ከዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
20/05/2004
ለስሙ ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ስቅለቱ ተፈጥሮአዊ
ሥርዐታትን ሁሉ በመሻር እኛም እንደርሱ ከፍጥረታዊ ሕግ በላይ እንድንሆን አበቃን፡፡ አስቀድሞ ከተፈጥሮአዊ
ሕግ ውጪ ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለወንድ ዘር ተፀነሰ፤ በኅቱም ድንግልናም ተወለደ፤ እንደንግሥናው ማረፊያውን ከንጉሥ እልፍኝ
ያደርግ ዘንድ የሚገባው ጌታ ከከብቶች በረት እንስሳት እስትንፋሳቸውን እያሟሟቁት ተገኘ፡፡ ድንግል ከሆነችም ክብርት ብላቴና ጡት ጠብቶም እንደ ሕፃናት አደገ፡፡ በአይሁድ ሥርዐት ሙሉ ሰው እስከሚባልበት እስከ ሠላሳ እድሜው ድረስ ሁሉን በቃሉ የፈጠረ አምላክ ዝምታን መረጠ፡፡
እርሱ ሁሉን ማድረግ ሲቻለው በቅናት ተነሣስተው በእርሱ ላይ
የስድብን ቃል በተናገሩት ላይ ስለክፋታቸው በብድራት ክፋትን አልመለሰላቸውም፡፡ ይልቁኑ “…አባቴን አከብረዋለሁ እናንተ ግን ታዋርዱኛላችሁ”
ብሎ በትሕትና ቃል መለሰላቸው፡፡(ዮሐ.8፡49) ከፍጥረታዊው ሕግ ውጪ በጭቃ የዕውሩን ዐይኖች አበራ፡፡ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር
ሆኖ እግዚአብሔርን ይሳደባል ብለው ከሰሱት፡፡ ወንጀለኞችን በሲኦል የሚቀጣ እንደ ወንጀለኛ ተቆጠረ፡፡ አሕዛብ ለእግዚአብሔር የቀኑ
መስሎአቸው ሊቀኑለት በሚገባው አምላካቸው ላይ ተዘባበቱበት፡፡ በጥፊ መቱት የረከሰ ምራቃቸውንም ተፉበት እርሱ ግን በምራቁ እርሱን
ሰምተው መንጎቹ ይሆኑ ዘንድ ጆሮአቸውን ኤፍታህ ብሎ ከፈተላቸው፤(ማር.7፡35) አርዓያቸውንም ይለዩበት ዘንድ ዐይኖቻቸውን በምራቁ አበራላቸው፡፡(ዮሐ.9፡8) አይሁድ በወንጀለኛው ምትክ ቅዱስ የሆነውን ክርስቶስን ይሰቅሉት ዘንድ ተማከሩበት፡፡
አምላክ ሰው በመሆን በደሙ እንዲቤዣቸው ተስፋ ይሆናቸው ዘንድ በሕግ መሥዋዕትን ያቀርቡ የነበሩ አይሁድ ኃጢአታቸውን
አስወግዶ ሕሊናቸውን ንጹሕ የሚያደርገውን እውነተኛውን የእግዚብሔር በግ በአካል ባገኙት ጊዜ በእርሱ ደም ከመዳን ይልቅ "ደሙ በእኛና
በልጆቻችን ላይ ይሁን" በማለት እዳ በደል ሆነባቸው፡፡(ማቴ.27፡25)በባሕርይው ሕማም የሌለበት ጌታ የእኛን ሥጋ ገንዘቡ በማድረጉ በእርሱ ገላ ላይ ያሳረፉት ግርፋት እስከ አጥንቱ ድረስ ተሰማው፡፡ ዓለምን በመሃል እጁ የያዘው ጌታ የእኛን ሰብእና ገንዘቡ አድርጎአልና መስቀሉን ተሸክሞ ቀራንዮ
ኮረብታ ለመድረስ ጉልበቶቹ ዛሉ፡፡ እግዚአብሔርን እናቃለን የሚሉ የአይሁድ ካህናት ፈጣሪያቸውን ለአሕዛብ ገዢዎች አሳልፈው ሰጡ፡፡ አሕዛብም ለእግዚአብሔር
ቀንተናል በማለት አምላካቸው ላይ የጭካኔ ክንዳቸውን አሳረፉ፡፡ እርሱ ግን ልክ "በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ" ተብሎ እንደተጻፈለት ሆነ፡፡ ነገር ግን ከእናቶች ዘንድ ሲደርስ እንደነዚህ ጨካኝ የሆነ አምላኩን የማያውቅ ትውልድና ለመንጋው የማይራሩ እረኞች በኋለኞቹ ዘመናት ይነሣሉና ይህን ለማሳሰብ ሲል ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ “መካኖችና ያልወለዱ ማኅፀኖች ያላጠቡ ጡቶች ብፁዓን ናቸው”(ሉቃ.23፡29)ብሎ
ተናገራቸው፡፡
ኃጥአንን ከኃጢአታቸው የሚያነጻቸው እርሱ በሰው ልጆች
ላይ ሠልጥነው የነበሩትን ሞትንና ሲኦልን በሞቱ ድል ሊነሣቸው በመስቀል ላይ እጆቹ ተቸነከሩ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን “የሚያደርጉትን አያቁምና
አባት ሆይ ይቅር በላቸው” በማለት ፍጹም ሙሉ የሆነውን ፍቅሩን ከማሳየት ውጪ አንድም የበቀል ቃልን አላሰማም ነበር፡፡ ለፍጥረት
ሕይወት የሆነው እርሱ ነፍሱን በራሱ ሥልጣን ከሥጋው ለያት፡፡ እንደ ፍጡርም ሞትን ቀመሰ ወደ መቃብርም ወረደ፡፡
በነፍሱም እንደፍጡር በሲኦል በመገኘት በሲኦል ለነበሩት ነፍሳት የምስራች አላቸው፡፡ በአዳም ስብከት አምላካቸውን
በናፍቆት ሲጠባበቁ የነበሩ ነፍሳት ጌታቸው ለአዳም አባታቸው እንደገባው እንደተስፋ ቃሉ በመካከላቸው በመገኘቱ እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡
አዳም በገነት ድምፁን የሰማውን አምላክ ገጽታ በነፍስ ዐይኖቹ ተመለከተው፣ ሔዋን በገነት ያሳዘነችውን ፈጣሪዋን በነፍስ ዐይኖቿ ለመመልከት በቃች ፡፡ ከሰማያውያን
መላእክት ይልቅ እጅግ የላቀ ምስጋና በሲኦል ተሰማ፡፡ ሰይጣንና ሠራዊቶቹ ከኃያሉ ጌታ መሸሻ መደበቂያ ስፍራ አጡ፡፡ ነገር ግን ነፍሳት በጌታችን የምሕረት ክንፎች ተሳፍረው ሲኦልን ጥለው ወደ ገነት ሲገቡ
አጋንንትም ከነፍሳት ባዶ ወደ ሆነችው ስፍራቸው ወደ ሲኦል ተመለሱ፡፡ በሦስተኛው
ቀንም ከተፈጥሮዊ ሥርዐት ውጪ እንደ አልዓዘር መቃብሩ የተገጠመበት ድንጋይ ሳይነሣ መግነዙንም ሰዎች ሳይፈቱለት በኅቱም ድንግልና
እንደተወለደ ከኅቱም መቃብር ሞትን ድል በመንሳት ተነሣ፡፡
ይህን የድኅነት ሥራ ሠርቶ በመፈጸምም ወደ መቃብር እንጂ ወደ ላይ ወደ አርዓያም መነጠቅ የማይችለውን ሰብእናችንን በተዋሕዶ ገንዘቡ አድርጎታልና በእርሱ ባሕርያችን በፍጡራን ዘንድ ተመለከ፡፡
ኦ አፍቃሪያችን ክርስቶስ ሆይ ለእኛ ያለህ የፍቅርህ ከፍታ እንዴት ግሩም ነው!!! ለእኛ ያለህ ፍቅር እንደ አንተ
ወሰን አልባ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ብቻ አላደረግህልንም፡፡ ጌታ ሆይ ጥምቀትን በራስህ ጥምቀት በመባረክ ከተፈጥሮአዊ ሥርዐት ውጪ ከውኃና ከመንፈስ መንፈሳዊ ልደትን ሰጠኸን፡፡
እንዲህም ስለሆነ ልደታችን በምድር መኖሪያችን በሰማያት ሆነ፡፡ አሁን ግዛታችን በሆነችው ሰማይ የምታበራ ፀሐይ አታስፈልገንም፤ ጨለማም የለባትም፤ በጨለማ የሚያበሩም ጨረቃና ከዋክብት አላስፈለጉዋትም ቀንና ሌሊት አይፈራረቁባትም ቀናትና ወራት እንዲሁም አዝማናት አይቆጠሩባትም፡፡ ፀሐያችን እርሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ነቢዩ
ዳዊት “በኃጥአን ድንኳን ከመቀመጥ ይልቅ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ”(መዝ.83፡10) ብሎ የተመኛት ሥፍራ ይህቺ ናት፡፡
እነሆ አሁን እኛ በጥምቀት የዚህች ሰማያዊት ሥፍራ ዜጎች ስለሆንን የቀን ልጆች ተባልን፡፡
ይህቺን ቀን ቅዱሳን ስምንተኛዋ ቀን ይሉዋታል፡፡ ከምድራዊያኑ
ሰባቱ ቀናት ውጪ ያለች ቀንና ሌሊት የማይፈራረቁባት መላእክት ከትመውባት የሚኖሩባት ሁሌም በመለኮታዊ ብርሃን ብሩህ ሆና የምትኖር ይህችን ስፍራ ስምንተኛዋ ቀን ይሉዋታል፡፡ በተለምዶም ይህቺን ቀን ስምንተኛው ሺህ የሚሉዋትም አሉ፡፡ እንዲህም ማለታቸው በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲቱ ቀን እንደ ሺህ ሺህም
ቀን እንደ አንዲት ቀን ስለሚቆጠር ነው፡፡ አንድም ሺህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘለዓለማዊነትን የሚገልጥ ቁጥር ነውና ስምንተኛው ሺህ ሲሉ
ለዘለዓለም ከአምላክ ጋር የምንኖሩባት የማታልፈዋ ቀን ሲሉን ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በውስጡዋ ነዋሪዎቹዋ ስለሆንነው ስለእኛ ሲናገር “እናንተ … የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና”
ብሎ መሰከረ፡፡ ይህቺ ናት የክርስቲያኖች ሰንበት በእርሱ ያመንን ከክርስቶስ ጋር የገባንባት የዕርፍት ቀናችን፡፡(ዕብ.4:10) ነገር ግን ሐዋርያው “ድንኳን
የሚሆነውን ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን
እናውቃለንና፡፡…በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ በድንኳኑ ያለን እና
ከብዶን እንቃትታለን፡፡”(2ቆሮ.5፡1-5) እንዲል (እርሱም በጥምቀት የለበስነው ዘለዓለማዊ ልብሳችን ክርስቶስ ነው) እኛም ይህን
ሰማያዊ መኖሬአችንን እንዳናጣ ኃጢአትን ደምን እስከማፍሰስ ድረስ ደርሰን ልንቃወመው ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለዚህ ክብር
የበቃን ያድርገን ለዘለዓለሙ አሜን!!
ይህቺን ቀን ቅዱሳን ስምንተኛዋ ቀን ይሉዋታል፡፡ ከምድራዊያኑ ሰባቱ ቀናት ውጪ ያለች ቀንና ሌሊት የማይፈራረቁባት መላእክት ከትመውባት የሚኖሩባት ሁሌም በመለኮታዊ ብርሃን ብሩህ ሆና የምትኖር ይህችን ስፍራ ስምንተኛዋ ቀን ይሉዋታል፡፡ በተለምዶም ይህቺን ቀን ስምንተኛው ሺህ የሚሉዋትም አሉ፡፡ እንዲህም ማለታቸው በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲቱ ቀን እንደ ሺህ ሺህም ቀን እንደ አንዲት ቀን ስለሚቆጠር ነው፡፡ አንድም ሺህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘለዓለማዊነትን የሚገልጥ ቁጥር ነውና ስምንተኛው ሺህ ሲሉ ለዘለዓለም ከአምላክ ጋር የምንኖሩባት የማታልፈዋ ቀን ሲሉ ስምንተኛው ሺህ አሏት፡፡
ReplyDelete