ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004
አምላክ ሆይ በነቢዩ ኢሳይያስ “ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል ጻድቅ ባርያዬ
በዕውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል ኃጢአታቸውንም ይሸከማል፡፡”(ኢሳ.53፡11) ተብሎ አስቀድሞ የተናገረው እውን ሆኖ ዛሬ በዐይናችን ተመለከትነው፡፡
ጌታ ሆይ! በሕማምህ ወለድከን፤ በጥምቀትም ከሞትህ ጋር በመተባበር በመንፈስና በእሳት በመጠመቅ እሳታውያንና መንፈሳውያን የሆኑ መላእክትን መሰልናቸው፡፡ ስለዚህም በእደ ዮሐንስ በባሕረ ዮርዳኖስ በመጠመቅ ለእኛ ጥምቀትን የመሠረትክባት ይህቺን ዕለት በታላቅ መንፈሳዊ ደስታና ፍቅር እንዲሁም በታላቅ ተመስጦ
ሆነን እናከብራታለን፡፡
ጌታ ሆይ ልጆችህ ልዩ ልዩ ሕብረ ቀላማት ባላቸው አልባሳት አጊጠውና ደምቀው ቅዱስ ሥጋህንና
ክቡር ደምህን ከተቀበሉበት ማዕድህ፣ አምሳለ መስቀል ከሆነው ከምሕረት ቃል ኪዳን ታቦትህ ፊት ሆነው፣ በሐዋርያት ለአንተ ለሰማያዊው ሙሽራ የታጩበትን ቀን ነፍስን በሐሴት በሚሞላ መንፈሳዊ ዝማሬና በታላቅ ደስታ ሆነው ሲያከብሩ ከላይ ከአርዓም ተመልከት፡፡