Tuesday, April 10, 2012

ክርስቶስ በዮሴፍ(በቅዱስ ኤፍሬም)



ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
2/08/2004
የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ሆይ አንተን ከሚያፈቅሩህ አገልጋዮችህ ንጹሕ ዘርን የመረጥህ፤ አባታችንን ያዕቆብን በእርጅናው ደስ ስላሰኘው ስለዮሴፍ የቅድስና ሕይወት እሰብክ ዘንድ ታላቅ ከሆነው ቸርነትህ የጸጋ ስጦታህን አብዝተህ ያፈሰስክልኝ አምላኬ ሆይ ስምህ ቡሩክ ይሁን፡፡
በዚህ ጻድቅ ወጣት ሕይወት ውስጥ የክርስቶስን ሁለቱን ምጽአቶች በምሳሌ እናገኛቸዋለን፡፡ የመጀመሪያው ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ወደዚህ ዓለም የመምጣቱን ሲሆን ሁለተኛው ግን በሚያስፈራ ግርማ ሆኖ ዓለምን ለማሳለፍ የሚመጣውን ምጽአትን ነው፡፡

ተወዳጆች ሆይ በክርስቶስ ኢየሱስም የምትፈቀሩ ምዕመናን፣ እጹብ ድንቅ የሆነውን የዚህን ብላቴና የቅድስና ሕይወት ለመስማት አእምሮአችን ሳይባክን በቅድስና ጸንተን በነፍሳችን ደስ ብሎን ለመስማት እዝነ ልቡናችንን እናዘንብል፡፡ ነገር ግን ወንድሞች ሆይ ይህ ጻድቅ ወጣት ከንጹሐን አባቶች ዘር ስለሆነ ክቡሩን ልነግራችሁ አልሻም፡፡ ቢሆንም የዚህን ወጣት እጹብ ድንቅ የሆነ የቅድስና ሕይወትን ዛሬ እንማራለን፤ በኃጢአት ላይ የተቀዳጀውን ታላቅ የሆነውን ድሉንም እንሰማለን፡፡
ይህ ጻድቅ ብላቴና በእውነት የጌታችንን የመድኀኒታችንን ዳግም ምጽአት በሕይወቱ ያሳየን ብላቴና ነው፡፡ ስለዚህም ስለእርሱ የምናገረውን የሚሰማ ክርስቲያን ሁሉ ከሕሊና ምድራዊ የሆነውን አስተሳሰብ አውጥቶ ይጣል፡፡ ይህንንም መንፈሳዊ ቅኔን ለመቀኘት በነፍሱ ደስ ብሎት በመናፍቆት ይስማ፡፡
እኛን ለማዳን ከአባቱ እቅፍ የነበረው ጌታ ወደ እኛ እንደ ተላከ እንዲሁ ዮሴፍም ከአባቱ ከያዕቆብ እቅፍ የወንድሞቹን ደኀንነት ይጠይቅ ዘንድ ወደ ወንድሞቹ ተላከ፡፡ ነገር ግን የዮሴፍ ወንድሞች ክፉዎች እንደነበሩና ለእነርሱ ሰላምን ይዞ የመጣውን ወንድማቸውን ለመግደል በክፋት እንደተማከሩበት እንዲሁ አይሁድ ልቡናቸውን በክፋት አደንድነው እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ በተረዱ ጊዜ ይህ ወራሹ ነውና እርሱን ገድለን ርስቱን የእኛ እናደርገው ዘንድ ኑ እንግደለው ብለው በክፋት ተማከሩበት፡፡
 የዮሴፍ ወንድሞች ኑ ከሕልሙ አንዱም እንዳይፈጸም እንግደለው ብለው እንደተማከሩ እንዲሁ አይሁድም ኑ እንግደለውና ስለእርሱ የተነገረውን ሁሉ ከንቱ እናድርገው ብለው በክፋት መከሩበት፡፡ የዮሴፍ ወንድሞች እርሱን ከሸጡትና በሕሊናቸው ከገደሉት በኋላ በደስታ እንደበሉና እንደጠጡ፤ እንዲሁ አይሁድም ክርስቶስን ከገደሉት በኋላ ፋሲካቸውን አደረጉ በደስታም በሉ ጠጡ፡፡
 የዮሴፍ ወደ ምድረ ግብጽ መውረድ መድኅናችን ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመምጣቱ ምሳሌ ነው፡፡ ዮሴፍ በጲጥፋራ መኝታ ቤት ውስጥ የኃጢአትን ኃይል አዋርዶ በእርሱ ላይ እንደተረማመደበት፣ የእመቤቱን የዝሙት ፈቃድ ድል በመንሣት የብርሃን አክሊልን እንደተቀዳጀ እንዲሁ የነፍሳችን አዳኝ የሆነ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ፈቃድ በነፍስ ወደ ሲኦል በመውረድ የኃጢአትን ኀይል ድል በመንሳት በእርሷ ላይ ተረማመደባት፤ ፍጹም ድልንም በሲኦል ላይ ተቀዳጀ፡፡
ዮሴፍ ኃጢአትን ድል እስኪነሳት ድረስ ወደ እስር ቤት እንዳልተጣለ እንዲሁ ጌታችንም የዓለምን ኃጢአት በሞት ድል እስኪነሳ ድረስ ወደ መቃብር አልወረደም፡፡ ዮሴፍ በወህኒ ቤት ሁለት ዓመት በነጻነት እንዳሳለፈ እንዲሁ ጌታችን በመቃብር ሥጋው ሳይፈርስና ሳይበሰብስ ሦስት ቀንና ሦስት መዓልት አደረ፡፡ ዮሴፍ በፈርዖን ትእዛዝ በታላቅ ክብር ከእስር ቤት እንደወጣ፣ የሕልሞቹንም ምሳሌ በሚረዳ መልኩ በቀላሉ ለፈርዖን እንደተረጎመለት፤ ወደፊትም አዝመራው እንደሚበዛና እጅግ የስንዴ ምርት እንደሚሆን ለፈርዖን እንደነገረው፤ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በራሱ ሥልጣን ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት ሲኦልን በዝብዞ ከነፍሳት አራቆታት፤ ለአባቱም እኛን የነጻነት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ ትንሣኤንና ዘለዓለማዊ ሕይወትን ተሰፋን ሰጥቶን ደስ አሰኘን፡፡
ዮሴፍ በፈርዖን የንግሥና ሰረገላ ላይ ተቀምጦ ግብጽን እንደገዛት፤ እንዲሁ ለንግሥናው ዘመን የማይቆጠርለት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በብሩህ ደመና ወደ ሰማይ በማረግ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ እንደመሆኑ መጠን ከኪሩቤል በላይ በአባቱ ቀኝ መቀመጫውን አደረገ፡፡
ዮሴፍ በግብጽ ላይ ገዢ በሆነ ጊዜ በጠላቶቹ ላይ እንደሠለጠነባቸው፤ በእነርሱ ላይ ይነግሥ ዘንድ ባልወደዱትና ባሪያ አድርገው ይሞት ዘንድ የሸጡት ወንድሞቹ በዮሴፍ ዙፋን ፊት በፍጹም መገዛትና መንቀጥቀጥ እንደ ሰገዱለት፤ ነገር ግን ዮሴፍ ወንድሞቹ እንደሆኑ ባወቃቸው ጊዜ በአንዲት ቃል እነርሱ ነፍሰ ገዳዮች እንደሆኑ እንደገለጠባቸው፡፡ እነርሱም ይህን በተረዱ ጊዜ እንደድዳ በመሆን ታላቅ እፍረት እንደያዛቸውና ክፉ ስለሆነው ሥራቸው ምክንያት ማቅረብ እንደተሳናቸው፤ እንዲሁ በዚያ በሚያስፈራው የፍርድ ቀን ጌታችን በብሩህ ደመና በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሲገለጥ በእነርሱ ላይ ገዢ እንዳይሆን ያልፈቀዱት አይሁድ በዙፋኑ ዙሪያ ባሉት ግሩማን መላእክት ግርማ ይንቀጠቀጣሉ፡፡
እንደ ሰው ሞቶ ይቀራል ብለው ያሰቡት አይሁድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲመለከቱት በክፉ ምክራቸው ያፍራሉ እንደድዳም ይሆናሉ፡፡ እነዚህ እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ተገልጦ እንደመጣ አውቀው ሊከተሉት ያልወደዱት ወገኖች ናቸው፡፡ ልክ የዮሴፍ ወንድሞች "ሊገዛንና ባሮቹን ሊያደርገን በእኛ ላይ እየተነኮለብን ነው" ብለው በሰጉ ጊዜ ዮሴፍ በግልጽ "እኔ ባሪያ አድርጋችሁ የሸጣችሁኝ ወንድማቹሁ ዮሴፍ ነኝ፣ ምንም እንኳ በእናንተ ላይ ገዢ እንድሆን ባትፈቅዱም እግዚአብሔር ገዢ አደረገኝ" እንዳላቸው፤ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በታላቅ ሥልጣን በዕለተ ምጽአት በሚያስፈራ ግርማ በተገለጠ ጊዜ በእነርሱ ላይ ገዢ እንዳይሆን በመስቀል ላይ ሰቅለው ለገደሉት አይሁድ የብርሃን መስቀሉን ያሳያቸዋል፤ እነርሱም በዚህ መስቀል ላይ ሰቅለው የገደሉት የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጁ የሆነው ክርስቶስ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ስለኃጢአታቸውም ማስተባበያ የሚሆን አንዳች ምክንያት ማቅረብ ይሳናቸዋል፤ ያፍራሉም፡፡ ኦ ያ ጊዜ እንዴት የሚያስፈራ ነው !!!  ተወዳጆች ሆይ ይህን ልብ በሉ፤ ዮሴፍ በትክክል የጌታውና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ  ምሳሌ እንደሆነም ተረዱ፡፡        

2 comments:

  1. kale hiwot yasemaln tsegawn yabzalh edmi na teyna yadlh ye agelgulot zemenh yibarklh amlake kudusan!!! endante aynetoch memhran yabzaln .

    ReplyDelete
  2. ዮሴፍ በግብጽ ላይ ገዢ በሆነ ጊዜ በጠላቶቹ ላይ እንደሠለጠነባቸው፤ በእነርሱ ላይ ይነግሥ ዘንድ ባለመወደዱትና ባሪያ አድርገው ይሞት ዘንድ የሸጡት ወንድሞቹ በዮሴፍ ዙፋን ፊት በፍጹም መገዛትና መንቀጥቀጥ እንደ ሰገዱለት፤ ነገር ግን ዮሴፍ ወንድሞቹ እንደሆኑ ባወቃቸው ጊዜ በአንዲት ቃል እነርሱ ነፍሰ ገዳዮች እንደሆኑ እንደገለጠባቸው፡፡ እነርሱም ይህን በተረዱ ጊዜ እንደድዳ በመሆን ታላቅ እፍረት እንደያዛቸው፤ ክፉ ስለሆነው ሥራቸው ምክንያት ማቅረብ እንደተሳናቸው፤ እንዲሁ በዚያ በሚያስፈራው የፍርድ ቀን ጌታችን በብሩህ ደመና በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሲገለጥ በእነርሱ ላይ ገዢ እንዳይሆን ያልፈቀዱት አይሁድ ጠላቶቹ በዙፋኑ ዙሪያ ባሉት ግሩማን መላእክት ግርማ ይንቀጠቀጣሉ፡፡
    Awo yiniketeketalu yiridalu bezachi seati memihiri kale hiyiweti yasemali menigisite semayati yawirisili besega bekibiri yitebikilin

    ReplyDelete