Wednesday, January 18, 2012

ሞቴን አስቤ ልደቴን

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
03/06/2000 ዓ.ም የተጻፈ
ቀኑ እንዴት ነጎደ! ውስጤን ፍርሃት ፍርሃት አለው መቼም ሰው ሳያውቀው ወደ እግዚአብሔር መጣራቱ አይቀሬ ነው፡፡ አምላኩ ፊት ለፍርድ ሊቆም ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ጊዜ ከትሞ ይኖርባት የነበረችውን ይህችን ግዙፍ ዓለም እንደ ሕልም እንደቅዠት ሆና ትረሳዋለች፡፡ በተቃራኒውም ይህችኛዋም ዓለም እርሱን ፈጥና ለዘለዓለም ትረሳዋለች፤ ስም አጠራርህም ከእነአካቴው ከሰው ሕሊና ይጠፋል፡፡ ወደ አምላካችን በሄድን ጊዜ ለዘለዓለም ከምንለያት ከዚህች ዓለም ሳለን ማወቅና መጠንቀቅ ያለንባቸውን እውቀቶችንና መንፈሳዊ ተግባራት ከፊት ይልቅ ግልጥ ሆነው በሰዋዊ አእምሮአችን ከምናቀው በላይ የመላእክትን እውቀት ገንዘባችን በማድረግ እናውቃቸዋለን፡፡ በፊቱ በቆምን ጊዜ እኛ በእርሱ ዘንድ የታወቅን፣ የጠጉራችንም ቅንጣት የተቆጠረች፣ በእርሱ ዘንድ የተራቆትን እንደሆንን ይበልጥ ግልጥ ይሆንልናል፡፡ በዚህ ምድር ሳለን በእምነት የምንረዳቸውን እውነታዎች በዚያን ጊዜ በግልጥ እናያቸዋለን፡፡

እኛ ገና ሳንፈጠር በፊት በእርሱ ሕሊና ታስበን ነበር፡፡ እርሱ እኛን ፍጠረን ሳንለው፣ ሳናውቅም ከእናታችን ማኅፀን እጅ እግራችንን አጥንት ጅማታችንን እንዲሁም ረቂቅ የሆነችውን ነፍሳችንን በአጠቃላይ መላ ሰብእናችንን ፈጠረ፡፡ ኢዮብ “በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን? ቁርበትና ሥጋ አላለበስኸኝምን? በአጥንትና በጅማትም አላጠነከርኸኝምና?” እንዲል ከአባቶቻችን ዘርን ወስዶ ከእናቶቻችን ሥጋና ደም ከፍሎ እግዚአብሔር እኛን ፈጠረን፡፡(ኢዮ.10፡10-12) ወላጆቻችን በደስታ ጫፍ ደርሰው ሳለ እግዚአብሔር አምላክ ግን በማስተዋል ሥራውን በእነርሱ አካል ውስጥ ይሠራ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አባቴና እናቴ  በእነርሱ እግዚአብሔር ምን እየሠራ እንደሆነ ፈጽመው አያቁም፤ በእነርሱ ቤት ከእርሱ ዘንድ ልክ እንደ አዳም የተደበቁ መስሎአቸው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ግን እኔ በእርሱ ሕሊና ታስቤ በመፈጠር ላይ መሆኔን ፈጽሞ አላውቅም ፡፡ የእኔን እውቀት በዚህ መልክ መግለጡ በራሱ ለማወቅ አንደቀረብኩ የሚያስቆጥርብኝ ስለሚመስልብኝ እንዲህ ማለትን ትቼዋለሁ፡፡ ስለዚህም እኔን ከማወቅ ጨዋታ ውጪ አድርጎ እግዚብአሔር ፈጠረኝ፡፡ እናቴና አባቴ ግን እጅግ እጅግ በመጠኑ፣ እኔ ልሁን አልሁን አይወቁ እንጂ.፣ እግዚአብሔር በስውር እጁ በእነርሱ የሚያከናውነውን አያስተውሉ እንጂ፣ እጅግ በጥቂቱ ማለትም የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል በዚያች ቅጽበት ልጅ ሊፈጠር እንዲችል ያውቁ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ሁሉን ያውቃል የሚለው አገላለጽ ባይገልጠውም እጅግ እጅግ በላቀ ጥበቡ እኔን ፈጠረኝ፡፡ እርሱ አስቀድሞ በሃሳቡ ፀነሰኝ፡፡ እናትና አባቴን በፈንጠዝያ አገናኛቸው፤ እኔንም በእነርሱ ከሃሳብነት ወደ ግዙፈ አካልነት አመጣኝ፡፡ እናቴም አምጣ ወለደችኝ አላወቅሁም፤ጡቶቹዋን አጠባችን አላወቅሁም፤ እስከ ሰባት ዓመቴ እንዲሁ ቀጠልሁ፡፡

አባት ሆይ! ወደ አንተ እጄን እዘረጋለሁ ፍቀድልኝ፤ ያንተን ሕልውና እንድገልጥ ፍቀድልኝ፡፡ ወደ እናቴም የማቀርበው ጥያቄም አለኝ፤ ወላጅ አባቴ ሆይ! ከቅዱሳን መላእክትም ጋር ወይም ከማልመኝልህ ከአጋንንትም ጋር ሆነህ ይሆናል፤ እንደምትሰማኝ ግን እረዳለሁና ወደ አንተ የማቀርበውም ጥያቄ አለኝ፡፡ ለመሆኑ አጥንቴን ያበጀሽው እናቴ ሆይ አንቺ ትሆኝ? አባቴስ አንተ ትሆን? ከፀንሰቴ እስከ ልደቴ ማን ሠራኝ? እናንተ ግዙፋን የሆናችሁት እንዳልሆናችሁ እናንተው እራሳችሁ  ትመሠክሩልኛላችሁ፣ ባልጠይቃችሁም እኔን እናንተ እንዳልፈጠራችሁኝ ታምናላችሁ፡፡ እንግዲያውስ ረቂቅ ሆኖ ረቂቃኑንና ግዙፋኑን የሚፈጥር ፈጣሪ አለ፡፡ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አለ፡፡ ማንም ይህን ሊቃወም ቢሞክር አንድ ከፍጡራን በላይ ረቂቅ የሆነ ሁሉን እንደ ፈቃዱና እንደወደደ የሚያከናውን ኃይል እንዳለ የራሱን ከየት መጣሁ ሲመረምረው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ያምናል፡፡

 የእግዚአብሔር ርቀት(ረቂቅነት) ፈጽሞ የማይመረመርና ከመረዳት ያለፈ ነው፡፡ እርሱ ከእኛ ዘንድ እንዳለ ሳይታወቀን እጅግ ረቂቅና ፍጹም የሆኑ ሥራዎችን በእኛ ሰብእና ውስጥ ያከናውናል፡፡ እስኪ እናስተውለው እርሱ በሁሉ ቦታ ሳይጎድል በእናታችን ማኅፀን ተገኝቶ ሁሉንም የሰውነት ክፍሎቻችንን ይሠራቸዋል፡፡ እንዲህ አድርጎ በእናት ማኅፀን ያለውን ፅንስ የሚያበጃጀው  ፈጣሪ እንዴት ረቂቅ አይደለም ማለት ይቻለናል? አንተ ቁሳዊ አመለካከት ያለህ ሰው ሆይ! ፈጣሪህ እጅግ ረቂቅ በሆነ ጥበቡ ረቂቅ በሆነው ማንነቱ ተገኝቶ ዝግ በሆነው በእናትህ ማኅፀን አንተን እጅግ ግሩምና ድንቅ አድርጎ መፍጠሩን አስተውለህ እንዲህ ድንቅ አድርገህ የፈጠርከኝ ፈጣሪዬ ሆይ እባክህ ተገለጥልኝ በለው፡፡ ወዳጄ ሆይ እባክህ እርሱን ብቻ አምልከው፤ ፈጣሪውን በትክክል ከሚያውቀው ነገር ግን አንተን አንድ እግዚአብሔርን ከማምለክ የሚያርቅህን ሰይጣንን እወቅበት፤ ስለነፍስህ ዕረፍት የራስህን ከየት መጣውነት በጥልቀት ፈትሸው፤ ከልብህም ጋር ተመካከር፤ አስከትለህም የራስህን አፈጣጠር መርመምርና የሚያፈቅርህን ፈጣሪ እወቀው በመቀጠልም ራስህን ለእርሱ ፈቃድ አስገዛ ፡፡    

1 comment:

  1. የእግዚአብሔር ርቀት(ረቂቅነት) ፈጽሞ የማይመረመርና ከመረዳት ያለፈ ነው፡፡ እርሱ ከእኛ ዘንድ እንዳለ ሳይታወቀን እጅግ ረቂቅና ፍጹም የሆኑ ሥራዎችን በእኛ ሰብእና ውስጥ ያከናውናል፡፡ እስኪ እናስተውለው እርሱ በሁሉ ቦታ ሳይጎድል በእናታችን ማኅፀን ተገኝቶ ሁሉንም የሰውነት ክፍሎቻችንን ይሠራቸዋል፡፡ እንዲህ አድርጎ በእናት ማኅፀን ያለውን ፅንስ የሚያበጃጀው ፈጣሪ እንዴት ረቂቅ አይደለም ማለት ይቻለናል? አንተ ቁሳዊ አመለካከት ያለህ ሰው ሆይ! ፈጣሪህ እጅግ ረቂቅ በሆነ ጥበቡ ረቂቅ በሆነው ማንነቱ ተገኝቶ ዝግ በሆነው በእናትህ ማኅፀን ተገኝቶ አንተን እጅግ ግሩምና ድንቅ አድርጎ መፍጠሩን አስተውለህ እንዲህ ድንቅ አድርገህ የፈጠርከኝ ፈጣሪዬ ሆይ እባክህ ተገለጥልኝ በለው፡፡ ወዳጄ ሆይ እባክህ እርሱን ብቻ አምልከው፤ ፈጣሪውን በትክክል ከሚያውቀው ነገር ግን አንተን አንድ እግዚአብሔርን ከማምለክ የሚያርቅህን ሰይጣንን እወቅበት፤ ስለነፍስህ ዕረፍት የራስህን ከየት መጣውነት በጥልቀት ፈትሸው፤ ከልብህም ጋር ተመካከር፤ አስከትለህም የራስህን አፈጣጠር መርመምርና የሚያፈቅርህን ፈጣሪ እወቀው በመቀጠልም ራስህን ለእርሱ ፈቃድ አስገዛ ፡፡

    ReplyDelete