Sunday, February 19, 2017

የምትጠቅመዋ ኅዘን እናት



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
13/06/2009

ጠቢቡ ሰሎሞን በመክብቡ  " ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና"(መክ.7:3) ብሎ አስቀድሞ ጻፈልን።  ከሃዘን በኋላ ደስታ እንዳለ እንዲሁ ጌታችን  "የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና"(ማቴ.5.4) ብሎ አስተማረን።  መጽናናትንና ደስታን የሚሰጠው እንዴት ያለ ኅዘን ነው? ለሚለው ጥያቄ ቅዱስ ጳውሎስ ሲመልስ "እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል"(2ቆሮ.7:10) ብሎ አብራራልን። የዚህች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነች ኅዘን እናት ደግሞ ጦም ናት።
ጦም ራስን ወደ ማስተዋል የምታደርስ፥ በዚህም ምክንያት የራሳችንን ግንድ የሚያህል ኃጢአት ለማየት የምታበቃን፥ የሚያቃጥል የንስሐ እንባ እንድናነባ ምክንያት የምትሆነን፥ ራስን በአምላክ ፈቃድ ውስጥ ለማሳደር የምታስጨክን፥ ኅጢአትን አጥብቀን እንድንጸየፋትና ከምክንያቶቿ እንደ አቦ ሸማኔ በፍጥነት እንድንሽሽ የምታደርገን ናት። ይህች ጦም አስቀድመን እግዚአብሔርን መፍራት፥ እግዚአብሔርም መፍራት ንስሐን፥ ንስሐ ደግሞ መጽናናትንና የማይቀማ ደስታን፥ መጽናናትና ደስታ ደግሞ እግዚአብሔርን ማፍቀር እግዚአብሔርን ማፍቀር ፍጥረትን ሁሉ ወደ ማፍቀር የምታደርስ ጎዳና ናት።

ጦም ለእውነተኞቹ መምህራን በሁለት በኩል እንደተሳለች ስይፍ ተናጋሪውንም ሰሚውንም የምትቆርጥ ስትሆን ከሆዳቸው ማለትም በሙሉ መረዳት ሆነው በማስተዋልና በፍቅር እንዲሁም በመቆርቆር መንፈስ ሆነው  የቃሉ ውኃ የሚፈልቅባቸው ምንጮች እንዲሆኑ ስትረዳቸው፥ ምዕመናንን ደግሞ ሠላሳም ስልሳም መቶም የሚያፈሩ በንስሐ የለሰለሰ የእግዚአብሔር እርሻ እንዲሆኑ የምታበቃቸው ናት። ይህችም ማስተዋላቸው ናት።
ቅዱስ ኤፍሬም እንደ ጌታ ፈቃድ የሆነች ጦምና ጦም የምትወልዳት ንስሐ፥ ንስሐ የምትወልዳት እግዚአብሔርን መፍራት፥ እግዚአብሔርን መፍራት የምትወልዳት ፍቅር፥  አዳም ያጣትን ራስን መግዛት መልሰን እንድናገኛት ከማብቃትዋ በተጨማሪ ወደ  ወጣንባት ገነት መልሳ የምታገባን ጎዳና ናት ይላታል። በዚህች ጎዳና ራሳችንን ተቀብተን በስውር በሚያየን አባታችን ፊት እናዋርዳለን፥ እርሱም ነፍስን የደስታ ዘይት ይቀባታል። ይህች ዘይትም ለሥጋችን ትተርፍና ፊታችንን በማይወሰድ ደስታ ታበራዋለች። ይህች ደስታ ቅዱስ ጳውሎስ  "ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ"(ፊል.4:4) ያላት ደስታ ስትሆን ከሃዝን በኋላ በንስሐ ውስጥ ካለች ልቅሶ የምትፈልቅ ከጌታ የምናገኛት ደስታ ናት። ይህች ደስታ ደስ ከተሰኙ ከአእላፍት ቅዱሳን መላእክትና ከቅዱሳን ነፍሳት ጋር አንድ ቤተሰብ በመሆናችን የምናገኛት ደስታ ናት። ለፍጥረታዊ ሰው የምትታወቅ አይደለችም። በቁስ የምንለውጣት፥ በገንዘብ የምንገዛት ፈጽማ አይደለችም። እርሱ ሰላማችን የሆነ እግዚአብሔር አብ፥ ወልድ ፥ መንፈስ ቅዱስ ሰውነታችንን መኖሪያው በማድረግ የምናገኛት ደስታ ናት እንጂ ።
 አቤቱ አምላካችን ሆይ ይህችን የጦም ሕይወት ሰጥተኸን እንድናጣጥማት ራሳችንን ተመልክተን በንስሐ በአንተ ፊት እንድናዋርድና ከአንተ ጉባኤ እንድንደመር የበቃን አድርገን በእውነት ለዘለዓለም አሜን።

No comments:

Post a Comment