ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
18/05/2004
እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር
ሲያበጀው በአርዓያውና በአምሳሉ መፍጠሩ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ ያለ ሦስትነትና አንድነት በሰዎችም
ዘንድ እንዲታይ በመሻቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሲሆን በአካል ሦስት ነው፡፡ በአካል ሦስት ሲሆን በእግዚአብሔርነቱ አንድ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መገለጫው ባሕርይ የሕግጋት ሁሉ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር በመሆኑ በባሕርይው መገለጫ ስሙ እግዚአብሔርን ፍቅር እንለዋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ፍጹም የሆነ አንድነት በአርአያውና አምሳሉ በፈጠረው ሰው እንዲገለጥ በሰው ሰብእና ውስጥ
ፍቅርን ተከላት፡፡ በፍቅርም ሰውን ሁሉ ፍጹም ወደ ሆነ አንድነት ያመጣዋል፡፡ ያለፍቅር ሰው እግዚአብሔርን ከቶ ሊመስለው አይችልም፡፡
ይህ እንዲሆን እግዚአብሔር አምላክ
አስቀድሞ አዳምን ከፍቅር ጋር አዋሕዶ ፈጠረው፤ በመቀጠል ስለፍቅር ከጎኑ አጥንት ሔዋንን አበጃት፣ የፍቅርን ፍሬ ይመለከቱ ዘንድ ደግሞ በሁለቱ አንድነት
እኛን ልጆቹን ሰጣቸው፡፡ እነዚህ በቁጥር ሦስት ቢሆኑም በመገኛቸው አዳም አንድ ናቸው፡፡ እንዲህም ሲባል አባት፤ እናት እና
ልጅ ማለታችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ አንድነት ሲመሰክር “እግዚአብሔር አዳምን በፈጠረ ቀን በእግዚአብሔር ምሳሌ አደረገው፤
ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ባረካቸውም፡፡ እነርሱንም በፈጠረበት ቀን ስሙን አዳም ብሎ ጠራው” ይለናል፡፡(ዘፍ.5፡1-2) በዚህም
እግዚአብሔር አምላክ በእርሱ ውስጥ ያለው ሦስትነትና አንድነት በሰዎች ውስጥ እንዲታይ መፍቀዱን እናስተውላለን፡፡
በሶርያ ቅዱሳን አባቶች ዘንድ መንፈስ
ቅዱስን እናት ብሎ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ በክርስትና ስሙ ያዕቆብ ዘንጽቢን የሚባለው አባት መንፈስ ቅዱስን እናት ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ “ስለሚስቱ
ሲል አባትና እናቱን የተወ ሰው ማን ነው? እንዲህ ማለት ትርጉሙ ይህ ነው፡- አንድ ሰው ሚስት እስካላገባ ድረስ አባት የሆነውን
እግዚአብሔር አብን እናት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ይወዳል፡፡ ከእርሱ በቀር ሌላ ፍቅር አያቅም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ሚስት
ካገባ አባትና እናቱን ይተዋል” ይላል፡፡ እንዲህ ሲል እርሱ ሙሉ ሰው ነው፤ ሚስት አግብቶ ቤተሰብ መሥረቶ ራሱን መምራት ይችላል ሲል እንጂ ከእግዚአብሔር አብ አባቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እናቱ ይለያል ማለቱ አይደለም፡፡ ይህ ሊነጻጸር የሚችለው ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ
ወደዚህ ዓለም መምጣት ጋር ነው፡፡ እርሱ ራሱን ዝቅ በማድረግ "ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴትን ታደርጋለች"(ሉቃ.1፡47) በማለት ራሱዋን
በቅድስና ጠብቃ ከነበረችው ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያነት ሰውነቱዋን ካጨችው በሙሽሪት ከተመሰለችው ዘንድ በመምጣት ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ
ነፍስ በመንሳት በምድር ስለመገለጡ ምሳሌ ነው፡፡
ነገር ግን እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል” የሚለው ቃል ለእግዚአብሔር ወልድና ለትስብእት ውሕደት ስንናገር እግዚአብሔር አብንና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ይተዋል ማለታችን እንዳልሆነ ለአዳምም እንዲሁ ነው፡፡ ስለአዳም “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል” ሲባል እግዚአብሔርን ይተዋል ፍቅሩ ይከፈላል እያለንአይደለም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን መስሎ ቤተሰቡን ይመራል ማለት ነው ልክ እንደ ክርስቶስ፤ እርሱ እጮኛው የሆነችውን ቤተክርስቲያንንና ቤተሰቡ የሆነውን እኛን ይመራናል፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው እኔ ይህን ስለ ክርስቶስና ስለቤተ ክርስቲያን እላለሁ፡፡”(ኤፌ.5፡31-33)
ነገር ግን እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል” የሚለው ቃል ለእግዚአብሔር ወልድና ለትስብእት ውሕደት ስንናገር እግዚአብሔር አብንና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ይተዋል ማለታችን እንዳልሆነ ለአዳምም እንዲሁ ነው፡፡ ስለአዳም “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል” ሲባል እግዚአብሔርን ይተዋል ፍቅሩ ይከፈላል እያለንአይደለም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን መስሎ ቤተሰቡን ይመራል ማለት ነው ልክ እንደ ክርስቶስ፤ እርሱ እጮኛው የሆነችውን ቤተክርስቲያንንና ቤተሰቡ የሆነውን እኛን ይመራናል፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ “ሰው አባትና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው እኔ ይህን ስለ ክርስቶስና ስለቤተ ክርስቲያን እላለሁ፡፡”(ኤፌ.5፡31-33)
ይህ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ የሥላሴ መልክ እንዳለ ለማስረዳት ያነሳነው
ፍሬ ነገር ነው፡፡ ስለዚህም ከላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት ወይም በትክክል እንደምናስተውለው እግዚአብሔር አብ አባት፣ እግዚአብሔር
መንፈስ ቅዱስ እናት፣ እግዚአብሔር ወልድ ልጅ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡ ይህ በሥላሴ የሚታየው አንድነትና ሦስትነት በሰው ዘንድ አለ፡፡ ይህን ጽንሰ
አሳብ ለማስረዳት ሥሉስትነት የሚል ስያሜ መስጠት ሳይሻል አይቀርም፡፡ እናም ይህ ሥሉስትነት በእኛ በሰዎች ዘንድም እንዲጸባረቅ
አድርጎ ሥላሴ እኛን ፈጥሮናል፡፡ ይህን በመረዳት ወደ አነሣነው ቁምነገራችን
እንመለስ፡፡
በሰዎች ዘንድ አባት፤ እናት እና
ልጅ አሉ፡፡ አባት በእግዚአብሔር አብ፣ እናት በመንፈስ ቅዱስ፣ ልጅ ደግሞ በእግዚአብሔር ወልድ ይመሰላሉ፡፡ እነዚህ በአካል ሲታዩ
ሦስት ቢሆኑም በመገኛቸው አዳም አንድ ናቸው፡፡ በፍቅር ሁለቱ ፆታዎች እርስ በእርሳቸው ይሳሳባሉ፡፡ በጋብቻ አንድ ጎጆን ይቀልሳሉ፣
በትዳርም አንድ ሥጋ በመሆን በአንድነታቸው ልጅን ይወልዳሉ፡፡ እነዚህ በአካል ሲታዩ ሦስት ቢሆኑም አንድ ባሕርይ አላቸው፡፡
በሥላሴ ውስጥ ያለው አንድነትና
ሦስትነት በሰው ዘንድ መታየት የጀመረው ከአዳም የጎን አጥንት ሔዋን በተገኘች ጊዜ ነበር፡፡ ያኔ በገነት እግዚአብሔር አብ እንደ
አባት፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደ እናት፣ እግዚአብሔር ወልድም እንደ ልጅ ተገኝተው፣ ቅዱሳን መላእክት በታደሙበት ልጃቸው
አዳም ከጎኑ አጥንት ከተገኘችው ከሔዋን ጋር ትዳርን ይመሠርት ዘንድ ታላቅ ድግስን ደግሱ፡፡ ይህ ድግስ የጠፋው ልጅ በተገኘበት
ወቅት እግዚአብሔር አምላክ በሰማያት የደገሰውን ድግስ ይመስላል፡፡ እግዚአብሔር የጠፋውን ልጅ
(አዳምን) ባገኘበት ጊዜ ባሮቹን “ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለውን ልብስ
አምጡና አልብሱት፤ ለእጁም ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ ስጡ፡፡ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፤ እንብላም ደስም ይበለን፡፡”(ሉቃ.፲፭፥፳፪—፳፬)ብሎአቸው
ነበር፡፡ ይህ ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ድግስ ነበር፡፡
እግዚአብሔር እንዴት ይህን በቅደም
ተከተል እንደከወነው ደግሞ እንመልከት፡፡ አዳም በተፈጥሮው ውስጥ ሥሉስትነት እንደተሠራ ይረዳ ዘንድ በገነት ለምድር እንስሳት ስምን
ያወጣው ዘንድ እግዚአብሔር ወደ እርሱ አቀረባቸው፡፡ እንስሳቱም ወንድ እና ሴት እየሆኑ ወደ እርሱ ቀረቡ፡፡ አዳም እንስሳቱ ጥንድ
ጥንድ እንደሆኑ አስተዋለ፡፡ ስለዚህም ለእርሱ ረዳት የምትሆነው አንዲት
ሴት እንደምታስፈልገው ወደ መረዳት መጣ፡፡ ሰውነቱም አጥብቆ ሻታት፡፡ ስለዚህም አዳም በውስጡ ያለውን እግዚአብሔርን የሚመስለበት
ባሕርይውን ወደ መረዳት ተመልሶአልና እግዚአብሔር “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም ረዳት የምትሆነውን እንፍጠርለት
” አለ፡፡( ዘፍ.፪፥፲፯)ስለዚህም አዳም በፍጹም ተመስጦ በመሆን ፍቅሩን፣ ረዳቱን ፣የኑሮ አጋሩን፣ እግዚአብሔር ሲያበጃት ይመለከት
ዘንድ በእርሱ ላይ ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፡፡ እንደምናውቀው ሥጋችን ሲያንቀላፋ ነፍሳችን አብራ አታንቀላፋም፡፡ በዚህም እግዚአብሔር
የሚያስተምረን አንድ ትምህርት አለ፡፡ እርሱም የኑሮ አጋራችንን በምንመርጥበት ወቅት የሥጋ ፈቃዳችንን በመከተል በሰሜት ሳይሆን
እንደ ነፍሳችን ፈቃድ በፍጹም ማስተዋል መሆን እንዳለበት ነው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ሂደት
ከክርስቶሰ ስቅለት ጋር አቆራኝቶ ሲያስተምር እንዲህ ይለናል ፡፡ “ዳግማዊው አዳም ክርስቶስ በሞት እንቅልፍ በመስቀል ላይ አንቀላፍቶ
ሳለ ቤተክርስቲያንን ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ አንጽቶ ከጎኑም በፈሰሰው ደም ቀድሶ መሠረታት የራሱም አደረጋት” ይለናል፡፡ ይህን ቅዱስ
ጳውሎስ ስለቤተ ክርስቲያንና ስለክርስቶስ በተናገረበት መልእክቱ “ባሎች ሆይ ክርስቶስ ደግሞ ቤተክርስቲያንን እንደወደዳት እንዲሁ
ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አጽንቶ ይቀድሳት ዘንድ ራሱን አሳልፎ ሰጠ”( ኤፌ.፭፥፳፭—፳፮) እንዲሁም “በገዛ
ደሙ የዋጃችን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን…” (የሐዋ.፳፥፳፰) በማለት
በግልጽ አስፍሮልን እናገኘዋለን፡፡
ስለዚህም አዳም አንቀላፍቷል ሲባል ባለማስተዋል ውስጥ ነበር ማለት
ሳይሆን ፣ ከሥጋዊና ከደማዊ አስተሳሰብ ርቆ ፍጹም በሆነ መንፈሳዊ መረዳት ውስጥ ነበር ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህም ነበር እግዚአብሔር
የፈጠራትን ሴት ወደ እርሱ ባቀረበለት ጊዜ በማስተዋል ላይ በተመሠረተ ምርጫ “ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋዋም ከሥጋዬ ናት እርሱዋ
ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ያለበት ምክንያት፡፡(ዘፍ.፪፥፳፬—፳፮) እንዲህ የማንል ከሆነ እርሷ ከእርሱ አካል ስለመገኘቱዋ እንዴት
ሊረዳ ቻለ ልንል እንችላለን ?
እግዚአብሔር
ከአዳም ልብ አጠገብ ከጎኑ አጥንት የናፈቃትን ረዳቱን ለአዳም አበጅቶ ሰጠው፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ማድረጉ ያለ ምክንያት
አልነበረም፡፡ ሚስቱ ትሆን ዘንድ ለተሰጠችው ሴት እስከሞት ድረስ ደርሶ ያፈቅራትና አኩያው መሆኑዋን ይረዳ ዘንድ ነው፡፡ ስለዚህም
አዳም እርሱዋን ሴት ትባል አለ፤ እንዲህ ሲል “ሚስቴ ትሁን” ማለቱ ነበር፡፡
በዚያን ጊዜ ሥላሴ በሰማያት ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ሰርግን ሰረገ፤
ቅዱሳን መላእክት በእንግድነት ታደሙ፤ ሰርጉንም አጥንትን በሚያለምልም መንፈሳዊ ዝማሬ አደመቁት “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም
ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” ብለው ዘመሩ፡፡(ሉቃ.፪፥፲፬) ምክንያቱም የጌታ ልደትና መንፈሳዊ ጋብቻ በይዘታቸው ይመሳሰላሉና፡፡ እግዚአብሔርም በቃል ኪዳን ቃል “ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል
ከሚስቱም ይጣበቃል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው፡፡”(ዘፍ.፪፥፳፬፤ማቴ.፲፱፥፮)
በማለት አንድነታቸውን አጸናው፡፡ ትዳሩ በዚህ መልክ በገነት ተፈጸመ፡፡ ከዚህም በኋላ ነበር በእግዚአብሔር ያለው ሦስትነትና አንድነት
በአዳምና በሔዋን መታየት የጀመረው፡፡
እኛም ልጆቹ መጽሐፍ ቅዱስ “ዐሥራትን የሚቀበል ሌዊ ስንኳን በአብረሃም በኩል ዐሥራትን ሰጠ፡፡”(ዕብ.7፡9)ብሎ እንደገለጠልን ከአዳም ጎን አጥንት ነበርን፡፡ ከዚህ አንድ ነገርን እናስተውላለን፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ እንደተገኘ እንዲሁ ከአዳም በአፈጣጠር የምትስተካከለው ሔዋን ተገኘች፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እንዲሰርጽ እንዲሁ ሔዋንም ከአዳም ከነፍሱ ነፍስን ነስታ ተገለጠች፡፡ ይህም እኛ ሰዎች በሥላሴ አርአያና አምሳል ስለመፈጠራችን ምስክር ነው፡፡
እኛም ልጆቹ መጽሐፍ ቅዱስ “ዐሥራትን የሚቀበል ሌዊ ስንኳን በአብረሃም በኩል ዐሥራትን ሰጠ፡፡”(ዕብ.7፡9)ብሎ እንደገለጠልን ከአዳም ጎን አጥንት ነበርን፡፡ ከዚህ አንድ ነገርን እናስተውላለን፡፡ እርሱም እግዚአብሔር ወልድ ከእግዚአብሔር አብ እንደተገኘ እንዲሁ ከአዳም በአፈጣጠር የምትስተካከለው ሔዋን ተገኘች፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከአብ እንዲሰርጽ እንዲሁ ሔዋንም ከአዳም ከነፍሱ ነፍስን ነስታ ተገለጠች፡፡ ይህም እኛ ሰዎች በሥላሴ አርአያና አምሳል ስለመፈጠራችን ምስክር ነው፡፡
ቢሆንም ሰው በገነት በቅድስና ጸንቶ መቆየት ተሣነውና በመተላለፍ ወደቀ፡፡
ውድቀቱን ያልወደደው እግዚአብሔር አዳምንና ልጆቹን ዳግም እንዳይወድቁ አድርጎ ሊያነሣቸው ሰማያዊ ጋብቻን ከእነርሱ ጋር መሠረተ፡፡
መንፈሳዊ ጋብቻ በጌታ ልደት ይመሰላል፡፡ በጌታችን ሰውነት በኩል መለኮትና ሰው አንድ እንደሆኑ እንዲሁ በመንፈሳዊ ጋብቻ ይህ ፍጹም
የሆነ አንድነት በባልና በሚስት እውን ይሆናል፡፡ ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሲፀነስ ከወንድ
ፈቃድ ወይም ከሥጋ ፈቃድ አልነበረም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ግብር ፍጹም በሆነ መንፈሳዊ ፈቃድ ነው እንጂ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችንም
የሚፈጸመው መንፈሳዊ ጋብቻ እንዲሁ ከሥጋ ፈቃድ ፈጽሞ የራቀና በመንፈሳዊ መረዳት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
ይህ የመሰለ መንፈሳዊ ጋብቻን በምድር ይፈጽም ዘንድ እግዚአብሔር አብ
ወደዚህ ዓለም ልጁን ላከው፡፡ ለእርሱ የታጨነው እኛ ክርስቲያኖች ነን፡፡ እኛ ደግሞ በመንፈሱ አንድ ሆነን ቤተ ክርስቲያን ተሰኝተናል፡፡
ስለዚህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርሱ ወደ ታጨችው ቤተ ክርስቲያን መጣ፡፡ ሚዜዎቹ በነቢያት ይመሰላሉ፡፡ የሚወከሉትም
በመጥምቁ ዮሐንስ ነው፡፡ ስለዚህም መጥምቁ ዮሐንስ “ሙሽራይቱ ያለችው
እርሱ ሙሽራ ነው፡፡ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል፡፡ እንግዲህ ደስታዬ ተፈጸመ አለ፡፡(ዮሐ.፫፥፳፱—፴)
ሚዜዎች ሆይ እናንተም ለሙሽሪትና ለሙሽራው “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው” በሉ፡፡
ሰርጉ ፍጹም ሰማያዊ ከመሆኑ የተነሣ የተሠዋው ፍሪዳ እስከ ዓለም ፍጻሜ
ለሚነሡት ወደ ሠርጉ ለተጠሩት ሁሉ የሚበቃ ነው፡፡ የእግዚአብሔር በግ የተባለውም ራሱ ሙሽራው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የሰርጉ ባለቤት እግዚአብሔር አብ ሲሆን ድግሱንም የሚያስፈጽመው መንፈስ
ቅዱስ ነው፡፡ በድግሱም ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን መላእክት በአጸደ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን ነፍሳት በፍስሐው ይታደማሉ፡፡ ቤተ
ክርስቲያንም የተሰኘነው እኛ እነሆ አሁን ተገኝተናል፡፡ እነዚህ ቅዱሳን በአንድነት ሆነው እጅግ ማራኪ በሆነው በዚህ የሠርግ ሥነ ሥርዐት
ላይ ታድመው ጣዕም ያለውን መንፈሳዊ ዝማሬን ያቀርባሉ፡፡ ድንግል ማርያምም ፍሬዎቹዋን በዐይኖቹዋ ተመልክታቸዋለችና በደስታ ትባርካቸዋለች፡፡
እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም የልጆቻቸውን ጋብቻ በዚህ ሰማያዊ ሥርዓት በመፈጸሙ ደስ ተሰኝተዋል፡፡ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የት አለ? “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት
እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶአልና፡፡”(ዮሐ. ፫፥፲፮) ስለዚህም
ጌታችን እንዲህ አለ “የሙሽራው ክንድ በሙሽሪት ላይ አንደሆነ የእኔም ቀንበር እኔን በሚያውቁት ላይ ነው፡፡ ሙሽራውና ሙሽሪት የሚሞሸሩበት
የሙሽርነታቸው አዳራሽ በውበት እንደተጌጠ እንዲሁ የእኔም ፍቅር በእኔ ያመኑብኝን ያስጌጣቸዋል”(ማኀልየ ማኅልይ ዘሶሪያ)
መልካም ጋብቻ
ለተጋቢዎች ይሁንላችሁ
No comments:
Post a Comment