Friday, June 1, 2012

"አባታችን ሆይ"በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ (ክፍል ሦስት)


‹‹መንግሥትህ ትምጣ››
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
25/09/2009
ይህም በጎ ሕሊና ያለው ሰው ጸሎት ነው፡፡ እንዲህ ዐይነት ሰው በዐይን በሚታዩ ምድራዊ ነገሮች የሚማረክ ሰው አይደለም፡፡ ወይም ይህን የሚታየውን ዓለም እንደ ትልቅ ቁምነገር የሚቆጥረው ሰው አይደለም፡፡ ነገር ግን ወደ አባታችን በጸሎት ይፋጠናል፡፡ከእግዚአብሔር ዘንድ የምትሰጠውንም መንግሥት ይናፍቃል፡፡ ይህ ፈቃድ ከመልካምና ከምድራዊ አመለካከት የተለየ ሕሊና ካለው ሰው ዘንድ የሚገኝ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሕይወት ዘወትር ይናፍቀው ነበር፡፡ ስለዚህም‹‹… የመንፈሱ በኩራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን››(ሮሜ.፰፡፳፫ )ብሏል፡፡ እንዲህ ዐይነት ናፍቆት ያለው ሰው በዚህ ምድር ባገኛቸው መልካም ነገሮች ራሱን አያስታብይም ወይንም በጽኑ መከራ ውስጥ ቢሆንም ከመከራው ጽናት የተነሣ አይመረርም ፡፡ ነገር ግን ወደ ሰማይ ወደ እረፍቱ ቦታ እንደገባ ሰው ምስቅልቅል ከሆነው ከዚህ ዓለም ሕይወት ነፃ የወጣ ሰውን ይመስላል፡፡






“ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን”
እነሆ ታላቅ የሆነው መንፈሳዊ ልምምድ፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል ከእርሱ ከአባታችን ጋር ለመኖር መናፈቅ እንዳለብን መከረን፡፡ ያም እስከሚሆን ድረስ በዚህ ምድር ሳለን የሰማያዊያን ቅዱሳን መላእክትን አኗኗር ሕይወታችን አድርገን መመላለስ እንዳለብን በዚህ ኃይለ ቃል አስተማረን፡፡ እንዲህ አለን፡- ከአባታችሁ ጋር በሰማያዊ ክብር መኖርንና ሰማያዊ በረከቶችን  መናፈቅ ውደዱ፡፡ ስለዚህ ምድርን ሰማይ በማድረግ ሰማያዊ ኑሮንና ሰማያዊ ንግግር ተነጋገሩባት፡፡ አንዲህም ሲለን  “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ አዘዘን፡፡ እነዚህ ሁለቱ ጉዳዮች የጸሎታችን ዋና ክፍሎች ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ እኛ በዚህ ምድር በመኖራችን ምክንያት ሰማያውያን መላእክትን በቅድስና የማንመስለበት አንዳች ምክንያት የለም ፡፡ እኛ ሰዎች በሰማያዊ ሥፍራ የሚሠሩ የቅድስና ሥራዎችን  በዚህ ዓለም ማከናወን አይሳነንም፡፡ መላእክት የቅድስና ሥራን ያለአንዳች እንቅፋት ያከናውናሉ፡፡ በእነርሱ ዘንድ ልክ በምድር እንደሚታየው ግማሹ የሚታዘዝ ግማሹ የማይታዘዘብበት ሕይወት የለም፡፡ ሁሉም በአንድነት ለጌታቸው ፈቃድ ይታዘዛሉ፡፡ስለዚህም ኃያላን ተባሉ ፡፡ እንዲሁም እኛ ሰዎች ፈቃድህን ያለልዩነት ፈጻሚዎች እንሆን ዘንድ አብቃን ስንል እንዲህ ብለን  መጸለይ እንዳለብን አሳሰበን፡፡
በዚህ ቦታ ትሕትናንም ጭምር እንዳስተማረን እናስተውላለን፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል የእርሱ ፈቃድ የእኛ ብቻ መዳን ሳይሆን  በዓለም ዙሪያ ላሉ የሰው ዘሮች በሙሉ እንደሆነ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዳችን ለዚህች ዓለም ሰላምና ደኅንነት ማሰብ እንዳለብን የሚያስጠነቅቅ ኃይለ ቃልም ነው፡፡ “ፈቃድ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በእኔ” ይሁን ብለን እንድንጸልይ አላዘዘንም ነገር ግን “… እንዲሁም በምድር ትሁን” እንድንል አዘዘን፡፡ ይህም የእርሱ ፈቃድ በዓለም ዙሪያ ባሉ የሰው ዘሮች ይተገበር ዘንድ መጸለይ እንዳለብን የሚያሳስብን ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ እውነት ታብባለች ስህተት ትጠፋለች፣ ኃጢአት ሁሉ ይወገዳል ጽድቅ ትተከላለች፡፡ ይህ በተፈጸመ ጊዜ በምድርና በሰማይ መካከል የነበረው ልዩነት ይጠፋል፡፡ ጌታችን እንዲህ ይለናል “ምንም እንኳ ምድር የምታልፍ ብትሆንም በሰማያውያንና በምድራውያን መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም በአፈጣጠራቸው የተለያዩ ቢሆኑም ምድር ለእናንተ ሌላኛዋ የመላእክት መኖሪያ ትሆናለች፡፡”
 የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ
"የዕለት እንጀራችንን" ሲለን ምን ማለቱ ነው፡፡ አሁን ለምንላት ለዛሬዋ ቀን ሲለን ነው፡፡ ለምን ይህ ማለት አስፈለገው? ምክንያቱም አስቀድሞ “ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ስላለን ነው፡፡ ሰው ረቂቅ የሆነች ነፍስ ያለችው ቢሆንም ምድራዊ ሥጋንም ገንዘቡ ስላደረገ ለሥጋውም መሠረታዊ መብቶች(ፍላጎቶች) የሆኑት የሚያስፈልጉት ፍጥረት ነው፡፡ በእነዚህ መሠረታዊ መብቶች መጓደል ምክንያት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ልክ እንደ መላእክት በትጋት መፈጸም ይሳነዋል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ መሠረታዊ መብቶች ምክንያት የእግዚአብሔር ፈቃድን መፈጸምን  እንዳናቋርጥ “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ” ብለን እንድንጸልይ አዘዘን፡፡
ይህ ማለት ጠቢቡ ሰሎሞን “ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ነገር ግን የሚያስፍልገኝን እንጀራ ስጠኝ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም፤ እግዚአብሔርስ ማን ነው እንዳልል፣ ደሀም አንዳልሆን አንዳልሰርቅም፤ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል” (ምሳ.፴፥፰-፱)ብሎ የገለጸው ለኑሮ አስፈላጊ የሆነ ጉዳዮችን ሁሉ ነው፡፡ ከንቱነት ሲል ባለጠግነትን ነው ሐሰተኛነትን ሲል ደግሞ ደህነትን ነው፡፡ ከንቱነትና ሐሰተኝነት የባለጠግነትና ከድህነት ውጤቶች ናቸው፡፡ ይህንን አስከትሎ በጻፈው ላይ ለማብራራት ሞክሮአል፡፡
ስለዚህም ጌታችን መካከለኛ ሕይወትን ስጠን ብለን መጸለይ እንዳለብን ሲያስተምረን እንዲህ አለን፡፡ቅዱስ ጳውሎስም ክርስቲያን ደሃም ባለጠጋም መሆንን መሻት እንደሌለበት ሲያስተምር፡፡ “ኑሮዪ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው ወደ ዓለም ምንም እንኳ  ይዘን አልመጣንምና አንዳችም ልንወስድ አይቻለንም ምግብና ልብስ ከኖረን  ግን እርሱ ይበቃናል፡፡ ዳሩ ግን ባለጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ፡፡”(፩ጢሞ.  ፮፥፮-፱) እንዲሁም “የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም”(ኤፌ. ፬፥፳፰) በተጨማሪም “ ከማንም ብር ወይም ወርቅ ወይም ልብስ አልተመኘሁም አነዚህ አጆቹ በሚያስፈልገኝ ነገር ለእኔና ከእኔ ጋር ላሉት እንዳለገለገሉ እናንተ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲሁ እየደከማችሁ ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፅዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ”ብሎ መላልሶ አስተምሮአል፡፡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ ብላችሁ ጸልዩ ሲለን “ለኑሮ በቂ የሆኑ መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን ስጠን ብላቹ ጸልዩ ማለቱ ነው፡፡
 ክርስቲያን መኖር ያለበት መካከለኛ አኗኗር ነው( moderate life ) ፡፡ እንዲህ ከሆነ ልክ እንደ መላእክት ያለማቋረጥ እርሱን ማመስገንና ፈቃዱን መፈጸም ይቻለዋል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ መብቶች(ፍላጎቶች) ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም የሆነ ኅብረት እንዲኖረን ይረዱናል፡፡  thus “the perfection of conduct” saith He, “I require as great, not however freedom of from passions no, for the tyranny of nature permites it not for it requeres necessary food.” ጌታችን “ፍጹም ለሆነ ለሰመረ ግንኙነት ወሳኝ ናቸው ብሎ ያወሳቸው እነዚህ መሠረታዊ ፍላጎቶች ለእኔ በእጅጉ ያስፍልጉኛል፡፡ ነገር ግን ለሥጋዬ አርነትን ልሰጣት አይደለም፡፡ በጭራሽ! እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች እንድንጠይቅ ያስፈለጉበት ምክንያት ሥጋን በኃጢአት ባርነት ውስጥ በሚጥላት ፈቃድ ውስጥ ለመጣል አይደለም ፡፡
ስለዚህም ወንድሜ ሆይ አስተውል ለሥጋ በሚያስፈልጉ በእነዚህ መሠረታዊ ፍላጎች ላይ መንፈሳዊ ዳርቻ አላቸው፡፡ ስለ ሀብት፣ ስለ ምቾት ኑሮ፣ ወይም ውድ ስለሆኑ የቅንጦት ልብሶች፣ ወይም እነዚህን የመሰሉ ነገሮችን እንጠይቅ ዘንድ አልታዘዝንም፡፡ ነገር ግን የዕለት እንጀራችንን አለን “ ስለ ነገ አታስቡ ሲለን ነው፡፡ ስለነገም አታስቡ ሲለን በሕይወት መኖራችን በእነዚህ ምክንያት ነው አትበሉ ሲለን ነው፡፡ ጌታችንም “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ ከመጎምጀትም ሁሉ ተጠበቁ ”(ሉቃ.፲፪፥፲፫-፳) ብሎ አስተምሮናልና፡፡ ስለዚህም ጌታችን“ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” አለን፡፡(ማቴ.፬፥፬)
“የዕለት” አለን ስለነገ በመጨነቅ እንዳንኖር ሲያሳስበን፡፡ ምክንያቱም ነገ ስለመኖርህ የምታውቀው ነገር የለህም፡፡ የእኛ መኖር በእግዚአብሔር እጅ የተያዘች ናት “የሰው እድሜ የተወሰነ ነው፤ የወሩም ቁጥር በአንተ ዘንድ ነው ፤እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን  ዳርቻ አደረግህለት እንደ ምንደኛም እድሜው እስኪፈጸም ድረስ”(ኢዮ.፲፬፥፭-፮ ) እንዲል፡፡
 እዚህ ላይ አንድ የምናስተውለው ነገር አለ፡፡ ነገ የእኛ ካልሆነ እለቱዋ የእግዚአብሔር ስጦታ ከሆነች አሁን የያዝነው ሀብትም የእኛ አይደለም ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም “ወደ ዓለም ምንም እንኳ  ይዘን አልመጣንምና አንዳችም ልንወስድ አይቻለንም” ማለቱ አሁን ይዘነው ያለው ንብረት የእኛ እንዳልሆነ ነገር ግን ተገልግለንበትና አገልግለንበት እንድናልፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠን መሆኑን ይህ ኃይለ ቃል በግልጽ ያስቀምጥልናል፡፡ “አንተ ሰነፍ በዚች ሌሊት ነፍስህን ከአንተ ሊወስዱአት ይፈልጓታል፡፡ ይህስ የሰበሰብኸው ለማን ይሆናል ?( ሉቃ.፲፪፥፳)የሚለውም ኃይለ ቃልም ይህንን በደንብ የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ ምዕራፍ ማጠቃለያ ላይ “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል፡፡”አለን (ማቴ.፮፥፴፱)
ጌታን በትምህርቱ ሁሉ በዚህ ምድር ፈቃድ እንዳንታሰር በማድረግ ወደሰማየ ሰማያትን በሕሊና አንድንነጠቅ  ትምህርቱን በዚህ መልክ አደረገው፡፡ ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment