12/6/2009
ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ወገኖቼ ግርምት የሆነችው በትንሣኤው የምትመሰለው የአርምሞ፣ የእንባ፣ የርኅራኄ፣ የጸሎት፣ የፍቅር፣ ሠላሳ ስልሳና መቶ ፍሬ የምታፈራው የማስተዋል ፍሬ ሁሉ ምንጭ የሆነችውን ጦምን ቀድሶአት፡፡ ጌታችን ከትንሣኤ በኋላ ለሐዋርያት ሲገለጥላቸው ምግብ ለመኖር ምንም ዋጋ እንደሌለው ነገር ግን ሥጋው ከትንሣኤ በፊት ካለው ሥጋ ተቀይሮአል እንዳይሉ ወይም ወደ መንፈስነት ተለውጦአል ብለው እንዳያስቡ ከእነርሱ ጋር ከተጠበሰው ዓሣ ተመገበ፡፡ ይህች ግርምት የሆነችው ጌታችን በተግባር ያስተማረን የትንሣኤ አኗኗራችን ናት፤ ይህቺን የትንሣኤ ሕይወት በምድር ሳለን የምናጣጥማት ደግሞ በጦም ውስጥ ነው፡፡
ይህቺ የገነት አምሳያ የሆነች የጦም ሕይወት ዓለምና አኗኗርዋ የተናቀ እንደሆነ፤ ገነትን በዚህም ዓለም በሥጋ ሕይወት ሳለን መልካምን ሠርተን ብንገኝ የማናጣት፣ መልካምን ባንሠራ የምናጣት እንደሆነች ዘወትር የምታሳስበንና በማስተዋል እንድንመላለስ የምትረዳን ሕይወት ናት፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የትሣኤን ሕይወት በዚህ ምድር ሳለ በሕይወቱ ስላወቃት ከዚህች ሕይወት እንዳይወጣ ሥጋው ለነፍሱ ትገዛ ዘንድ ዘወትር ይጎስማት ነበር፡፡(1ቆሮ.9፡27) ሥጋ የምትጎሰመው ደግሞ በጦም ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለም ሲኖር “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን” አለ፡፡ ለምን እንዲህ አለ? ምክንያቱም በዚህ ዓለም ሳለ የትንሣኤን ሕይወት ጣዕም ቀምሶአልና፡፡ ስለዚህ “በዚህ ውስጥ ሆነን በእውነት እንቃትታለንና ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም፡፡ በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን”(2ቆሮ.5፡1-4) ይላል፡፡ ይህ ለምን ሆነ በዚህ ምድር ያለን ከአምላክ ጋር ያለ አኗኗራችን እንዳቋረጥ ነው፡፡ ከተቋረጠ አደጋ አለውና ፈጽሞ መቆረጥ አለና፡፡ ስለዚህ እርሱም ብቻ አይደለም፥ “ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን”(ሮሜ.8፡23)ምክንያቱም በኃጢአት ጸንተን ብንኖር ልጅነትንም የማጣት ስጋት አለብንና።
ጌታችን ይህን ሕይወት በጦሙ ቀድሶ ሰጠን፡፡ የጦም ሕይወት የዓለምን ፈቃድና ዲያብሎስን ድል የምንነሣበት፤ ቅዱሳን መላእክት እኛን የሚራዱበት በሰማያዊ ሥፍራ ካሉ ቅዱሳን ጋር በመንፈስ አንድ የምንሆንበት ነው፡፡ ጦም የትንሣኤ ሕይወትን በምድር እያለን የምታለማምደን በመንፈሱ ሕያዋን ሆነን መኖር እንደሚቻለን የምታስረግጥልን በመንፈሳዊ ሥፍራ ካለ አምላክ ጋር በትሕትና የምታመላልሰን ድል ከነሡ ቅዱሳን ነፍሳት ጋር የምታወዳጀን፣ የቅዱሳን መላእክት እርዳት የምናገኝበት አንደበታቸው እኛን ለማበርታትና ለማጽናት የምትከፈትበት ከእኛ ተሰውረው የሚገኙ ምሥጢራትን የምንረዳባት በር ናት፡፡
አቤቱ አምላካችን ሆይ በጦም የሥጋ ፈቃዳችንን የዓይን አምሮታችንን ድል ነሰተን በፍጹም ተመስጦና ትጋት ሆነን የትንሣኤን ሕይወት ጣዕም በዚህ ጦም ውስጥ እንድናጣጥምና የኃጥአን ድንኳን ከሆነች ከዚህች ዓለም አኗኗር እንድንለይና ወደ አንተ መምጣትን እንድንናፍቅ እርዳን በደላችንን ይቅር በለን ማስተዋልን ስጠን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡