Tuesday, January 24, 2017

ጸሎት በእንተ ትዳር

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
16/05/2009

ጌታ ሆይ ከእናቴ ሆድ ግሩምና ድንቅ አድርገህ ፈጠርኸኝ፡፡ ይህ ተፈጥሮዬም ግሩምና ድንቅ መባሉ በውስጥም በውጪም አንተን እንዲመስል ሆኖ መፈጠሩ ነው፡፡ ወንድና ሴት አድርገህ እንደፈጠርኽን ተናግረህ ካበቃ በኋላ አስቀድመህ የፈጠርኸው  ግን አዳምን ነበር፡፡ በእርሱ ውስጥ ሔዋን እንዳለች ግን አልተረዳንም ፡፡ ጌታ ሆይ ሥራህ ረቂቅ ነው፡፡ አንተ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር በማለት እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በምሳሌው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠረው” ብለህ አስቀድመህ ሙሴን አጻፍኸው እንዲያም ሆኖ ግን “ ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” ብለህ በውስጡ የነበረችውን ሴትን በእርሱ ላይ ከባድ እንቅልፍን በማምጣት ፈጥረህ አሳየኸው፡፡ እርሱም ይህቺ ሴት ከአጥንቴ አጥንት ከሥጋዬም ሥጋ ናት ስለዚህ ሴት ትባል አለ፡፡ አንተም ሰው እናትና አባቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፡፡ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” አልህ፡፡ ስለዚህ በልዩነት ውስጥ ወደ አለ አንድነት አመጣኻቸው፡፡ በፊት ግን እንዲህ አልነበሩም፡፡  ፍጹም በማይለይ አንድነት ከአብራካችን እንደሚገኝ ልጅ አንድ አካል ነበሩ፡፡ ጌታ ሆይ ነገር ግን ለአንተ ይህ በአንድ አካል አንድ ሆኖ መኖር የተመረጠ አልነበረምና በአንተና በቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሁለት አድርገህ ግን ደግሞ አንድ ሆነው እንዲኖረ ከአዳም ሔዋንን አስገኘሃት፡፡ እነዚህ ሁለት ሲሆኑ አንድ አንድ ሲሆኑ ሁለት ነበሩ፡፡ በአንድ ጥንድ ብዙ ጥንዶችን በመፍጠርም ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉዋት ብለህ ሥራህን ፈጸምህ፡፡ በዚህ መሐል ግን አንተን በድለን ፈቃድህን ተላለፈን ስለተገኘን ሁለት ሆኖ አንድ ሆኖ መኖር ለእኛ ፈታኝ ሆነብን፡፡ ስለዚህም  “የባልና የሚስት ሥርዐት እንዲህ ከሆነ አይጠቅምም” ላሉ ሐዋርያት ይህም ሕይወት ለተሰጣቸው ነው ብለህ መለስህላቸው፡፡ እንዲህ ማለትህ ሲሰጥ እንጂ ሳይሰጥ ይህም ጃንደረብነት ከትዳርም ይከፋል ልትለን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ሳይሰጥ ጃንደረባ መሆን አለሌ ወደ መሆን ያደርሳልና፡፡ ጌታ ሆይ እለምንሃለሁ እባክህ የሰጠኸንን ሕይወት አጣፍጥልን ትርጉሙም ገብቶኝ የምኖርበት እንዲሆን ፈቃድህ ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

ጸሎት በእንተ ሰንበት


ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ 
16/05/2009


ኦ የዘለዓለም አምላክ ጌታችን ሆይ!!  የሰንበት ጌታዋ የሆንኽ፣  ሰንበታችንም የሆንኽ እባክህ እኛም የሚቀዋወመንን የሥጋ ፈቃድ ጸጥ አድርገን ልባችንን የቃልህ ጽላት፣ ሰውነታችንን ማደሪያ ቤተ መቅደስህ አድርገን፤ አንተ ግዛታችን ሆነህ እኛም በእውነት ርስትህ ሆነን እኛም ሰንበት እንባል፤ አንተም በሚታይና በተገለጠ ጌታችን ሁነን ያኔ እናርፋለን እረፍታችንም የማይወሰድ ይሆንልናል፡፡ እኛ ፈቃድህን ፈጻሚዎች አንተም በእኛ የምትገለጥ ሁንልን፡፡ ስለምን እሾህና አሜካላ ታብቅልብህ ተብላ በተረገመች ምድራዊ ሥርዓት ውስጥ ወላጅ እንደሌለው ሰው ሆነን ተጥለን እንቅበዘበዛለን፡፡ ጌታ ሆይ እኛን የአንተ ከማድረግህ በፊት በአንተ ከእናታችን መኅፀን ፈጠርኸን፤ ቅዱስ ጳውሎስ እኔ እተክላለሁ አጵሎስ ያጠጣል እግዚአብሔር ግን ያሳድጋል እንዲል ሁሌም ቢሆን አንተ ከሕዋሳታችን ጋር ነበርህ በአንተ ፈቃድ አደገን እንጂ ራሳችንን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን አይደለንም፡፡ ምርጫ ሰጠኸን ምርጫችን በወላጆቻችን እጅ በነበረበት ጊዜ እነርሱ ለአንተ ቀደሱን ልጆችህም አደረጉን፡፡ በራሳችን በቆምን ጊዜ የወላጆቻችን ምርጫ ትክክል እንደሆነ ገብቶን የወላጆቻችንን ምርጫ በምርጫችን አጸደቅነው፤ ለአንተም ሆንን፡፡  ምክንያቱም አንተ በእውነት ሰላማችን፣ እረፍታችን ሕይወታችን ነህና፡፡ ስለዚህ ጌታ ሆይ ከዚህ ዘለዓለማዊ ከሆነ ሰላም፣ እርጋታ፣ ፍቅር፣ ሕይወትና እውነት እባክህ አታውጣን በእርሱ ያመነ ወደ እረፍቱ ገብቶአል ይላልና በተግባር አንተን በመምሰል በአንተ ጥላ ሥር እንመላለሰ ዘንድ እባክህ ፍቀድ፤ ጤናችንን መልስ ልጆቻችንን ባርክ እኛንም በዓለም ከመባከን ታደገን፣ ሥራችንን ባርክ፣ ጌታ ሆይ በሁሉ የሆነብንን ታውቃለህና እርዳን ለዘለዓለም አሜን፡፡

ፊደል ይገድላል መንፈስ ግን ያደናል



ዲ/ሽመልስ መርጊያ
16/05/2009

ጸሐፍት ፈሪሳውያን መጻሕፍትን በማወቅ የዘለዓለም ሕይወት የሚገኝ ይመስላቸው ነበረ፡፡ ነገር ግን ሕይወትን የሚሰጠው ወይም ሰውን ሕያው አድርጎ ሕያው የሆነውን ቃሉን እንዲረዳ የሚረዳው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ጸሐፊው መንፈስ ቅዱስ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ መረዳት የሚቻለው በመንፈስ እንጂ ስላነበቡት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን አውቆአል ማለት  አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከአእምሮ በላይ የሆኑ፤ ነገሮች ሳይፈጸሙ አስቀድሞ የሚያውቅ እርሱ እግዚአብሔር በመንፈሱ ያጻፈው ነውና፡፡ ስለዚህ ሊረዱዋቸው የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ነው፡፡ ስለዚህ መጻሕፍትን ለማስረዳት የተረዳነውን ለማብራራት የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ብቻኛ መንገድ ነው፡፡ ፍጥረታዊ በሆነ አእምሮ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሞከር እንደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ይቀድማል ቅዱሳት መጻሕፍት ይከተላሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ይረዳል፡፡ 
ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ በእርሱ አሳሳቢነት እንደ አበው ቅዱሳን(ከአዳም -ሙሴ) ወይም እንደ ሐዋርያቱ በጽድቅ ጎዳና ሊራመድ ይችላል ነገር ግን መንፈሱ ያላደረበት አይሁዳዊ ከሆነ ግን የግድ መጽሐፍ በሚለው ብቻ ሊራመድ ይገደዳል፡፡ ቢሆንም ግን ያለመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ስለሆነ ማንበቡ ብቻውን ወደ መዳን አያደርሰውም፡፡ ቃል ይገድላል መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል እንዲል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን ቅዱሳት መጻሕፍትን ባነበበ ቁጥር ሁሉ በቀላሉ በመንፈስ ቅዱሰ ገላጭነት ይረዳቸዋል፡:
 በእርግጥ በመጻሕፍት ብቻ ሕይወት የሚገኝ ለሚመስላቸው ወገኖች የመንፈስ ቅዱስን ድጋፍ ስለማያውቁ መንፈስ ቅዱስን ሊሰሙት ሊረዱትንም አይችሉም፡፡ ስለዚህ ክርስቶስን ሊያውቁት ሊረዱት አልቻሉም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎችን የሚያሰናክለው ያለ መንፈሰ ቅዱስ ድጋፍ በአእምሮ ጠባያቸው ብቻ ተደግፈው መጻሕፍትን እንረዳ ባሉ ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ስለ ክርሰቶስ ያላቸው ግንዛቤ እጅግ የተዘበራረቀ ይሆናል፡፡ ወይም በቀጥታ ቃሉን ይዘው ሰማያዊ የሆነውን እንደ አእምሮ ጠባያቸው በመረዳት ምድራዊ ያደርጉታል፡፡  መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ሰው ግን በመንፈስ የተጻፈውን ይረዳል፤ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሁሉን ይተነትናል ሲያብራራም ለሕሊናችን፣ ለተፈጥሮአችን የሚስማማ በመሀኑ ነፍሳችን ትፈካለች ፡፡ ስለዚህ ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ይቀድማል፡፡ ኦርቶዶክስ እንዲህ ናት ይህም ማለት ከጥንት የነበረችው እስካሁንም ያለችው ለዘለዓለም ሕያዊት ሆና የምትኖረዋ ክርስትና ማለቴ ነው፡፡