Saturday, January 14, 2012

“ከተኩሎች ተጠበቁ”


ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
ቀን16/09/2000 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መግቢያ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰዎች ፍቅርን ከማጥፋቸው የተነሣ እግዚአብሔር መንግሥትን እንደሰጣቸው ያስተምራል፡፡ በእርግጥም ላስተዋለው ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ገዢና ተገዢ ወይም ባርያና ጌታ የሚሉት ቃላት የመጡት የኖህ ልጅ ካም የአባቱን እርቃን ተመልክቶ በእርሱ ላይ በመሳለቁ ነበር ፡፡ ኖህ ከስካሩ ሲነቃ ካም በእርሱ ላይ እንደተሳለቀበት አወቀ ስለዚህም ልጁን ረገመው፡፡ “ከንዓን የባሮች ባሪያ ይሁን” አለው፡፡ ከዚያ ወዲያ በኃጢአት ምክንያት የገባው የገዢና የተገዢ ሥርዐት በአህዛብ መልክና ቅርጽ እየያዘ  መንግሥት ወደ መሆን መጣ፡፡ በእስራኤልም ሕዝቡ እግዚአብሔር ገዢአቸው እንዳይሆን በመሻታቸው እንደ አሕዛብ ንጉሥ ይኑረን ብለው ነቢዩ ሳሙኤልን በጠየቁት ጥያቄ መሠረት የመጀመሪያውን የመንግሥት ሥርዐት በጨካኙ ሳኦል ተዋወቀ፡፡ እንደ ቤተሰብ ይተያዩ በነበሩት ሕዝቦችም ዘንድ ገዢና ተገዢ ተፈጠረ፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ የነበረው ግን ሰው ቤተሰባዊ በሆነ ሕግ እንዲመራ ነበር፡፡ አሁን ይህ ቤተሰባዊ ሥርዐት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በደሙ በመመሥረት ሰጥቶናል፡፡