Saturday, November 3, 2012

ድንቅ ግን እውነት



ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/02/2005
ክብር ይግባውና ስለ ድንቅ እምነቱ እግዚአብሔር አብርሃምን ለአሕዛብ አባት አደረግሁ አለው፡፡(ዘፍ.17፡7-8፤ሮሜ.4፡12) ድንቅ ስለሆነውም በእምነት መታዘዟ እግዚአብሔር ሣራን የአሕዛብ እናት አደረጋት፡፡ ስለእርሱዋ እግዚአብሔር “እባርካታለሁ ደግሞም ከእርሱዋ ልጅ እሰጥሃለሁ እባርካታለሁ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፡፡”(ዘፍ.17፡16)ብሎ ተናገረላት፡፡
ንጉሥ ዳዊትም እንዲሁ ከልጅነቱ ጀምሮ ልቡን የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ፣ አንደበቱን የመንፈሱ አገልጋይ በማድረጉ እንደ ልቤ ተባለ፡፡ ከእርሱም ዘር ክርስቶስ እንዲወለድ “ዘርህን ለዘለዓለም አዘጋጃለሁ፤ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ፡፡”(መዝ.88፡4) እንዲሁም “ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ መንግሥቱንም አጸናለሁ፡፡ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል የመንግሥቱም ዙፋን ለዘለዓለም አጸናለሁ” አለው፡፡ ይህን ቅዱስ ዳዊት በመንፈስ አስተውሎ “ጌታዬ ሆይ! እግዚአብሔር ሆይ ! እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው? ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፤ ስለባሪያህም ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፤ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! ይህ የሰው ሕግ ነው፡፡(2ሳሙ.7፡12-4፤ 18-19) ብሎ ጌታውን አመሰገነ፡፡ በዚህ ቦታ ይህ “የሰው ሕግ ነው” ያለው “ክርስቶስን መምሰል” ነው፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ለማስረዳት "የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና” ብሎ ጽፎልናል፡፡(ሮሜ.10፡4)