Friday, June 1, 2012

"አባታችን ሆይ"በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (ክፍል ሦስት)


‹‹መንግሥትህ ትምጣ››
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/09/2009
ይህም በጎ ሕሊና ያለው ሰው ጸሎት ነው፡፡ እንዲህ ዐይነት ሰው በዐይን በሚታዩ ምድራዊ ነገሮች የሚማረክ ሰው አይደለም፡፡ ወይም ይህን የሚታየውን ዓለም እንደ ትልቅ ቁምነገር የሚቆጥረው ሰው አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደ አባታችን በጸሎት ይፋጠናል፡፡ከእግዚአብሔር ዘንድ የምትሰጠውንም መንግሥት ይናፍቃል፡፡ ይህ ፈቃድ ከመልካምና ከምድራዊ አመለካከት የተለየ ሕሊና ካለው ሰው ዘንድ የሚገኝ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሕይወት ዘወትር ይናፍቀው ነበር፡፡ ስለዚህም‹‹… የመንፈሱ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን››(ሮሜ.፰፡፳፫ )ብሏል፡፡ እንዲህ ዐይነት ናፍቆት ያለው ሰው በዚህ ምድር ባገኛቸው መልካም ነገሮች ራሱን አያስታብይም ወይንም በጽኑ መከራ ውስጥ ቢሆንም ከመከራው ጽናት የተነሣ አይመረርም ፡፡ ነገር ግን ወደ ሰማይ ወደ እረፍቱ ቦታ እንደገባ ሰው ምስቅልቅል ከሆነው ከዚህ ዓለም ሕይወት ነፃ የወጣ ሰውን ይመስላል፡፡