Saturday, March 4, 2017

"ወደ ዕረፍቱ የገባ ከሥራ አርፎአል"



በዲ/ሽመልስ መርጊያ
25/06/2009

ቅዱስ ጳውሎስ፥- "የነቢያትም መናፍስት ለነቢያት ይገዛሉ"(1ቆሮ.14:32)ሲል መቼም ስለመንፈስ ቅዱስ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ለአጋንንትም አይደለም። እርግጥ ነው ሐዋርያት በአጋንንት ላይ ስልጣን አላቸው። ቢሆንም ግን ይህ ቃል ስለ አጋንንት የሚናገር አይደለም ስለቅዱሳኑ መላእክት እንጂ።  እና ቅዱሳን መላእክት ለነቢያት ይገዛሉ እንዴ?  የሚል ጥያቄን ሊያስነሣም ይችላል። ፡በፍጹም እንዲያ ቢሆን ነቢያት የእግዚአብሔር መልአክ ሲገለጥላቸው እግዚአብሔር እንደተገለጠላቸው ቆጥረው ባልሰገዱላቸውና ባልታዘዙላቸው ነበር። እንደ አብነት ለኢያሱ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት ነበር። እንዲያም ቢሆን ቅዱሱ መልአክ ለኢያሱ አልተገዛም። እንዲሁ ለነቢዩ ዳንኤል ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጦለታል። ሲገለጥለት ግን እውቀትንና ማስተዋልን ይሰጠው ዘንድ ነበር። ዳንኤልም ለመልአኩ መስገዱ ተጽፎልናል። ጌታችንም በእርሱ ፊት ስለሚቆሙት ሰለጠባቂ መላእክት ስንል ታናናሾችን እንዳንንቅ አስጠንቅቆናል። ለካህኑ ዘካርያስ፥ ለዮሴፍ፥ ለእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦአል። አንድም ቦታ ግን ስለመገዛቱ አልተጻፈም።