ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/08/2004
ጌታዬ ሆይ! ይቅር በለኝ፤ ወደ አንተ በንስሐ እመለስ ዘንድም ብርታትን
ስጠኝ፡፡ እንደ ቅዱስ ፈቃድህ በቅድስና እመላለስ ዘንድ ወደ አንተ መልሰኝ፡፡ የአጋንንት መኖሪያና ጎሬ የሆነውን ልቡናዬን
እባክህ ቀድሰው፡፡
ጌታዬ ሆይ! እኔ ከአንተ ዘንድ ለራሴ ይቅርታን እጠይቅ ዘንድ የማይገባኝ
ጎስቋላ ሰው ነኝ፡፡ በተደጋጋሚ ንስሐ ለመግባት ቃል እገባና ለራሴ የገባሁትን ቃል መጠበቅ ተስኖኝ ዋሾ ሆኜ እገኛለሁ፡፡ አንተ
ከወደቅሁበት የኃጢአት አዘቅት በተደጋጋሚ ብታወጣኝም እኔ ግን በገዛ ፈቃዴ በደጋጋሚ በኃጢአት ተሰነካክዬ እወድቃለሁ፡፡
ስለዚህም ጌታዬ ሆይ! በራሴ ላይ እፈርዳለሁ፤ በመተላለፌ ከአንተ ዘንድ የሚመጣብኝን ቅጣት ሁሉ በጸጋ እቀበላለሁ፡፡ አምላኬ
ሆይ! ስንቴ ጨለማ የወረሰውን ልቡናዬን በጸጋህ ብርሃንህ አበራኸው? እኔ ግን ተመልሼ ወደ ተናቀውና ከንቱ ወደሆነው አስተሳሰብ
ተመለስሁ፡፡ ይህን ባሰብኩ ቁጥር ሰውነቴ በፍርሃት ይርዳል፡፡ ነገር ግን የኃጢአት ፈቃዴ አይሎ በኃጢአት አዘቅት ውስጥ
በተደጋጋሚ እወድቃለሁ፡፡