Saturday, January 28, 2012

የእውነተኛ ጸሎት ባሕርያትና ውጤቱ (ከስምዖን ሶርያዊ)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
19/05/2004
መግቢያ
ይክበር ይመስገንና የጥንት ክርስቲያኖች ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ሕይወት ይኖራቸው ዘንድ ራሳቸውን የሚያስተካክሉበት የጽሙና ጊዜና ቦታ ነበራቸው፡፡ ቤታችውንም ሲያንጹ የጸሎት ቤትንም ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህች የጸሎት ቤት ጸሎት የሚያደርሱባት ብቻ ሳትሆን ቤተመጻሕታቸውም ናት፡፡ ለእነርሱ ሰገነታቸው እርሱዋ ናት እግዚአብሔር በዚያ ያስተማራቸውን ለማኅበራዊ ሕይወታቸው ማጣፈጫ አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ ይህ ሕይወት የትህርምት ሕይወት ተብሎ ይታወቃል፡፡
 ይህ ሕይወት ከምንኩስና ሕይወት ፈጽሞ የተለየና ማንም ክርስቲያን ሊተገብረው የሚችል ምናልባትም ከምንኩስና ሕይወት የሚልቅ ሕይወት ነው፡፡ ክርስቶስ ቀን ቀን ሕዝቡን ካስተማረ በኋላ ማታ ማታ ወደ ደብረዘይት ተራራ በመሄድ በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ ይህ ግን እርሱ ተገብቶት ሳይሆን ለእኛ አብነት ሊሆነን በመሻት ነው፡፡ በትህርምት ሕይወትም ጸሎትን የምንጸልይበትና መንፈሳዊ መጻሕፍትን የምንመረምርበት ጊዜና ቦታ ሊኖረን ግድ ነው፡፡ በጨለማ ከአምላክ የተማርነው በተግባራዊ ሕይወታችን ለዓለሙ ሰባኬያነ ወንጌል በመሆን ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡ በዚህ ሕይወታችን በጥምቀት ያገኘነው የክህነት ሥልጣን ተግባራዊ ይሆናል(royal priesthood ይህን ለመረዳት “እናንተ የመንግሥቱ ካህናት ናችሁ የሚለውን ጽሑፌን ይመልከቱ) በዚህ ሕይወቱ እጅግ የሚታወቀው ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ እርሱ ጌታውን በመሰለ ሕይወት ይኖር ነበር፡፡ ማታ ማታ በጸሎትና መንፈሳዊ መጻሕፍት በመመርመር ሲተጋ ቀን ቀን ደግሞ ሕዝቡን በማስተማር ይተጋ ነበር፡፡ ወደፊት ይህን አስመልክቶ መጽሐፍ ይኖረኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ላይ የትህርምት ሕይወት ሲባል ይህን ሕይወት እንደሆነ አንባብያን እንዲያስተውሉልን በትሕትና እጠይቃለሁ፡፡   

ሥራ ፈትነት ለብዙ ኃጢአቶች መወለድ በር ይከፍታል” ተብሎ ተጽፎአል፡፡ በትህርምት ሕይወት የሚኖር ክርስቲያን ጸሎት የማያደርስ ከሆነ እርሱ ሥራ ፈት ነው ፡፡ ቅዱሳን አባቶች ከሌሎች አግኝተው ለእኛ እንዳስተማሩን በእግዚአብሔር አገልግሎት የተጠመደ ሰው እርሱ በጸሎት እየተጋ  ነው ፡፡እኔ እንደማምነው “ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል”(መዝ.፩፥፪) እንዲል ነቢዩ ዳዊት በመልካም ሥራ በመትጋት ሕጉን ለመፈጸም የሚታትር ከሆነ እርሱ በእውነት ያለማቋረጥ እየጸለየ ነው፡፡ ይህ ክርስቲያን ወደ ተሟላ መንፈሳዊ ከፍታ ሲደረስ፣ አመለካከቱም በመንፈስ ቅዱስ ሲታደስና ፍጹም ሰላምን ሲያገኝ፣ አንዲሁም አእምሮው በእግዚአብሔር ፍቅር ሲያዝ  እግዚአብሔር የዚህን ታራሚ ልቡና መገለጫው አድርጎታል ማለት ነው፡፡

ጸሎት በትምህርት የሚገኝ ወይም በእውቀት መጠን ወይም ቃልን አሰምቶ በመድገም የሚገለጥ አይደለም ፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ጸሎት ራስን ባዶ በማድረግና ንቁና ጸጥ ባለ አእምሮ አንዲሁም የስሜት ሕዋሳቶቻችን ጸጥ በማሰኘት የምናገኘው የተመስጥኦ ውጤ ነው፡፡ ይህም ማለት ሕሊናችንን ከማንኛውም አስተሳሰብና ዓለማዊ ጥንቃቄ ንጹሕ በማድረግ የምናገኘው ነው ፡፡
በጸሎት ሰዓት ለብቻ መሆን ይመረጣል ፡፡ እንዲህ ከሆነ ጸሎታችንን ከሚያደነቃቅፉ ክፉ አሳቦች ርቀን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እንችላለን ወይም ጸሎታችንን ከሚያደነቃቅፉ መልካም ነገሮች ይጠብቀናል ፡፡ ልጁን በማር የገደለ ሰው ልጁን በስለት ከገደለ ሰው አይለይም ፡፡ እንዲሁ ጸሎትን በመልካምም ይሁን በክፉ አስተሳሰቦች መስተጓጎል አይገባም ፡፡ እንዲያ ከሆነ ግን ውጤቱ ፍሬ አልባ ነው ፡፡ ጸሎቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ አይሰማለትም ፡፡
ለመጸለይ ካሻህ ከሕሊና ጫንቃህ ላይ ያኖርካቸውን ዓለማዊ እውቀቶችን አውርድህ አስወግዳቸው ፡፡ከዚህም ጋር አስተባብረህ ራስህን ከዓለማዊ ጥንቃቄና ፈሊጥ ነጻና ንጹሕ አድርገህ በፍጹም ተመስጦ ፈጽም ፡፡ ልጆችህን (መልካምና ክፉ አሳቦችህን) ከእጆችህ በታች ሰብስባቸው ፡፡ በጸሎት ሰዓት በሕሊናህ የሚታሰቡትን ሁሉ ከአንተ አርቅ ፡፡ የተተገበሩትንም ያለተተገበሩትንም አስተሳሰቦችን በመስቀል  በመቸንከር ወደ አዲሲቱ ዓለም ግባ ፡፡ ራስህን ከማንኛውም አስተሳሰብ ንጹሕ ባደረግህ በኋላ ለጸሎት ተነሥ ፡፡ እንዲያ ከሆነ ምናልባት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ብትሆን እንኳ ሰላም የሞላበት ጸሎትን መጸለይ ይቻልሃል ፡፡
ሕመምህን እያዳመጥኽ ለእርሱ ምን ማድረግ አለብኝ እያልኽ ፣ወይም ሕሊናህ በክፉ አሳብ ሞልተህ እግዚአብሔር የሚወደውን  ጸሎት ማድረስ አይቻልህም ፡፡ ነፍስ ከእነዚህ ነገሮች ንጹሕ ሳትሆን በጸሎት ደምቃ ልታበራ አይቻላትም ፡፡ በውስጥህ በአንድ ሰው ላይ እንኳ ቢሆን ያጎነቆለች ትንሽ ቁጣ ብትኖር ንጹሕ በሆነ መንገድ መጸለይ ይቻለኛል ብለህ አታስብ ፡፡
ፍቅር በውስጡ የያዘ ጸሎት የማይነጥፍ የውኃ ምንጭ ነው ፡፡ ነፍስን በሰላምና በደስታ ውኃ ያረሰርሳታል ፡፡ ይህ የሚሆነው የልባችን ምንጮች በፍቅር የተነደሉ እንደሆነ ነው ፡፡ ለዚህ መንደያ እንጨቱ የእኛ ቅን ፍርድ ነው ፡፡ አእምሮአችን መልካም አስተሳሰቦችን በተመስጦ የሚያመላልሳቸው ከሆነ የፍር እሳት በልባችን ውስጥ  ይቀጣጠላል ፡፡ እንደ ቡቃያ የሆነችው ጸሎታችን እንድትጠነካክር በመንፈሳዊ እውቀት ብርሃን እንድታበራ ከእርሱም ልትመገብ ይገባታል ፡፡ እንዲህ ከሆነ ፍጹም ሰላማዊና ደስታ የሚፈልቅበት ፣ መዓዛው መልካም እንደሆነ እጣን ያለማቋረጥ የሚያውድ ጸሎትን ማቅረብ ይሆንልናል ፡፡ …
ከንጹሕ አእምሮ የሚመነጭ እውነተኛ ጸሎት ልብን ከሃዘንና ከትካዜ ንጹሕ አድርጎ የደስታን እንባ በፈቃደኝነት እንድናነባና ነፍስ ወደ አምላኩዋ እንድትቀርብ የሚያበቃት ነው ፡፡ የዚህን ጸሎት ጣዕም ያጣጣመች ነፍስ ብፅዕት ናት ፡፡ የሥጋ ድካም የሌለበት በልብ ብቻ የሚፈጸመው ጸሎት ፣ ልብም በአእምሮ ታግዛ በማስተዋልና በመረዳት በተመስጦ እግዚአብሔርን በማሰብ ሃዘን ባልተቀላቀለበት ከውጭ በልብ ላይ እንደሚሰፍ ሳይሆን እንደ ቡቃያ ከሆነ ነገር ግን ካልተጠነካከረ ከውስጥ ከሚፈልቅ ጸሎት የሚገኝ መንፈሳዊ ሀብት ነው ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ደረጃ ላይ ሳለህ አእምሮህ በሌላ ነገር ከተሳበ ጸሎትህ ይቋረጣል ፡፡ ስለዚህም በተሟላ መልኩ ጸሎት ማድረግ ይሳንሃል ፡፡
ጸሎት ውስጣዊ ምልከታ ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ምሥጢራዊ በሆነ መንገድ በልባችን ተተክሎ ያለውን መልካም ነገር የምናስተውልበት መስታወት ነው ፡፡ ፍጹም የሆነ ጸሎት የምንለው አእምሮአችን ያለማቋረጥ የምስጋናን መዝሙር በመላእክት ልሳን ለአምላኩ ያቀረበ እንደሆነ ነው ፡፡ አባቶቻችን አንዳስተማሩን የሰናፍጭ ቅንጣትን የመሰለው የጸሎት ዓይነት ገና ስንፈጠር ጀምሮ  የእግዚአብሔር መንግሥት በተባለው ተፈጥሮአችን ውስጥ የተዘራው እውቀት ነው ፡፡ ዘሩም ልዩ ልዩ ዓይነት እውቀቶችን እያፈራ ያድጋል ፡፡
አስተዋይ በእነዚህ ቅርንጫፎች ተወጣጥቶ ከፈጣሪው ዘንድ ይደርሳል ፡፡  ይህ ሰው የመግረዣውም መሳሪያ በሁለቱ መሠዊያዎች ቅርጫፎች ላይ የተንጠለጠሉትን የማስተዋል ፍሬዎችን በመሰብሰብ በሰማያዊው መሠዊያ ላይ ይቀርቡ ዘንድ መሥዋዕት አድርጎ ያዘጋጃቸዋል ፡፡ በተለይ ማስተዋልን ገንዘባቸው ያደረጉ ቅዱሳን በእነርሱ ውስጥ ባለው ማስተዋል ቀስ በቀስ በሆነ ልምምድ መሥዋዕቱን ፍጹም በማድረግና በመሞት(በመሠዋት)ተአምራዊ በሆነ መንገድ ድጋሚ ሕያው ሆነው ይነሣሉ ፡፡ እንደ ተስፋ ቃሉ በዚህ ምድር ሳለ በመጠኑ ጣዕሙን የምንቀምስበት ነገር ግን ለአንዴና ለሁል ጊዜ በመጪው ዓለም ከሥጋ እስራት ነፃ ወጥተን የምናጣጥመው ይህን ሕይወት ነው ፡፡
በዓለም ዙሪያ ያሉ ፣ መልካም ሥነምግባር በመፈጸም የሚተጉ ፣ በምድር መልካም የሆነ ብድራትን ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሰጣቸው በመሻት ወይም የገሃነም ቅጣት ፈርተው ወይም በምትመጣው ዓለም የምትሰጠውን ተድላና ደስታ ሽተው በጸሎት የበረቱ ወገኖች አሉ ፡፡ ነገር ግን እውነተኛ የትህርምት ሕይወትን የሚመራ ክርስቲያን የእርሱ ጸሎት ፣ ተማጽኖ ፣ በንስሐ መትጋት እንዲሁም ማንኛውም እርሱን ወደ ፍጹምነት የሚያደርሱትን መንፈሳዊ ሥራዎችን ሁሉ ማከናወኑ ከሥጋዊ ፈቃድ ራሱን ነፃ ለማውጣት ነው ፡፡ ይህን ዓላማ ሰንቆ በጸሎት የሚተጋ ከሆነ ለቅድስና ማዕረግ ይበቃል ፡፡ እነዚህ ትጋቶች እርሱን ክርስቶስን እንዲመስል ያበቁታል ፤ በሚረዳ መልኩም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በሰውነቱ ሲፈጸም ለመመልከት የበቃ ይሆናል ፡፡
በንጽሕና የሚቀርብ ጸሎት በስተመጨረሻ ማስተዋልን ፣ የሕሊና እርጋታን ፣ የአእምሮ እረፍትን ፣ የሰከነ አስተሳሰብን ፣ መጪውን ዓለም መናፈቅን ፣ ውስጣዊ ምቾትን ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ተሰልፎ ሰይጣንና ሠራዊቱን መውጋትን እንዲሁም  እግዚአብሔር የሚፈጽማቸውን ምሥጢራት ለመመልከት የመብቃት ፍሬዎችን ያፈራል ፡፡
መላ የሕይወት ዘመኑን በትህርምት ሕይወት የሚመራ ሰው ግቡ ከሁለተኛው የእውቀት ከፍታ በማለፍ ወደ በለጠው የእውቀት ከፍታ መሸጋገር ነው ፡፡ ሁለተኛው የእውቀት ማዕረግ የነፍስ የእውቀት ማዕረግ ይባላል ፡፡ ከዚህ የእውቀት ከፍታ አንድ ክርስቲያን ከፍ ሲል ከሁሉ ወደሚልቀው እውቀት ይሸጋገራል ፡፡
ሳያቋርጥ በመጸለዩ ወደ ፍጹምነት ማዕረግ ስለደረሰ ሰው ባሕርይ ቅዱስ ባሲልዮስ ሲጽፍ እንዲህ ብሎአል፡- “በዚህ ማዕረግ ላይ ያለ ሰው ስለሁሉ ነገር ለእግዚአብሔር ምስጋናን ያቀርባል ፤ ከተፈጥሮም ጋር ባለውም መስተጋብር ሁሉ ፣ በማየት ፣ በመስማት ፣ በዚህ ዓለም ስለሚተገበሩት መልካምም ክፉም ምግባራት ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ፡፡ ስለክፉ ሥራዎች እንዴት ብሎ አምላኩን ያመሰግናል ቢባል ስለትዕግሥቱ ፣ ለሰዎች ልጆች ስላለው ጥልቅ ፍቅር ፣ እንዲም በእነርሱ የክፋት ሥራ የእግዚአብሔር ቅድስና ጎልቶ ስለሚታይ ፣ ቸርነቱን እያሰበ ንጽሕናውን እያሰበ ፣ ክፉውን የሚጸየፍ መሆኑን እያሰበ እግዚአብሔር አምላኩን ያለማቋረጥ ያመሰግናል ፡፡” እግዚአብሔርን የጻድቁን ማስተዋል ለእኛም ያድለው፡፡

3 comments:

  1. በጣም ደስ ይላል ይሄንን ድረ ገጽ እስከዛሬ አለማየቴ ቆጨኝ፡፡

    ReplyDelete
  2. በጣም ደስ ይላል ይሄንን ድረ ገጽ እስከዛሬ አለማየቴ ቆጨኝ፡፡

    የምፈልገውን ትምህርት በማግኘቴ እግዚአብሔር በእድሜ በፀጋ ያቆይልኝ ብያለው አሜን፡፡

    ReplyDelete
  3. እግዚአብሔርን የጻድቁን ማስተዋል ለእኛም ያድለው፡፡
    Amen Qalehyweten Ysemalen Ymengesetu Werashe Ysemu Qedashe Yadergeln Amen::

    ReplyDelete