Friday, February 17, 2012

“በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም”(ዮሐ.9፡17)


በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
10/06/2004

ፍቅር የሆነው አምላካችን ስለእርሱ የመከራ ወቅትና ትንሣኤ በአስተማረን ወቅት “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሚዜዎች ሊያዝኑ ይገባቸዋልን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፡፡ በዚያን ጊዜ ሚዜዎች ይጦማሉ” ብሎ ነበር፡፡ ጌታችን የእርሱን ልደትና የስብከት ዘመንን የሙሽርነት ወቅት ይላቸዋል፡፡ በእውነትም ልደትህ በአንተ ያመኑትን ለአንተ ታደርጋቸው ዘንድ በእነርሱ አርአያ ለተገለጥከውና የሰዎች ልጆች መዳን ደስ ለሚያሰኝህ ላንተ ለጌታችን የደስታ ቀን ናት፡፡ ጌታ ሆይ ላንተ ከነፍሱዋ ትገዛልህ ለነበረችውም ለቅድስት ድንግል ማርያምም የአንተ ከፅንሰት እስከ ልደት ያሉት ቀናት የደስታ ቀናቶቹዋ ናቸው፡፡ የስብከትም ዘመን ለአንተ ራሳቸውን ለማጨት የፈቀዱ ሐዋርያት ወደ አንተ የቀረቡበት ወቅት ነውና በእርግጥም የደሰታ ቀን ነው፡፡







 ለሙሽራው ሙሽሪትን ያጩ የነበሩ ሚዜዎቹ ነቢያት ነበሩ፡፡ ስለ እርሱ ጭንቅ መከራ የተቀበሉት እነዚህ ነቢያት በመጥምቁ ዮሐንስ ዐይን ጌታቸውን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ ማርያም ተገልጦ ተመልክተውታልና ነፍሳቸው በደስታ ፈንጭታለች፡፡ አንዲት ሴት ልጁዋን በምጥና በጣር ከወለደችው በኋላ ስቃይዋንና ሕመሟን ሁሉ ፈጽማ እንድትረሳና በልጅዋ ልደት እንድትጽናና ሚዜዎች የተባሉት ነቢያት ከእርሱ ባገኙት ቃል ለእርሱ የሆነችውን ሙሽሪትን ሲያስጌጡዋት ሲያስውቧት ከቆዩ በኋላ እነሆ ከሙሽራው ጋር ሲያገናኝዋት እንዴት በደስታ አይቦርቁ!!
 ነቢያት ሙሽሪት ሐዋርያትን ለእውነተኛው እረኛ ክርስቶስ ካጩዋት በኋላ በነቢዩ ዮሐንስ አንደበት “ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው ቆሞ የሚሰማው ግን በሙሽራው ድምፅ እጅግ ደስ ይለዋል፡፡ እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ፡፡ እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል”በማለት ተልኮአቸውን ፈጸሙ፡፡(ዮሐ.3፡29-30) ቢሆንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ወደዚህ ዓለም መምጣት ዓለምን በእርሱ ለመጠቅለል ነውና ሐዋርያትን መልሶ የባዘኑትንና ከእርሱ መንጋ የሆነቱትን በጎች ወደ እርሱ ያቀርቡአቸው ዘንድ ሜዜዎቹ አድርጎ ሾማቸው፡፡ ስለዚህም የዮሐንስ ደቀመዛሙርት “ስለምን ደቀመዛሙርትህ እንደ እኛና እንደ ፈሪሳውያን አይጦሙም” ብለው በጠየቁት ጊዜ“ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ሙሸራው የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል በዚያን ጊዜም ይጦማሉ፡፡” በሚለው ቃሉ ጌታችን ሐዋርያትን ሚዜዎች አድርጎ መሾሙን ማስተዋል እንችላለን፡፡  ከመንጎቹ የሆኑትን ነገር ግን የባዘኑትን በጎች ወደ በረቱ ማምጣት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚቀጥል ነውና ሙሽሮች ሆነው የታጩት ተመልሰው የሐዋርያትን ሥልጣን በመቀበል ሌሎችን ለክርስቶስ ያጫሉ፡፡ "ያዝናሉ" ሲባል ስለእነርሱ የተቀበለውን ሕማም ሲያዩ ያዝናሉ ሲለን እንጂ ከእነርሱ ስለሚለያቸው ያዝናሉ እያለን አይደለም፡፡ እንዲያማ ቢሆን “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ" ባላላቸው ነበር፡፡(ማቴ.28፡19-20)
ሙሽራው ክርስቶስም እርሱዋን ያጨበትን የጋብቻ ጥሎሽ ሳይሰጥ ለእርሱ የታጨችውን ሙሽራ አይወስድም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሙሽራው ሰማያዊ ንጉሥ ነውና ሙሽሪት ሰማያዊት ሆና እንድትገኝ እርሱዋን ማሳመን ጊዜ ይጠይቃል፡፡ እርሱዋን የእርሱ ለማድረግ የተጠየቀው የማጫው ጥሎሽ ክቡር ደሙ ነበር፡፡ አሁን ግን የታጨችውም ፣ ሚዜዎቹም በአንድነት በሙሽራ ልደትና ስብከት አብረው ደስ ይሰኛሉ፡፡ ነገር ግን ሙሽራው እጮኛይቱን ለራሱ ሊያደርጋት በወሰነበት ሰዓት እጮኛይቱ ስለፍቅረኛዋ ስቃይና መከራ እንዲሁ ሞት በተዘጋ ቤት ሆና በእጅጉ ታዝናለች፡፡ ይህ ከመፈጸሙ በፊት ግን ሙሽሪት ደስ ይላታል እንጂ አታዝንም፡፡እንዲሁም ሙሽራይቱ እርሱ ለእርሱዋ ያለውን ፍቅርና ፈቃድ ምን እንደሆነ ሳትረዳና ሳታውቅ እርሱዋም በፍቅሩ ሳትወድቅ ይህ ስለእርሱዋ የሚከፍለው የደም ዋጋ አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም “በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጥጅ የሚያኖር የለምና፡፡ ቢያደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፡፡ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል ሁለቱም ይጠባበቃሉ፡፡”(ማቴ.9፡17) እንዲህ ማለት በአሮጌው አዳማዊ ተፈጥሮ መንፈስ ቅዱስን ማኖር ወይም አዲስ አቁማዳ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ለታደሰው ሰውነት አሮጌውን የብሉይ ሥርዐት መፈጸም አይቻልም፡፡ እንዲህ ያደረግን እንደሆነ አንደኛው አንደኛውን ያጠፋዋል፡፡ በሌላ አባባል በአሮጌው አዳማዊ ተፈጥሮ የመንፈስን አሳብ መፈጸም አይቻለንም፡፡ ወይም በብሉይ ኪዳን ኃጢአትን ለማስተስረይ የሚቀርበው መሥዋዕት በመንፈስ ቅዱስ ለታደሰ ሰውነት አያገለግልም ሲለን ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ግን እርስ በእርሳቸው አይጠባበቁም፡፡ ነገር ግን አዲሱ የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ከሆነ እርስ በእርሳቸው ይጠባበቃሉና ሊጠፋፉ አይችሉም፡፡ ይቀጥላል….  

No comments:

Post a Comment