ስለምልጃዋ አንደበታችን ሳይሆን ሕይወታችን ምስክር ይሆንልናል፡፡ ድንግል ሆይ አንቺን መስለን ነፍሳችን በልጅሽ ፍቅር እንዲቀጣጠል፣እርሱን መስለን ለዓለም ብርሃን ሆነን እንድናበራ፣ የጠፉትን የልጅሽን መንጎች ወደ ዘለዓለማዊው ማደሪያቸው እንድናገባቸውና በፈጣሪያቸው ፍቅር ሰክረው ለዘለዓለም በደስታ እንዲኖሩ ለምኝልን ለዘለዓለሙ አሜን!!!   

14 comments:

  1. Thank you Dn.! May the Almighty bless you more! If it is possible for you, if you can teach us what is to mean: It is Impossible for the world to be saved with out the intercession of the Virgin Mary? Hope to see your post soon.

    ReplyDelete
    Replies
    1. መዳን አለመዳን በእያንዳንዱ ሰው እጅ የተሰጠ እንጂ በሌሎች ውሳኔ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እንኳ በእኛ መዳንና አለመዳን ምርጫ ላይ ነጻ ፈቃዳችንን ተጋፍቶ ወይም ጥሶ የራሱን ውሳኔ አይወስንም፡፡ ወሳኔ ሰጪዎቹ እኛው ራሳችን ነን፡፡ ነገር ግን መዳንን ስንፈቅድ ወደ መዳን በምናደርገው ጉዞ ቅዱሳን መላእክት፣ ቅዱሳን ነፍሳት፣ እንዲሁም ካህናትና፣ መምህራን ከጎናችን ይሰለፋሉ እንደተሰጣቸው ጸጋ መጠን ትልቅ ድጋፍን ያደርጉልናል፡፡ ቅድስት እናታችን ደግሞ ጸጋ የሞላባት ናትና ከሌሎች ይልቅ በጽድቅ ሕይወት ያሉትን ስትራዳቸው ትገኛለች፡፡ ነገር ግን በመዳን አለመዳን ላይ ውሳኔው የእኛና የእኛ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያልጣሰውን ነጻ ፈቃዳችንን ማንም አካል ቢሆን ሊጥሰው አይችልም፡፡ ስለዚህም ያለድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም የሚለውን አገላለጽ በግሌ አልቀበለውም፡፡ እርሱዋ ስለእኛ ትማልድልናለች ነገር ግን እኛ ፈቃደኞች ባንሆን የእኛ መዳናችን ቀረ ማለት አይደለምን? እንዲያስ ከሆነ በቤተክርስቲያን የሚፈጸሙ ምሥጢራት ማለት ምሥጢረ ቁርባን፣ ጥምቀት፣ ንስሐ ለምን አስፈለጉ? እነዚህስ ከአምላክ ጋር ፍጹም እርቅን እንድናድርግ አያደርጉንምን? ስለዚህ ያለድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም የሚለው አስተምህሮ የቤተክርስቲያናችን መሆኑን እጠራጠራለሁ፡፡ ጌታችን ሐዋርያትን ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፡፡ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ስፍራ ባዘጋጀላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ፡፡”(ዮሐ.14፡1-3)ባላለን ነበር፡፡ ብዙ መኖሪያ ያለው የመዳን መንገዳችን ብዙና በአማራጮች የተሞላ መሆኑን የሚያስገነዝበን ነው፡፡

      Delete
  2. KHY wondimachine

    ReplyDelete
  3. belaye seb ... Seba nefsatinn yegedelew sew bewunu kaleEmebetachin amalajinet beqer min melkam sira tegegntobet lidn chale???
    Dingil hoy siletsadiqan yayidele silihatean asasibis keto lemin tebale? Alebelezias yedingil amalajinet medihanit hono yeneefsin kusil keshare yih medihanit letamemut lehatiyategnochu kalhone endemin letenegnochu yihonal? Neger gin hatiyategna bekifatu endayiqetil timihirt yemigeba new... Neger gin yihn sinaderg yeeminetin hayalinet leziyawum beEnatachin lay yalenin talaq yeeminet hayil endihu endante gedel eyesededin ayidelem... Bigeban emebetachinin mematsen silehatiyztachin malqes malet new... Silehatiyatachin malqes degmo tsidq new, tirufat new.
    Yemiyastewul yastewul... Ebakachihu yerasachihunn hasab taqomu zend atirutu... Lesewu hulu kemastemar befit yebetekiristiyanin timihrt maten ayigebami? Memihir ebakih kerasih sigawi hasab wutana yemenfesin hasab temar... Alebeleziam mistirin chafun bicha yizeh kemitibazin sirunim yazew.. Yane hulu melkam mehonu yitaweqal...
    Engdih yihm koment kaskefah endelelagnaw comment matifat tichilaleh, ene gin sihitetun sihitet malete ayiqerim, yihnm yemilew orthodoisawi silehonkina enem endeziaw bemehone new...
    Egziabher mastewalun yadilen. Amen.

    ReplyDelete
  4. ለአስተያየቴ ግልፅነት በአማረኛ ማድረጉ የሚሻል ስለመሰለኝ በአማረኛ ትንሽ ማብራሪያ በመጨመርና ከላይ ያሉ አንዳንድ ተግሳፆች በመተው ይህን ፅፌያለሁ፡፡ ስለቤተክርስቲያን አስተምህሮ ፡ ስለቅዱሳን ክብር በተነጋገርን ጊዜ የምናስተውላቸውን በስህተትም ሆነ በእውቀት የሚነገሩ አንዳንድ የተሳስቱ ትምህርቶችን በማይ ጊዜ ብዙውን ጊዜ ህሊናየ ይበሳጫል ፤ አንዳንድ ጊዜ ከአህያ ጋር የዋለች እንደሚባለው ተረት አይነት ብዙውን ጊዜያችንን ከመናፍቃን ጋር ያደረግን ጊዜ እነሱን ያስደሰትን ሲመስለን ፡ ወይንም እነሱን ወደተዋህዶ እንመልሳለን ብለን የአባቶቻችን ትምህርት ያልሆነ ፡ ኦርቶዶክሳዊም ያይደለ የመለሳለስ ትምህርቶችን መስጠት መልካም አይደለም፡፡ ጨለማ ከብርሃን ጋር ምን ህብረት አለው? ብርሃን ጨለማን ያስደስት ዘንድ ይደበዝዛልን? ዲያቢሎስስ ከሚካኤል ጋር ምን ህብረት አለው? ሚካኤል ዲያቢሎስን ያስደስት ዘንድ ፅኑ እምነቱን ያለሳልሳልን? አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ሁላችን እንደአባቶቻችን ፅኑአን ልንሆን የሚገባ ነው ፤ በግ ከሆንክ በግ ነህ ፡ ፍየል ከሆንክ ደግሞ ፍየል ነህ ፡ ከሁለቱ የተዋጣ ሌላ ሶስተኛ ባህርይ የለም፡፡ የለንም፡፡ እናስተውል ፦ በቅርቡ እንኳን እንደሰማነው ክርስቲያኖችን አንድ ማድረግ በሚል ብሂል እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት እስከማለት የደረሱ አባቶችን እስከመስማት ደርሰናልና፡፡ መናፍቃን ቢመለሱ ኦርቶዶክሳዊውን ገሃድ እምነት ተቀብለው ይምጡ ፡ ባይመጡም ለራሳቸው ይወቁ ፤ እኛ ግን እነሱን እንመልስ ብለን እምነታችንን አንሽራርፍ ፡ የታወቀች ንፁህ እምነታንንም በራሳችን ሃሳብ ለመሻር አንሞክር ፡ በተለይ የቤተክርስቲያን ማእረግን ተቀብላችሁ የቤተክርስቲያን አስተማሪ የሆናችሁ እናንተ፡፡
    ይቀጥላል

    ReplyDelete
    Replies
    1. እንግዲህ ኦርቶዶክሳውያን ሁላችን ራሳችንን እንጠይቅ ፦ አስቀድመን እንዲህ እንጠይቅ ፦ ፅድቅ ምንድን ነው? እምነት ፅድቅ አይደለምን? ወይንስ መድሃኒት ለማን ነው? ለበሽተኛ አይደለምን? ለጤነኛውማ ምን ይረባዋል? ወይንስ መድሃኒትን ማን ይናፍቃታል? የታመመ አይደለምን? ይህስ መናፈቁ በመድሃኒቱ ላይ እምነት ማሳደሩ አይደለምን? አለበለዚያስ እመቤታችን የነፍሳችንን ቁስል የስጋችንን ሽክም በፀጋዋ ፡ በፀሎቷ የምታድን ፡ የምታቃልል መሆኗ መድሃኒት መሆኗ አይደለምን? እንግዲህ መድሃኒትን የሚሹ በሽተኞች እነማን ናቸው? በእመቤታችን አማላጅነት የተማመኑ ሃጥአን አይደሉምን? መታመናቸውስ ፅድቅ አይሆንላቸውምን? እንዲህስ ከሆነ ራስን እንደበሽተኛ እንደሃጢአተኛ ዝቅ አድርጎ በመድሃኒት ፊት ከማቅረብ የሚከብር ትሩፋት ምንድን ነው? በራስ ፅድቅስ ከመታመን ራስን እንደሃጢአተኛ መቁጠር እጅጉን ማትረፊያ አይደለምን?

      Delete
    2. ወይንስ ምን እንላለን? በላየ ሰብ እንደምን ዳነ? መልካም የፅድቅ ስራ ተገኝቶበት ነውን? እርሱስ እንደስሙ ሰባ ነፍሳትን የበላ ክፉ ነበረ እንጂ፡፡ ነገር ግን የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜ ከክፋቱ ተመለሰ (ስሟን ይወድ ነበርና ፡ ስለስሟ ከክፋት ራቀ ፡ ድንግልም ስለውዴታው የፅድቅ ስራ አሰራችው) ይሄውም ጥቂት ውሃ ለተጠማ እንዲያጠጣ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው ለመዳን ክርስቶስን መስሎ መቼ ታየ? ስጋውን ደሙን መቼ ተቀበለ ፡ ንስሃንስ ከማን ወሰደ? ከአንዲት ጠብታ ውሃ ለተጠማ ከማጠጣት ወዲያ ምን መልካም ተገኘበት? ነገር ግን ስለእመቤታችን ክብር ፡ ስለእመቤታችን የአማላጅነት ሃይል አንዲቷ ጠብታ ውሃ በዘመኑ ሁሉ ሲሰራው ከነበረው እጅግ ክፋት መዘነ? እንግዲህ ስለማን እንመካ? ስለበጎ ስራ ፡ ስለፅድቅ ስራ ነውን? አይደለም፡፡ ነገር ግን በእመቤታችን እንመካለን፡፡ ይሄውም መመካታችን ስለእምነት ነው ፡ ስለሚታይ ስለሚዳሰስ የፅድቅ ስራ ግን አይደለም ፤ መመካታችን ግን ራሳችንን ስለሃጢአት መክሰሳችን እመቤታችንንም ምርኩዝ ማድረጋችን ነው ፤

      Delete
  5. ወይንስ ዘወትር ድንግል ሆይ ስለፃድቃን ያይደለ ስለተዳደፉት አሳስቢ ስለምን እንላለን? ፃድቅማ በፅድቁ ይድን ዘንድ የሚታመን አይደለምን? ነገር ግን ሃጥአን እንደምን ይድናሉ? እንደምን የንስሃ ፍሬ ሊያፈሩ ይችላሉ? እንደምን ስለሃጢአት መስዋእት ሊያቀርቡ ይቻላቸዋል? አስቀድሞ ሃጥአን ስለመሆናቸው ከዚህ የንስሃ ፍሬ እውቀት የተለዩ አይደሉምን? እንግዲህ ማን ከሃጢአት ህይወት ሊመልሳቸው ይችላል? ማንስ ከሃጢአት እንዲለዩ ይመክራቸዋል? ማንስ መልካሙን የህይወት መመለስ እውቀት ሹክ ይላቸዋል? አባቶቻችን ድንግልን ስለተዳደፉት አሳስቢ ያሉት ስለዚህ አይደለምን? ሃጥኡ ወደ ፅድቅ ይመለስ ዘንድ ድንግል ሆይ ፦በአማላጅነሽ በልጅሽ ፊት ቅረቢ ፤ ድንግል ሆይ የህሊናው አይን ለጠፋበት ሃጥእ የህሊናውን አይን አብሪለት ፤ ድንግል ሆይ የልቡ ብርሃን ለጨለመበት ፡ የማትጠፊ ፋናችን አንቺ ነሽና ጨለማውን ግፈፊለት ፡ ብርሃንን ያይ ዘንድ ፡ የፅድቅን ህይወት ይማር ዘንድ ፡ ከሃጢአት ይርቅ ዘንድ ፡ ወደማስተዋል ይቀርብ ዘንድ ፡ የንስሃ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ፤ ድንግል ሆይ ለእኛ በሃጢአት ያለነው ቅረቢ ፡ ለእኛ በፀሎት ህይወት ለደከምነው በፀሎትሽ ሃይል ብርታት ሁኚን ፤ ድንግል ሆይ ሃጢአት ግድግዳ ሆኖ በአምላክና በእኛ ፊት ተጋርዷልና ስለፅድቅሽ ሃይል ግድግዳውን አፍርሺልን ፤
    ይቀጥላል

    ReplyDelete
  6. ድንግል ሆይ ፦ እኔማ ሃጥእ ነኝና ያለ እርዳታሽ ይህን ማድረግ እንደምን ይቻለኛል? ድንግል ሆይ ፦ አለበለዚያማ ከሃጢአቴ መለየትን እንዳገኝ ርዳታን ካላገኘሁ እንደምን ወደልጅሽ ልቀርብ ይቻለኛል? ድንግል ሆይ ፦ አለበለዚያማ የንስሃ ፍሬ ማፍራትን እንደምን እማራለሁ? ድንግል ሆይ ፦ አለበለዚያማ የሃጢአት ወዳጆቼን ትቼ ለፅድቅ እንደምን እቀርባለሁ? አንቺ ካልረዳሺኝ? ካህኑ አባቴ በፀሎቱ ካላሰበኝ ፡ ቅዱሳን ፃድቃን በረከታቸውን ካላሳደሩብኝ ፡ መላእክት እለት እለት ካልተራዱኝ ፡ ሃዋርያት ካልመከሩኝ እንደምን ከሰፊው መንገድ ወጥቼ ወደ ጠባቧ መንገድ እገባለሁ? እንደምን የስጋን ድሎት ረስቼ የነፍሴን ማሰብ ይቻለኛል? እንደምን አለማዊነትን ንቄ መንፈሳዊነትን አጥብቄ እይዛለሁ? እንደምን ራስ ወዳድነቴን ርግፍ አድርጌ ትቼ ባልንጀራየን እወዳለሁ? ድንግል ሆይ እኔማ ሃጥእ ነኝ ፤ ሃጥእ ነህ ብለሽ ካልረዳሽኝማ እንደምን ፃድቅ እሆናለሁ?
    ይቀጥላል

    ReplyDelete
  7. እንግዲህ የፅድቅ ስራ እንደሌለኝ ድንግል ሆይ አንቺ ታውቂያለሽ ፤ ነገር ግን ባንቺ እምነት አለኝ ፤ በዚህም ሁለት መልካም ነገሮች አሉኝ አንዱ ራሴን ስለሃጢአቴ መውቀሴ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በአንቺ ፀሎት ረዳትነት መታመኔ ነው፡፡ ስለዚህም አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ ይላል ፦ እመቤቴ የተመረጥሽ ድንግል ማርያም ሆይ፦ የሰራሁትን ሐጢኣት ባስበው ልቦናየ እጅግ ደነገጠብኝ ፤ አእምሮ ሳለኝ አለል ዘለል እያልኩ በፅርአት መኖሬን ባሰብሁት ጊዜ ልቦናየ እጅግ ደነገጠ፡፡ የሐጢአቴን ብዛት በተቆጥጠርሁ ጊዜ ልቦናየ እጅግ ደነገጠ ፡ አንድ ሰአት ስንኳ ሐጢኣት ለመስራት አላቋረጥኩም ፤ በሰውና በመላእክት ጉባኤ መካከል ራቁቴን መቆሜን አሰብሁ ፤ በአይነ ልቦናየ እመለከት ዘንድ ወዲህና ወዲያ ተመላለስኩ ፡ ምናልባት የሚረዳኝ ባገኝ ፤ ከዚህ እጅግ ከሚያስፈራው ከሰራሁት ሐጢአት ፍዳ የተነሳ ምናልባት የሚዋሰኝ ባገኝ ብየ ፤ ነገር ግን በማማለድ እኔን ለማዳን የምትችይውን አንቺን አማላጅ አገኝሁ ፡ ዘወትርም ከእኔ እንደማትርቂ አወቅሁ፡፡ --- እናቴ ሆይ ፦ ነፍሴ ባንቺ ዘንድ ትክበር ፡ ስለቸርነትሽ እናቴ ነሽ ፡ ስለንግስትነትሽም እመቤቴ ነሽ ፡ ስለፍቅርሽ የታመንሽ ስለልጅሽም የመድሃኒት ቀንድ ሆይ አስቢኝ ፡ እንደወደቅሁም እቀር ዘንድ ኣትርሽኝ፡፡” አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን ዘሠሉስ
    እግዚአብሄር ማስተዋሉን ያድለን አሜን፡፡

    ReplyDelete
    Replies
    1. ውድ ወንድሜ እኔ ያልኩት እመቤታችን አታማልድም ነውን? ስለምንስ ራስህን በቁጣ ትጎዳለህ ቅዱስ ኤፍሬም “እሳት የወጣበትን እንጨት መልሶ ይበላል፡፡ ቁጣም እንዲሁ ቁጡ ሰውን ታጠፋለች” ይላል፡፡ መንፈሳዊ እርጋታ ተሞልተህ ልል የፈለግሁትን በትክክል ተረድተህ ቅን ያልመሰለህ እኔን የሚጎዳ መስሎ ያገኘኸውን በፍቅር ቃል ለማረም ሞክር፡፡ ማንም ቢሆን አንተ እንዳስቀመጥከው ከዲያብሎስ ወገን ሊሆን የሚፈቅድ ሰው የለም፡፡ ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አርዓያ የተፈጠረ ስለሆነ ባሕርይው የእግዚአብሔር የሆነ ነገር ይስማማዋል፡፡ እርሱ ትሑትና የዋሃ ነው እኔም አንተም ትሑታንና የዋሃን ልንሆን ይገባናል፡፡ እርሱ በባሕርይው ፍቅር ነው እኔና አንተም ፍቅር የሚገዛን የጠፋውን በፍቅር ቃልና በተግባራዊ ፍቅር ልንመልስ ይገባናል“ፍቅር አይበጭም” ይላልና፡፡(1ቆሮ.13፡4) ቅዱስ ጳውሎስ ጌታችን መድኀኒታችንም በፍቅርና በየዋህነት ተመላልሶ ነው እኛ እርሱን እንድንመስል የጠራን፡፡ ሌላውን ግን ከመናገር እከለከላለሁ ሰጣ ገባ ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡
      ግን እኔ ስለእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጣም ጽፌአለሁ፡፡ እኔ በድፍረት እንዲህ አላለሁ፡፡ ክርስቲያን ሁሉ አንተም እኔም እርሱዋን መስለን በእርሱዋ ዐይን ክርስቶስን ማየት ካልችልን ክርስቲያኖች አይደለንም፡፡ እርሱዋን ካልመሰልክ ክርስቶስን ፈጽሞ ልታውቀውም ልትረዳውም አትችልም ፡፡ ወንድሜ በእናታችን ላይ ያለኝ አመለካከት ጥልቅ ነውና ከወደድክ ጽሑፎቼን ሁሉ ተመልከታቸው እንጂ ደርሰ ክፉ ስም ለመለጠፍ አትፍጠን፡፡ ይህ ካንተም እንዲታረም የምፈልገው ነገር ነውና አስተካከለው፡፡ ማንም ነፍስን የሚያስቆጣ ንግግርን ይናገር ልክ እንደ መምህራችን ክርስቶስ በሰከነ አእምሮ በተረጋጋና መንፈስ እርሱን እንዳታስቆጣና እናዳታሰናክለው ተጠንቅቀህ በትሕትና ቃል ልትመልስለት ይገባሃል፡፡ ክርስቲያን ሁሉ የአንድ አባት ልጅ ነው እርስ በእርሳችንም ወንድማማቾች ነን ማንም በማንም ላይ የበላይ አይደለም፡፡ ለሁሉም ጌታቸው አንድ ክርስቶስ ነው ሁላችንም የእግዚአብሔር ባሮች ነን፡፡ ስለዚህ በእርሱ ላይ ምንም ዐይነት መብት ከሌለህ ወንድምህ ጋር ስትነጋገር ወይም እርሱን ከጥፋት ለመመለስ ስትደክም በትሕትናና ፈቃዱን ጠይቀህ መሆን አለበት፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “በእርሱ ውስጥ ካለው መንፈስ በቀር በሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው?” ይላልና ስለማታውቀው ከመናገር ተጠንቀቅ፡፡ በሰፈርከው መስፈሪያ ይሰፈርብሃልና ለራስህ ፍራ፡፡ በታውቀው ለማወቅም መብቱ በሌለህ ሰው ላይ ከመፍረድ ተቆጠብ ወንድሜ፡፡
      ወንድሜ ሆይ አንተ ላነሣኸው ጉዳይ ግን አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅህና ይህን ከመለስክልኝ በኋላ እኔ ልል የፈለግሁትን አሰፍርልሃለሁ፡፡ ዙሪያ ጥምጥም መልስ ግን አልፈልግም፡፡ ጥያቄውም ይህ ነው፡- ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኢየሩሳሌም ጥፋት ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር “ ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ …. ዶሮ ጫጩቶቹዋን ከክንፎቹዋ በታች እንድትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ አልወደዳችሁም፡፡ እነሆ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀራል፡፡”(ማቴ.23፡37-38) ሲል ምን ማለቱ ነው? እነርሱን ከጥፋት ሊያድናቸው አይቻለውም ነበርን? እነርሱን እንዳያድናቸው ምን ከለከለው? መልስህን እጠብቃለሁ፡፡

      Delete
  8. wendime memihir diyaqon shimels... Benigigire hulu kasqeyemkuh ejig yiqirta adirigilegn... Egziabherin silemakiber sewun mezilef yemigeba ayidelemina... Engdih ene hatiyategna negnina yiqr belegn tseliyilgnm....

    Neger gin anten sayihon hasabihin teqawume kehone, maninetih lay sayihon tsihufih lay yayehutin (yemeselegnin) gidfet awutiche kehone yihn endemin seyitanawi quta yihonal, minalibatis kirisriyanwi kiniat endehones?

    Memihir ante diyaqon neh, ene gin tera sew negn, ene bisasat rasen atefalehu, ante bitisasat gin bizuwechin tasasitalehin benigigirihm hone behulu lititeeneqeq yemigeba yimeslegnal...

    Yehonew hono kelay yetsafkut tsihuf begilts yeminagerew ante emebetachin atamalidim silemaletih ayidelm (yihen betiyaqe melk ansitehewalina) enem anten yetum bota bezih aredad alweqeskuhim....
    Neger gin yeemebetaxhininm hone yeqidusanun miljan erdata lemagegnet betsidq hiwote meqom yigebal yalkewun hasab teqawumialehu, silezih hasab bicha tsihufenim endetsafkugn gena sijemir tenagireyalehu.... Ante erdatan lemagegnet yetsidq siran qidmiya aderek, ene degmo miljan beteley lehatian endemiyasfelg, endehonem tenagerku...
    Dingil hoy siletsadiqan yaydele silehatian asasbi..

    Memihir, ene hatiyategna negnina tseliyilgn.

    ReplyDelete
    Replies
    1. ወንድሜ ሆይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊና የእመቤታችን ያደራ ልጅ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም”(3ዮሐ.4) ካለ ቅድስት እናታችንስ እኛ ልጆቹዋ በጽድቅ ሕይወት ብንመላለስላት እንዴት ይበልጥ ደስ አይላት? እኛ እንደ ፕሮቴስታንቱ እምነት ብቻ የምንል አይደለንም፤ ምግባርም አስተባበረን ልንይዝ ይገባናል ብለን እንሰብካለን፡፡ ምግባር ሳንይዝ አምነናል ብንል ክህደት ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ ቅዱስ ጳውሎስ አይሁድን“እግዚአብሔርን እንዲያቁ በግልጥ ይናገራሉ ዳሩ ግን የሚያጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለሆኑ በሥራቸው ይኩዱታል፡፡” ብሎ ጽፎልናል(ቲቶ.1፡16) የኔም መልክእት ይህ ነው፡፡ መጀመሪያ ፈቃዱ ይኑረን እንደ ችሎታችንም መጠን እንታዘዝ፤ ከዚያ በኋላ ምልጇዋን እንጠይቅ፤ ይህ ነው ኦርቶዶክሳዊው መንገድ፡፡
      ወንድሜ ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ሁሉ ስለእኛ ብንጠይቃቸውም ባንጠይቃቸውም እኮ መጸለያቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ስንጠመቅ እርሷ እናታችን እኛ ደግሞ ልጆቿ ቅዱሳንም ወዳጆቻችን በመሆን አንድ ቤተሰብ ሆነናልና፡፡ እስቲ ልጠይቅህ፡- እናት ስለልጁዋ መልካምን ከማሰብና ለእርሱ መልካምን ከማድረግ ልትቆጠብ ይቻላታልን? እናትህ መልካምን የምታደርግልህ አንተ ጠይቀሃት ነውን? እርሱዋ ላንተ ካላት ፍቅር የመነጨ መልካምን የምታደርግልህ አይደለችምን? ስለዚህም ምንም ክፉ ልጆች ብንሆን ስለእኛ መጸለየዋ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የዘሩዋ የክርስቶስ ኢየሱስ ልጆች ነንና፡፡
      ነገር ግን ለመዳንና ምልጁዋ እንዲፈጸምልን የእኛ ፈቃድ ወሳኝ ነው፡፡ ፈቃዳችን ብቻ አይደለም ፈቃዳችን በተግባር ሊታይ ይገባዋል፡፡ ያም ማለት መታዘዝ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከተፈጥሮአችን ጋር ፈጽሞ የሚስማማ ነው፡፡
      ወንድሜ ሆይ ሁላችንም እኮ በደለኞች ነን፡፡ ነገር ግን 38 ዓመት ሙሉ በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ የነበረውን ሰው ለማዳን ጌታችን “ልትድን ትወዳለህን? ብሎ እንደጠየቀው ለመዳን የእኛ ፈቃድ ወሳኝ ነው፡፡ ላንተም ያቀረብኩልህ ጥያቄ የሚያስረዳው ኢየሩሳሌም ለመዳን ባለመውደዱዋ እንደጠፋች ነው፡፡ መጻጉዕ ለጊዜው ያለበት ሁኔታ ተግባራዊ መታዘዝንን ለመፈጸም አይፈቅድለትም ነበር፡፡ ስለዚህ ፈቃዱን በተግባር አልገለጠም፡፡ እንዲህ ዐይነት ተመሳሳይ ነገርን በፈያታይ ዘየማን ላይ እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን እኛ ፈቃዱን ለመፈጸም ሁሉ ነገር የተመቻችልን ክርስቲያኖች ፈቃዳችንን በተግባር ካልገለጽን ከከሃዲያን ተነጥለን የምንታይ አይደለንም(ምንም እንኳ ቃሉ ከባድ ቢሆንም)፡፡(ቲቶ.1፡16)እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ልክ “እሺ” ብሎ እንዳልታዘዘው ልጅ እጣ ፈንታችን ይሆናል፡፡(ማቴ.22፡28-32) ምልጃም እንዲሁ ነው፡፡ መጀመሪያ ለመዳን ፈቃዱ ሊኖረን ይገባል፡፡ ከዚያም መታዘዝ እንዲህ ከሆነ ልንድን የቅድስት እናታችን ምልጃ ሲረዳን እናገኘዋለን፡፡ ግን ለመዳን የእኛ ፈቃድና መታዘዝ በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡

      Delete
  9. ራስህን ደግሞ ከተጠያቂነት ለማሸሽ አትሞክር፡፡ ጌታችን “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” ያለው ለሐዋርያት ብቻ አይደለም፡፡ እኛ ራሳችንን በጽድቅ ሕይወት በማመላለስ ለዓለም ብርሃን ካልሆንን ለሌሎችም ማሰናከያ በመሆናችን ፍርዳችን እጥፍን ነው፡፡ ማንኛውም ምዕመን በሹመት አይሁን እንጂ በጥምቀት በቅባዕ ሜሮን ከብሮ ለዚህ ዓለም ካህን ሆኖአል፡፡ ይህን ለመረዳት(http://shimelismergia.blogspot.com/2012/01/125-9.html) አንብበው ወንድሜ፡፡ ስለዚህ በጥምቀት ባገኘነው የክህነት ሥልጣን(royal priesthood or baptismal priesthood) ልቡናችንን በቃሉ ሞልተን በምግባራችን ሌሎችን እየሰበክን ልክ እንደ ካህናት ካልተመላለስን ስለሌሎች መሰናከል ተጠያቂ መሆኑ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ምዕመኑ በቃልም፣ በተግባርም ከሌሎች ተሸሎ ሊገኝና ክርስቶስ በእርሱ ሊገለጥ ይገባዋል፡፡ አንተም ወንድሜ ልታምን ብቻ ሳይሆን በተግባር በክርስቲያናዊ ሕይወት በመኖር ሌሎችን ወደ ክርስቶስ ልታቀርብ የንጉሥ ካህን ሆነህ ተቀብተሃል፡፡
    እንደኔ እንደኔ ቅጣቱ የሚከብደው በመምህራንና በተሾሙ ካህናት ላይ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እኛ መምህርነታችን መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው ለመዳን ብዙ አማራጩች ባሏቸው ምዕመናን ላይ ነው፡፡ ስለዚህ እነርሱ በእኛ ቢሰናከሉ እንኳ በውስጣቸው ሆኖ የሚገሥጻቸውና ወደ እውነት የሚመራቸው መንፈስ ቅዱስ አለና በንስሐ ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ወይም እነርሱ ባያዩም ባያስተውሉም ጌታችን በዕፀ በለሱዋ መስሎ እንዳስተማረው ጠባቂው መልአክ ያ ክርስቲያን ፍሬ ሳያፈራ እንዳይሞት ሊማጸንለትና በኢዮ.33፡23-28) ላይ እንደተገለጠው በመልአኩ ልመና “ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ሊለመልም፣ ወደ ጉብዝናውም ወራት ሊመለስ፣ ወደ እግዚአብሔር ሊጸልይ እርሱም ሞገስን ሊሰጠው ይችላል፡፡ እርሱም ስለተደረገለት ታላቅ ቸርነት “እኔ በድያለሁ፣ ቅኑንም አጣምሜአለሁ፣ የሚገባኝን ብድራት አለትቀበልኩም፣ ነፍሴን ወደ ጉድጓድ እንዳትወርድ አድኖአታልና፣ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች” ብሎ ፈጣሪውን ሊያመሰግን ይችላል፡፡
    ነገር ግን ምዕመናን ወደ ክርስትና ላልመጣውና በፍጥረታዊ አእምሮ ለሚመላለስ ሰው በምግባር ክርስቶስን እየሰበከ ወደ ጥምቀት የማቅረብ ሐላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን በእርሱ ክፉ ተግባር የክርስቶስ ስም ቢሰደብ በእርሱ ምክንያት ወደ መዳን መምጣት ያለበት ያ ፍጥረታዊ ሰው ስለሚሰናከል በእርሱ ወደ መዳን አለመምጣት ተጠያቂ ነው፡፡ ይህን ግን የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ አልተረዳውም፡፡ ወደ ክርስትና ያልመጣውን ወደ ክርስትና ለማቅረብ መንገዱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ማመንና መጠመቅ ነው፡፡ ከዚህ የወጡ ሌሎች አመራጮች የሉም፡፡ ከአሕዛብ ወገን የሆነ ቆርኖሌዎስ እንኳ ምንም የእግዚአብሔርን ሕልውና ተረድቶ እግዚአብሔርን ቢያመልክም ለመዳን መጠመቅ ስላለበት ለእርሱ የምስራቹን ዜና ይዞ የተገለጠለት መልአክ ይጠመቅ ዘንድ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ነበር የመራው ብቸኛ መንገዱ ጥምቀት ነውና፡፡ ስለዚህም በምዕመኑ የተሰናከለ ፈጽሞ ለመጥፋት በእጅጉ የቀረበ ነው፡፡ ምክንያቱም በውስጡ የእውነትን ቃልን የሚገልጥ መንፈስ ቅዱስ ገና አላደረበትምና፡፡ ስለዚህ ከመምህራንና ከካህናት በበለጠ በምዕመኑ ላይ ከባድ የሆነ ሸክም አለ እላለሁ፡፡ ስለዚህ ራስህን ከተጠያቂነት አታሽሽ ወንድሜ ይህን ስል ግን ከፍቅር በመነጨ ነው፡፡

    ReplyDelete