በዲ/ሽመልስ መርጊያ
25/06/2009
ቅዱስ ጳውሎስ፥- "የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ"(1ቆሮ.14:32)ሲል መቼም ስለመንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ለአጋንንትም አይደለም። እርግጥ ነው ሐዋርያት በአጋንንት ላይ ስልጣን አላቸው። ቢሆንም ግን ይህ ቃል ስለ አጋንንት የሚናገር አይደለም ስለቅዱሳኑ መላእክት እንጂ። እና ቅዱሳን መላእክት ለነቢያት ይገዛሉ እንዴ? የሚል ጥያቄን ሊያስነሣም ይችላል። ፡በፍጹም እንዲያ ቢሆን ነቢያት የእግዚአብሔር መልአክ ሲገለጥላቸው እግዚአብሔር እንደተገለጠላቸው ቆጥረው ባልሰገዱላቸውና ባልታዘዙላቸው ነበር። እንደ አብነት ለኢያሱ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት ነበር። እንዲያም ቢሆን ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ አልተገዛም። እንዲሁ ለነቢዩ ዳንኤል ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጦለታል። ሲገለጥለት ግን እውቀትንና ማስተዋልን ይሰጠው ዘንድ ነበር። ዳንኤልም ለመልአኩ መስገዱ ተጽፎልናል። ጌታችንም በእርሱ ፊት ስለሚቆሙት ሰለጠባቂ መላእክት ስንል ታናናሾችን እንዳንንቅ አስጠንቅቆናል። ለካህኑ ዘካርያስ፥ ለዮሴፍ፥ ለእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦአል። አንድም ቦታ ግን ስለመገዛቱ አልተጻፈም።
ይኸው ሐዋርያ በእስር ወደ ኢጣሊያ በመርከብ ሲሄድ በደረሰባቸው የማዕበል አደጋ ምክንያት የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ አጽናንቶታል። በሌላ ሥፍራም ቅዱሳን መላእክት ለነቢያትና ለሐዋርያት መገዛታቸውን በተመለከተ ተጽፎ አናገኝም። ስለዚህ "ይገዛሉ" ሲል ማገልገላቸውን ለመናገር እንደሆነ እንረዳለን። ይህንን ቃል ይኸው ሐዋርያ " ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል" በማለት ለጌታም ተጠቅሞበት እናገኘዋለን። እንዲህ ሲል ሞት እርሱን ገዝቶታል ማለት ሳይሆን በሰዎች ላይ የፈረደውን የሞት ፍርድ ራሱ ተቀብሎ ከሞት አገዛዝ ነጻ በማውጣትና ለራሱ በማስገዛት ለአብም አስገዝቶታል በዚህም የሞትን ስልጣን ሽሮታል ሲል እንዲህ እንዳለ እንጂ ዲያብሎስ ገዝቶታል ማለት አይደለም።
ጌታችን የተገዢን የሰውን ባሕርይ ገንዘቡ በማድረግ ለአባቱ ታዝዞአል ይህ ግን የፈቃድ ነው። ይህን በምን እናረጋግጣለን ቢሉ ጌታችን "ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ"(ዮሐ.15:17-18) ባለው ቃሉ ማረጋገጥ ይቻላል። በእርሱ ላይ ሊሰለጥን የሚችል ማንም እንደሌለ መሞቱና መነሣቱ በፈቃዱ እንደሆነ ግልጽ አድርጎ አብራርቶልናል። እና "ይገዛሉ" የሚለው ቃል የፈቃድ አገልግሎታቸውን እንደሆነ ልብ እንላለን። ዋናው የተነሣሁበት ጭብጥ ግን ይህን መተንተን አልነበረም።
ቅዱስ ጳውሎስ ግን የመናፍስት አምላክ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ዳዊት በዚሁ መንፈስ የተናገረውን እንደ ዳዊት ተረድቶ እንዲህ አለን፥-
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ እንዲሁ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ ማልሁ” ብሎ ጻፈልን።
እኔን የፈተኑበት፣ ያስመረሩበት፣ ሥራዬንም ያዩበት፣ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ ተቆጣሁ፤ ያለው ማን ነው? መልሱ ፡- መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ዳዊት ምን አለው? “እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና”(መዝ.95፡7) አለን፡፡ እናም መንፈስ ቅዱስን እንደ አንድ ኃይል የሚያስቡ ይፈሩ እነሆ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ስለመሆኑ ማስረጃ፡፡ ስለምን ግን ቅዱስ ጳውሎስ ይህን የዳዊትን ቃል ማንሳት ፈለገ? እስራኤላውያን ስለወረሱዋት “ከንዓን” ነውን? ለጊዜው ስለእርሷ ቢሆንም ፍጻሜው ስለእርሷ አይደለም፡፡
እናም ቅዱስ ጳውሎስ ሌላ ሊያመጣ አንደ መንደርደሪያ እንዲሆነው “ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም፡- እንዲህ፡- ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ እኛስ ወደ ዕረፍቱ ገብተናል፡፡(ዕብ.4፡3) ይላል፡፡ እኛስ እንደ እስራኤላውያን “ምድረ ከንዓንን” አልወረስንም፡፡ ታዲያ ቅዱስ ጳውሎስ በእምነት ወርሳችኋታል ያለን ማንን ነው? ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ “ዕረፍቴ” ያላት እስራኤላውያን ባለማመናቸው ያልገቡባት ይህቺ ምድራዊቱ ከንዓን እንዳልሆነች እየገለጠልን ነው። ምክንያቱም ያቺን ምድራዊቱን ከንዓን እኛ አልወረስናትምና፡፡ ግን ቅዱስ ጳውሎስ በእምነት እንገባባታለን ይለናል፡፡ መልሱን ለመስጠት ቅዱስ ጳውሎስ ይቀጥላል፡- እንዲህ ይላል፡- “ስለሰባተኛው ቀን በአንድ ሥፍራ፡- እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና በዚህ ስፍራም ደግሞ፡- ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” አለ፡፡
እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነው? በዚህም እግዚአብሔር የተባለው መንፈስ ቅዱስ ስለመሆርያው ጻፈልን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ተነሣንበት ነጥብ ስንመጣ ከሥራው ሁሉ ያረፈባትን ይህቺን “ቀዳሚት”ንም “ዕረፍቴ” እንደሚላትም ቅዱስ ጳውሎስ ገለጠልን ቢሆንም ግን እርሷም እንደምድረ ከንዓን ጥላ እንጂ አማናዊቱ አልነበረችምና ትንታኔውን በመጠይቅ ይቀጥላል ? “እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለቀሩ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ጠንቅ ስላልገቡ፡- ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከተኛ አታድርጉ” በፊት እንደተባለ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ ዳዊት፡- ዳዊት ዛሬ ብሎ እንደ አንድ ቀን እንደገና ይቀጥራል፡፡ ኢያሱ አስርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር” በማለት “እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል፡፡ ይልና አስከትሎ “ወደ ዕረፍቱ የገባ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና” ይለናል፡፡ በዚህም ኃይለ ቃሉ አሁንም መግባት እንዲቻል ወደፊትም እንደሚገባባት መግለጹን ይህም በእምነት እንደሆነ ገልጾልናል፡፡ ይህቺም ሰማያዊ ሥፍራ ናት፡፡ በቀን ቀመር ውስጥ የማትቆጠር በቦታ የማትወሰን ነገር ግን በእምነትና በመታዘዝ የምንኖርባት ናት፡፡
ስለዚህም ይህ ቅዱስ “በሥጋ ስናድር ከጌታ ተለይተን በስደት እንዳለን የምናውቅ ከሆንን ታመነናል፤ ይልቁኑም ከሥጋ ተለይተን በስደት መኖር ከጌታም ዘንድ ማደር ደስ ይለናል”(2ቆሮ.5፡6-8) እንዲል በዚህ ምድር ሳለንም ከጌታ ጋር መሆን ዕረፍት ነው፡፡ ይህችም ክርስትና ናት፡፡ ስለዚህም ጌታችን “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ”(ማቴ.11፡28) ይለናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን” ይለናል፡፡ እናም ወዳጆቼ በዚህ ምድር ክርስትና በምትጠይቀው እምነት ውስጥ ካለን በሰማያዊ ሥፍራ ነን፡፡ በዚያም “ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርሷ ዘንድ አላየሁም ለከተማይቱም የእግአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልግም”(ራእይ.21፡22-24) በዚህችም ሥፍራ ከቅዱሳን ጋር አንድ ጉባኤ አንድ ኅብረት ይኖረናል፡፡ ይህች ሥፍራ ክርስትና ናት፤ ይህቺም ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ይህቺ ቀን ስምነተኛው ቀን ናት ቅዱስ ጰውሎስ ቀንና የዕረፍት ሥፍራ ያላትን በዕብ.3 እና 4 ላይ ጻፈልን።
አቤቱ ከዚህች የዕረፍት ሥፍራ አታውጣን ።
No comments:
Post a Comment