ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ቀን16/09/2000 ዓ.ም
አዲስ አበባ
መግቢያ
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሰዎች ፍቅርን ከማጥፋቸው የተነሣ እግዚአብሔር መንግሥትን እንደሰጣቸው ያስተምራል፡፡ በእርግጥም ላስተዋለው ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ገዢና ተገዢ ወይም ባርያና ጌታ የሚሉት ቃላት የመጡት የኖህ ልጅ ካም የአባቱን እርቃን ተመልክቶ በእርሱ ላይ በመሳለቁ ነበር ፡፡ ኖህ ከስካሩ ሲነቃ ካም በእርሱ ላይ እንደተሳለቀበት አወቀ ስለዚህም ልጁን ረገመው፡፡ “ከንዓን የባሮች ባሪያ ይሁን” አለው፡፡ ከዚያ ወዲያ በኃጢአት ምክንያት የገባው የገዢና የተገዢ ሥርዐት በአህዛብ መልክና ቅርጽ እየያዘ መንግሥት ወደ መሆን መጣ፡፡ በእስራኤልም ሕዝቡ እግዚአብሔር ገዢአቸው እንዳይሆን በመሻታቸው እንደ አሕዛብ ንጉሥ ይኑረን ብለው ነቢዩ ሳሙኤልን በጠየቁት ጥያቄ መሠረት የመጀመሪያውን የመንግሥት ሥርዐት በጨካኙ ሳኦል ተዋወቀ፡፡ እንደ ቤተሰብ ይተያዩ በነበሩት ሕዝቦችም ዘንድ ገዢና ተገዢ ተፈጠረ፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ የነበረው ግን ሰው ቤተሰባዊ በሆነ ሕግ እንዲመራ ነበር፡፡ አሁን ይህ ቤተሰባዊ ሥርዐት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በደሙ በመመሥረት ሰጥቶናል፡፡
በዚህ ጽሑፌ የጎላውን ተመልክቼ የጻፍኩት እንደሆነ አንባቢው እንዲረዳልኝ እጠይቃለው፡፡
ክርስቶስ “እንደ ሄሮድስ ደምን ከተጠሙ ፖለቲከኞች ሽሹ፡፡ ሲሞቱም እንቅበራቸው ብላችሁ እነርሱን ከመሰሉት ጋር አትደባለቁ፡፡ ከእነዚህ ሬሳቸው ብቻ ከሚያረክስ እንዲሁም በቁማቸው ከሞቱ ሲኦል አፉዋን ከፍታ ከምትጠብቃቸው ሽሹ፤ ከአልቃሾቻቸውም ጋር ኅብረት አይኑራአችሁ፤ እኔን ተከተሉ እንጂ ከእነዚህ ቀበሮዎች ኅብረት ተለዩ” ሲለን “ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው” ብሎ አስተማረን፡፡
የእነዚህ ግብረአበሮች ከሆናችሁ እንደ እናንተው ሙት የሆነው ፖለቲከኛው የእናንተ ጠላት ሆኖ ይነሣባችኋል፡፡ ደም ለመቀባባትም እርስ በእርሳችሁ ትተዳደናላችሁ፡፡ አንዱ የአንዱን ነፍስ ይፈልጋል አንዱ በአንዱ ላይ ይሸምቃል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወገኖች እግዚአብሔር ትዝ አይላቸውም፡፡ በእነርሱ ቤት ለዘለዓለም የሚኖሩ ይመስላቸዋል፡፡ ስለእግዚአብሔር ማወቅም ይሁን መስማት አይሹም፡፡ ክርስቶስንም አያፈቅሩትም እነዚህ ዓለምን በክፋታቸው የሞሏት ተኩላዎች ናቸው፡፡ ክርስቶስ በእውነት ሐዋርያትን “በተኩሎች መካከል እልካችኋለሁ” አላቸው፡፡ በእውነትም ደምን የተጠሙ ተኩሎች ናቸው፡፡ የንጹሐንን ደም ያፈሳሉ፤ የንጹሐንን ቆዳ ገፈው እርሱን በመልበስ ንጹሐን መስለው ከሃይማኖት መሪዎች ጎን ይቆማሉ ወይም የሃይማኖት መሪዎች ይሆናሉ፡፡ የእውነተኛው የበጉ ደም ግን እንደ አቤል ደም እነርሱን ይካሰሳቸዋል፡፡
የሰይጣንም መንግሥት በመለያየት፣ በጥል፣ በክርክር የምትቆም ናትና እነዚህ ወገኖች በምድር ላይ እጅግ የበዙ ጠላቶች አሉባቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው እንደአውሬ ይበላላሉ፡፡ አንዱ አንዱን ጠብቆ ተጠባብቆ ይኖራል፡፡ ቀንም ሆነ ሌሊት በስጋት ውስጥ ናቸው፡፡ በምድርም አውቀውም ቢሆን ሳያውቁ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነው ይመላላሳሉ፡፡ የሰይጣን ግበረአበሮች ናቸውና በቀለኞች፣ በመጠጥ ውስጥ የሚደበቁ ሰካሮች፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የሆኑት ግን ከሰይጣን በቀር በምድር ላይ አንድም ጠላት የለባቸውም፡፡ እንደ ኢዮብ እግዚአብሔር አጥር ቅጥር ይሆናቸዋል፡፡
ምናልባት አንድ ሰው ስለምን ታዲያ ለእነዚህ ሰዎች ሥልጣኑ ይሰጣቸውዋል? ስለምንስ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው ተባለ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በፍቅር ሊታዘዙትና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመመላለስ ያልፈቀዱትን፣ ሰማይና ምድርን የፈጠረ ነፍስን ከሥጋ ለይቶ ወደ ሲኦል የሚጥለውን እግዚአብሔርን የማይፈሩትን ሕዝቦች የሰይጣን አገልጋዮች እንዲሠለጥኑባቸው በመፍቀዳቸው እንደምርጫቸው እግዚአብሔር ስለሰጣቸው ነው ይሆናል መልሱ፡፡ እነርሱም በአረመኔነት ለእግዚአብሔር አልገዛ ያለውን ሕዝብ ይገዙታል፡፡ ቅዱሳኑ ግን ከሕግ በላይ ስለሆኑ እነርሱ ላይ ፈጽመው ሊሠለጥኑ አይችሉም፡፡ ምድራዊው ሕግ አትስረቅ ይላል፤ እነርሱ ከሕግ አልፈው ይመጸውታሉ፤ ምድራዊው ሕግ አትግደል ይላል፤ እነርሱ ግን ነፍስ ያድናሉ፡፡ በአጠቃላይ እነርሱ ልክ እንደ ቅዱሳን መላእክት ከሕግ በላይ ናቸው፡፡
ወገኔ ሆይ! ሕግ እኮ የተሠራው ቅዱስ ጳውሎስ “ለአመፀኞችና ለኃጢአተኞች፣ ቅድስና ለሌላቸው ለርኩሳን፣ አባት እናትን ለሚገድሉ ለነፍሰ ገዳዮች፣ ለሴሰኖች ፣ ከወንድ ጋር ለሚተኙ፣ በሰዎች ለሚነግዱ፣ ለውሸተኞችም፣ በውሸት ለሚምሉ፣ የቡሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደተሰጠኝ ወንጌል የሆነው ደኅና ትምህርት ለሚቃወም፣ ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደተሠራ እንጂ ለጻድቃን እንዳልተሠራ ሲታወቅ ነው” እንዳለው ሕግ የተሠራው ለኃጥአን ነው፡፡ ሕግ ያስፈለጋቸውም ወገኖች እነኚህ ናቸው፡፡ እነዚህ ሙታን ናቸውና ሙታን ገዢዎች በላያቸው ላይ ይሾማሉ፡፡ እነርሱም በጉልበትና በጭካኔ ይገዟቸዋል፡፡ የእነዚህ የበላይ ገዢአቸው ሰይጣን እንደሆነ ግብራቸው ይገልጣቸዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ በእነርሱም በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁ”ብሎ ገልጦልናል፡፡
የቁጣ ልጆችን ሰይጣን ይመራቸዋል፤ ይህን እግዚአብሔር ያደረገው ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆችን ግን ክርስቶስ ይመራቸዋል፡፡ ድምፁን ይሰሙታል፣ ያውቁታል፣ ይከተሉታልም፤ ከእጁ ማንም ሊነጥቃቸው አይችልም፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔም አውቃቸዋለሁ፤ ለዘለዓለምም አይጠፉም፤ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም፣የሰጠን አባቴ ከሁሉ ይበልጣል ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም እኔና አባቴ አንድ ነን”
ስለዚህ ወገኔ ሆይ ክርስቶስ ርኅሩኅ አባት ነው፡፡ ነፍስህም ድምፁን ታውቀዋለች፡፡ ለእርሱዋም ሕይወቱዋ ነው፡፡ እንደ ነፍሰ ገዳይ ፖለቲከኞች ከሆንክ “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይወጣም” እንዲል እጅህ በደም የተጨማለቀ ስለሚሆን የእርሱን የሰላምን ድምፅ መስማት አትሻም፡፡ እንዳውም የማይጋፉትን እግዚአብሔርን በራስህ ላይ በጠላትነት ታነሣሣዋለህ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ከመሰሉ ፖለቲከኞች ሽሽ፡፡ እነርሱ የነካቸውን ሁሉ የሚያረክሱ በቁማቸው የሞቱ ሬሳዎች ክርስቶስ እንደተናገረው “በኖራ የተለሰኑ ውስጣቸው ግን በርኩሰት የተሞላ መቃብሮች፣ የበግ ለምድ ለብሰው የሚታዩ ተኩላዎች ናቸው፡፡ ወገኔ ሆይ በግ ሁን የዚያን ጊዜ እግዚአብሔር እረኛህ ይሆንሃል፡፡
በጎ ሥራዎችን አብዝተህ ሥራ፤ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑር፤ ሁል ጊዜ እግዚአብሔር አምላክህን በፊት ለፊትህ አድርገው፤ እርሱ ይመራሃል፤ ቀናውን ጎዳና ያሳይሃል፤ ከክፉ ተኩሎች ይጠብቅሃል፡፡ ነገር ግን ከክፉ ፖለቲከኞች እርሾ ተጠበቅ፤ ክፉ የሆነ ምክራቸውን አትቀበል እነርሱ አንተን ለክፉ ሥራቸው መጠቀሚያ ያደርጉህ ዘንድ ያባብሉሃል፡፡ ሁሉን መርምር እንጂ ፖለቲከኛውን ሁሉ አትስማ፡፡ ነገር ግን ስለድሆች፣ ስለአቅመ ደካሞች፣ ስለሴቶች፣ ስለሕፃናት፣ ስለአረጋዊያን ተሟገትላቸው፡፡ እነርሱን እንደ አቅምህ መጠን ደግፋቸው፤ ሴቶችን አክብር፤መብታቸውን አትጣስ፡፡ እነርሱን ፍቅር እንጂ ጉልበት አይገዛቸውም፡፡ ፍቅር ደግሞ በአመፃ ደስ አይላትም፤ ስሜትህን ግዛ እንጂ አይግዛህ፤ ሴትን ልጅ ፍቅር ብለህ ጥራት፡፡ ፍቅር እንደሆነችም ተረዳ፡፡ ፍቅር እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርን እንግዲህ በጉልበት ልግዛህ ማለት የማይታሰብ እንደሆነ ሴት ልጅንም እንዲሁ በጉልበት ማንበርከክ አይቻልም፡፡ “ያዕቆብ አባታችን እግዚአብሔርን ታግሎ አሸነፈ” ተባለለት፡፡ ለምንም ይመስልሃል? የእውነተኛ ፍቅር መገለጫ በሆነችው በትሕትና አምላኩን በመለማመኑ ነው፡፡
ሴት ልጅ ገበናህን የምትሰውርልህ ቤትህ ናት፡፡ በክርስቶስ ፍቅር የተማረከች ቤተክርስቲያንን ትመስላታለች፤ ጠብ፣ ጦርነት፣ አይስማማትም፡፡ ሰላምን ፍቅርን ትወዳለች፡፡ ክርስቶስንም ትመስለዋለች፤ ቅዱስ ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ ፣የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር” በማለት ክርስቶስን ከሴቷ ጋር እግዚአብሔር አብን ከወንዱ ጋር ማነጻጸሩን እንመለከታለን፡፡ ይህ የሚያሳየን ሴት ልጅ የቤተክርስቲያን ብቻ ምሳሌ ሳትሆንም በክርስቶስን መመሰሉዋን ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር አብ ከእግዚአብሔር ወልድ እንደማይበልጥ እንዲሁ ወንድም ከሴት አይበልጥም፡፡ ወንድ በፆታው በክርስቶስ እንደሚመሰል በምዕመንነቱ ግን በቤተክርስቲያን እንዲመሰል እንዲሁ ሴት በመታዘዙዋ ክርስቶስን በፆታዋ ቤተክርስቲያንን ትመስላታለች፡፡ ስለዚህም ወንድና ሴት አኩል ናቸው፡፡ በግብር እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር ወልድ እንዲለያዩ እንዲሁ ወንድና ሴት ተፈጥሮ በሰጠቻቸው የሥራ ድርሻ አንዱ ከሌላው ይለያል፡፡ ይህን ሁሉ መናገሬ ለሴት ልጅ ተገቢውን ክብር እንድንሰጥ፣ ሴቶችም ክብራቸውን አውቀው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ለማሳሰብ ነው፡፡ ሴት ልጅን ነፍሰ በላ ፖለቲከኛ አይስማማትም፡፡ ምክንያቱም የሕያዋን እናት እንጂ የሙታን እናት አይደለችምና፡፡ ሴትን ልጅ የፍጥረት ጥፋት ያሳዝናታል፤ የሕፃናት ዋይታ ያስጨንቃታል፤ የሰዎች እልቂት ያስተክዛታል፡፡ ወገኔ ሆይ ከነፍሰ ገዳዮች ሽሽ እነርሱንም አትምሰላቸው፡፡
hi i like ur blog it is really interesting. i also know a blog which is as good as yours if you dont know it here is the link http://www.betepawlos.com/
ReplyDeletewhere is ur email i need to contact you and share some ideas with you about blogging. you need to but your email or phone number somewhere in the blog.
ReplyDeleteወንድሜ ሆይ ስለ አስተያየትህ በእጅጉ አመሰግናለሁ ኢሜል አድሬሴንና ስለክ ቁጥሬን ጽፌልሃለሁ email. Chrys.shime@yahoo.com or chrys.shime@gmail.com phone no. 0911046165 ስለትብብርህ ከልብ አመሰግናለሁ
Delete