በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/05/2004
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከእናቱ ማኅፀን ሳለ የጌታውን እናት ድምፅ በሰማ ጊዜ
ፈጣሪው እርሱን በአካል ሊገኛኘው ሽቶ ወደ እርሱ መምጣቱን አስተዋለ ፡፡ ከደስታው ብዛት የተነሣ ዓለሙ በሆነው ማኅፀን ቦረቀ ዘለለ
፡፡ አስቀድሞ በእናቱና በአባቱ የቅድስና ሕይወት ምክንያት እርሱን በመንፈስ ሲጎበኘው የነበረው እግዚአብሔር ቃል ፣ የፈጠረውን
ሥጋ ለብሶ ከእናቱ ጋር ወደ እርሱ እንደመጣ ሲረዳ ሊተረጎም በማይሞከር ደስታ ተሞላ ፡፡
እናቱ ኤልሳቤጥ የሕያዋን ሁሉ እናት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምን ስትሳለማት
፣ ሕፃኑ ዮሐንስ ደግሞ ሕፃኑን ኢየሱስ
ክርስቶስን ተሳለመው ፡፡ በዚህም ምክንያት በማኅፀኑዋ ውስጥ እንግዳና ያልተለመደ ንውጽውጽታ ተሰምቶአታልና ቅድስት ኤልሳቤጥ ሕሊናዋ በእጅጉ ታወከ ፡፡ “ስድቤን ከእኔ ያራቀልኝ ልጄ ምን ሆነብኝ” በማለትም
ልክ እንደ ሱናማይቷ ሴት ልቡናዋ በከባድ ኃዘን ተመታ ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የቅድስት ኤልሳቤጥን ጭንቀት ተረድቶ በማኅፀኑዋ ውስጥ
ምን እየተፈጸመ እንደሆነ ገለጸላት ፡፡ ስለዚህም በታላቅ ድምፅ ጮኻ
ቅድስት ድንግል ማርያምን “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው ፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ
ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል ? እነሆ የሰላምታሽ ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና፡፡” ብላ ብፅዕት
አለቻት ፤ ልጁዋ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም ለሁለተኛ ጊዜ እርሱዋን ስለጎበኛት በእጅጉ አመሰገነችው፡፡ አንደኛው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን
በፀነሰች ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ይህ እርሱዋን ደስ ሊያሰኝ በእናቱ ወደ እርሱዋ በመጣ ጊዜ ነበር፡፡ጌታችን በአህያይቱ ውርጫ ላይ ሆኖ ወደ
ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕፃናት ከእናታቸው እቅፍ ወርደው “ሆሳዕና በአርያም ፣ ሆሳዕና በአርያም” በማለት ከማመስገናቸው አስቀድሞ
ገና ከእናቱ ማኅፀን ሳለ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ለጌታው፡- “ሆሳዕና በአርያም ፣ እነሆ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ
ነው” እያለ ፍቅሩን እንደምንጣፍ ፣ንጽሕናውን እንደዘንባባ፣ ናፍቆቱን እንደበገና እየደረደረ ፣ ጌታውን ሊተረጎምና ሊገለጽ
በማይችል ደስታና ፈንጠዝያ እየዘመረ ተቀበለው ፡፡
መላእክት በአንድ ቀን
ተፈጥረው የፈጠራቸውን አምላክ በፍቅር በመሆን ወደማመስገን እንደመጡ እንዲሁ ዮሐንስም ገና ከእናቱ ማኀፀን ሳለ
አያቱ ንጉሥ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦቱ ፊት ለአምላኩ ከደስታው ሙላት የተነሣ እየዘለለና እየቦረቀ ፈጣሪውን እንዳመሰገነው
(፪ሳሙ.፮፥፲፮) ፣ እንዲሁ በእጆቹ ያበጃጀው ጌታ እርሱን መስሎ ከማኅፀን ሲመለከተውና ሊገናኘው ወደ እርሱ እንደመጣ ሲረዳ
በደስታ ቦረቀ ዘለለ ፡፡
እነሆ ሕፃናት ምን ያውቃሉ የሚሉ
ይፈሩ ፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ ከእናቱ ማኅፀን ሳለ በተወደዱ እጆቹ አጥንቱን ከሥጋው፤ ሥጋውን ከጅማቱ አስማምቶ የፈጠረውን
አምላኩን አውቆታልና ፡፡
ሕፃናት ፈጣሪያቸው ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ
አይተው ከእናታቸው እቅፍ በመውረድ አመስግነውታል ፡፡ በሦስት ዓመቱ እግዚአብሔርን ያገለግል ዘንድ የተሰጠው ሳሙኤል ከእናቱ
ማኅፀን ሳለ የሚያውቀውን ነገር ግን ተወልዶ ካደገ በኋላ የዘነጋውን ድምፅ በቤተ መቅደስ ሰምቶ “እነሆ ባሪያህ ይሰማልና
ተናገር” ብሎአል(፩ሳሙ.፫፥፲) ፡፡ ያቤጽ እነሆ አልወለድም ብሎ በጣርና በምጥ የተወለደ ልጅ ነበር ፡፡ ከተወለደም
በኋላ ጌታውን “አባክህ መባረክን ባርከኝ አገሬንም አስፋው እጅህም ከእኔ ጋር ትሁን እንዳያሳዝነኝም ከክፋት ጠብቀኝ ብሎ
የእስራኤልን አምላክ ጠራ እግዚአብሔርም የለመነውን ሰጠው ፡፡(”፩ዜና.፬፥፱-፲)
ጌታም በሰው ዘንድ አላዋቂ
ተደርገው የሚታዩትን እርሱን ግን ጠንቅቀው ሰለሚያውቁት ሕፃናት “ሕፃናትን ተዉአቸው ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ
አትከልክሎአቸው መንግሥተ ሰማያት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና”(ማቴ.፲፱፥፲፬ )ብሎ ተናገረ ፡፡ በሌላም ቦታ ሐዋርያትን
“እውነት አላችኋለሁ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም ፡፡”(ማቴ.፲፰፥፲፬ )
አላቸው ፡፡ እንዲህ ሲል ጌታችን ገና ከማኅፀን ሳለ እኔን ጠንቅቆ እንደተረዳኝና በደስታ እንደተቀበለኝ መጥምቁ ዮሐንስ
ካልሆናችሁና ካልተመለሳችሁ ሲላቸው አይደለምን ? ስለዚህስ አይደለምን እንደገና በጥምቀት ተፀንሰንና ከሥላሴ አብራክ ተወልደን
ለእግዝአብሔር ሕፃናት መሆን ያስፈለገን ?
ሕፃናት ፈጣሪያቸውን ጠንቅቀው ያውቁታል ፤
ምንም እንኳ ሥጋቸው ያልዳበረ ፣ አጥንታቸው ያልጠነከረ ቢሆን በነፍሳቸው ንጹሐን ናቸውና ንጹሐን እንደሆኑት መላእክት ጌታቸውን
ይለዩታል ፡፡ ስለዚህም ጌታችን “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” (ማቴ.፭፥፰) ብሎ መሰከረላቸው ፡፡ ገና
ስንፈጠር ያለንን ባሕርይ ጠቢቡ ሰሎሞንም ሲናገር “እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደሠራቸው አነሆ ይህን ብቻ
አገኘሁ”(መክ.፯፥፳፱) ይለናን ፡፡
ከማኅፀን እንደ አባት ሆኖ ፍቅሩን
እየመገበን ፤ እንደ ፈጣሪነቱ ደግሞ የአካል ክፍሎቻችንን በማበጃጀት እኛን ወደ እዚች ምድር በሥጋ ልደት ያመጣን እርሱ ነው
፡፡ ከልደት በኋላ በሥጋ ለወለዱቱ የአጥንታቸው ፍላጭ ፣ የሥጋቸው ክፋይ የሆነውን ሕፃን ልጃቸውን እንደርሱ ሆነው በፍቅር
ያሳድጉት ዘንድ አደራ ይሰጣቸዋል ፡፡
ልቤ ግን አዘነብኝ ፡፡ እኔም ከእናቴ
ማኅፀን ሳለሁ ሆሳዕና በአርያም እንዳሉት ሕፃናት አምላኬን ለይቼ አውቀው ነበር ፡፡ ስለምን አሁን በዛን በጨቅላ እድሜ ሳለሁ
እንደማውቀው አድርጌ እርሱን አልተረዳሁትም ? መልሱ ግልጽ ነው ፡፡ በእናቴና በአባቴ ሕይወት ውስጥ ፈጣሪዬን ስላላየሁት ነው
፡፡ ስለዚህም በጊዜ ርዝመት ውስጥ እርሱን ማወቄ እየደበዘዘ እየደበዘዘ ሄዶ ጭራሹኑ ጠፋ ፡፡ ስለዚህም እንደማላውቀው ሆንኹኝ
፡፡ ኃጢአቴም እንደምርግ ጭቃ ሆኖ ከእርሱ ከሚወደኝ ከሚያፈቅረኝ አምላኬ ለየኝ ፡፡
አቤቱ አምላኬ ሆይ አንተን በእንባ
ሆኜ እለምንሃለው ፡፡ ጌታ ሆይ ፍቅራችን እንደ ድሮአችን እንደ ሕፃንነቴ ዘመን ይሁንልኝ ፡፡ የእናትና የአባቴንም ኃጢአት
ይቅር በል ፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ልክ እንደምትወደው ጢሞቴዎስ ወላጆች ፣ እኔን “ከሕፃንነቴ ጅምሮ አንተን በማመን መዳን
የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዳውቅ አላስተማሩኝምና ፡፡(፩ጢሞ. ፫፥፲፭) ይህን መተላለፋቸውን
ይቅር በል ፡፡ እነርሱም ምንአልባት በወለዱዋቸው ወላጆቻቸው ምክንያት እንዲህ እንደ እኔ ከአንተ ርቀው አድገው ሊሆን ይችላልና
፡፡ አንተ ሁሉን ታውቃለህ ፡፡ እኔንም ይቅር በለኝ በጽድቅ ሕይወት ጸንቶ መቆም ተስኖኛልና ፡፡ ልክ እንደ ሕፃንነቴ ወራት
ንጹሕ እንድሆን እርዳኝ ፤ እዲያ ከሆነ አንተን ለማየት እበቃለሁ ፡፡ ለሁላችንም አቤቱ ጸጋህን አድለን ፡፡ አንተንም ለማወቅ
ቅዱሳት መጻሕፍትን መመርመርን ስጠን ፡፡ ልጆቻችንም አንተን በእኛ ውስጥ በማየት እንዲያድጉ ፣ ጌታ ሆይ ይህ የአንተ ፈቃድ
ነውና ፣ አንተን ማወቅን አብዛልን ፡፡ በሕይወታችንም ተገኝ ፡፡ ቤታችንንም ባርከው ልጆቻችንንም “መባረክን ባርካቸው አገራቸውንም
አስፋ እጅህም ከእነርሱ ጋር ትሁን ክፉውም እንዳያሳዝናቸው ከክፋት ሁሉ ጠብቃቸው” ፍቅርህ ምግባቸው ይሁን ፤ በአባትነትህ
እቅፍ ውስጥ ገብተው ከፍቅርህ ይሙቁ ፣ መታመኛቸውና መጠጊያቸው አንተ ሁናቸው ፡፡ ለዘለዓለሙ ይሁን
ይደረገልን አሜን ፡፡
ወደ ሗላ ወደመጀመርያው ወደ ልጅነት አባታዊውን የእግዚአብሄርን ፍቅር እዳስብ ስለረዳኸኝ እግዚአብሄር ይስጥልኝ የአባቶቻችን አምላክ ጸጋውን ያብዛልህ። "ከማኅፀን እንደ አባት ሆኖ ፍቅሩን እየመገበን ፤ እንደ ፈጣሪነቱ ደግሞ የአካል ክፍሎቻችንን በማበጃጀት እኛን ወደ እዚች ምድር በሥጋ ልደት ያመጣን እርሱ ነው ፡፡ ከልደት በኋላ በሥጋ ለወለዱቱ የአጥንታቸው ፍላጭ ፣ የሥጋቸው ክፋይ የሆነውን ሕፃን ልጃቸውን እንደርሱ ሆነው በፍቅር ያሳድጉት ዘንድ አደራ ይሰጣቸዋል" ፡፡
ReplyDeleteKHY, it is true, They know Him, glory to his name.
ReplyDelete