ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/05/2004
እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር
ሲያበጀው በአርዓያውና በአምሳሉ መፍጠሩ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ ያለ ሦስትነትና አንድነት በሰዎችም
ዘንድ እንዲታይ በመሻቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን በአካል ሦስት ነው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆን በእግዚአብሔርነቱ አንድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መገለጫው ባሕርይ የሕግጋት ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር በመሆኑ በባሕርይው መገለጫ ስሙ እግዚአብሔርን ፍቅር እንለዋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ፍጹም የሆነ አንድነት በአርአያውና አምሳሉ በፈጠረው ሰው እንዲገለጥ በሰው ሰብእና ውስጥ
ፍቅርን ተከላት፡፡ በፍቅርም ሰውን ሁሉ ፍጹም ወደ ሆነ አንድነት ያመጣዋል፡፡ ያለፍቅር ሰው እግዚአብሔርን ከቶ ሊመስለው አይችልም፡፡
ይህ እንዲሆን እግዚአብሔር አምላክ
አስቀድሞ አዳምን ከፍቅር ጋር አዋሕዶ ፈጠረው፤ በመቀጠል ስለፍቅር ከጎኑ አጥንት ሔዋንን አበጃት፣ የፍቅርን ፍሬ ይመለከቱ ዘንድ ደግሞ በሁለቱ አንድነት
እኛን ልጆቹን ሰጣቸው፡፡ እነዚህ በቁጥር ሦስት ቢሆኑም በመገኛቸው አዳም አንድ ናቸው፡፡ እንዲህም ሲባል አባት፤ እናት እና
ልጅ ማለታችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አንድነት ሲመሰክር “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤
ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ባረካቸውም፡፡ እነርሱንም በፈጠረበት ቀን ስሙን አዳም ብሎ ጠራው” ይለናል፡፡(ዘፍ.5፡1-2) በዚህም
እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ሦስትነትና አንድነት በሰዎች ውስጥ እንዲታይ መፍቀዱን እናስተውላለን፡፡