v በጸሎታችሁ አሕዛብን አትምሰሉአቸው
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ
መርጊያ
23/09/2004
በመቀጠል ጸሎታቸንን እንዴት ማቅረብ እንዳለብን ያስተምረናል፡፡
‹‹አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደነርሱ በከንቱ አትድገሙ›› (ማቴ.፮᎓፯)አለ፡፡...
ጌታችን ከዚህ አስቀድሞ ጸሎትን በተመለከተ ደግሞ ደጋግሞ አስተምሮ ነበር፡፡ በዚህም ቦታ አስቀድሞ ጻፎችና ፈሪሳውያንን እንደወቀሳቸው ሁሉ ‹‹በከንቱ አትድገሙ›› በማለት አሕዛብን ወቀሳቸው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ወገኖችንም አሳፈራቸው፡፡
ጌታችን በትምህርቱ የምንሳብባቸውንና እኛም ልንፈጽማቸው የምንጓጓላቸውን
ነገሮች ጎጂነት ነቅሶ በማውጠት አስተማረን፡፡ ምክንያቱም እኛ ሰዎች ስንባል በውጫዊ ገጽታቸው አምረውና አሸብርቀው በሚታዩ
ነገሮች በቀላሉ ስለምንሳብ፣ በውጭ ሲታዩ ጻድቃን የሚመስሉትን ግብዞችን መስለን መመላለስን ስለምንመርጥ ነው፡፡
‹‹በከንቱ አትድገሙ›› በማለት እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ የዘቀጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ገለጠልን፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሥልጣንን፣ተከብሮን፣የጠላት ነፍስን፣ ባለጸግነትን፣ እንዲሁም ሌላም እኛን የማይጠቅሙንን ነገሮች በጸሎት ብንጠይቅ በከንቱ እንደመድገም ይቆጠርብናል፡፡
‹‹በከንቱ አትድገሙ›› በማለት እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች እጅግ የዘቀጠ አስተሳሰብ እንዳላቸው ገለጠልን፡፡ እኛ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሥልጣንን፣ተከብሮን፣የጠላት ነፍስን፣ ባለጸግነትን፣ እንዲሁም ሌላም እኛን የማይጠቅሙንን ነገሮች በጸሎት ብንጠይቅ በከንቱ እንደመድገም ይቆጠርብናል፡፡
ስለዚህም ‹‹አትምሰሎአቸው ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና ›› አለን፡፡ እዚህ ላይ ጌታችን እንዲህ
ሲል ጸሎታችሁን አታርዝሙት ማለቱ አይደለም፡፡ የጌታችን ዋናው የትምህርቱ ትኩረት ጊዜን በተመለከተ አይደለምና፡፡ ነገር ግን አስቀድመን
እንዳስቀመጥነው የማይገቡ ጸሎታትን በማድረግ በከንቱ በመድገም አብዝተንና አርዝመን የምንጸልየውን ጸሎት በተመለከተ እንዲህ አለን፡፡
የሚገባ ጸሎት ከሆነ ደጋግመን መጸለይ እንዲገባን ‹‹በጸሎት ጽኑ›
ተብለን ታዘናል፡፡ በኤፌ. ፮᎓፲፰ ላይም በጸሎት መጽናት እንዳለብን ተቀምጦልናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም
የጎደለውን ልንሞላ ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እንጸልያለን››(፩ተሰሎ.፫፡
፱−፲) በሚለው ንግግሩ ጸሎትን አርዝሞ ይጸልይ እንደነበረ ማስተዋል እንችላለን፡፡
ጌታችን ከጨካኙ ዳኛ ዘንድ ፍርድ ተጓደለብኝ በማለት በተደጋጋሚ ደጅ የጠናችውን መበለት ምሳሌ በማድረግ (ሉቃ.፲፰᎓፩)፣ እንግዳ ስለመጣበት እንጀራን በእኩለ ሌሊት ከወዳጁ ይለምን
ዘንድ የሄደውን ሰው ትጋት በማውሳትና ያም ወዳጁ የተጠየቀውን የሰጠበት ምክንያት ስናስተውል ስለወዳጅነቱ ሳይሆን ስለንዝነዛው ብዛት እንደሆነ አብራርቶ ገልጾልናል፡፡ በዚህም ያለማቋረጥ መጸለይ እንደሚገባ
አስተምሮናል፡፡ በእርግጥ እልፍ ስንኞችን ደጋግሞና አርዝሞ መጸለይ ይገባል አንልም፡፡ ይህም እንደማይገባ ሲያስረዳ‹‹በጸሎታችው ብዛት
የሚሰሙ ይመስላቸዋልና እነርሱን አትምሰሉአቸው›› ብሎናልና፡፡
አስከትሎም ‹‹ባትለምኑትም
አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል›› አለን፡፡ ነገር ግን እርሱ የሚያስፈልገንን ካወቀ የእኛ መጸለይ ለምን አስፈለገ? ብሎ የሚጠይቅ ከእኛ መካከል አይጠፋም፡፡ አምላክን እንዲህ አድርግ ብለን አናዘውም
ነገር ግን ከእርሱ ጋር የፈቃድ አንድነት ይኖረን ዘንድ ስለሚገባን ፈቃዳችን በአንደበታችን መጠየቅ አስፈለገን፡፡ (እግዚአብሔር ያለፈቃዳችን አንዳች ነገር ሊያደርግልን አይፈቅድም እርሱ ፈቃዳችንን ያከብራል) ከዚህም በተጨማሪ ከእርሱም
ጋር በጸሎት በምንመሠርተው የጠበቀ ግንኙነት ተጠቃሚዎች እንድንሆንና የገዛ ኃጢአታችንን ዘወትር በማሰብ በትሕትና እንመላለስ ዘንድ ፈቃዱ ስለሆነ ነው፡፡
v ‹‹ እናም ስትጸልዩ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር ››(ማቴ.፮፡፱)
በዚህ ኃይለ ቃል በእርሱ ለሚያምኑት የተሰጠውን ቸር ስጦታ ማስተዋል እንችላለን፡፡
እግዚአብሔርን አባቴ ብሎ የሚጠራ ሰው በእርሱ የኃጢአት ስርየትን ያገኘ፣ የእዳ ደብዳቤ ይሰረዝለታል፣ ቅድስናን ገንዘቡ ያደርጋል፣ ከኃጢአት በእርሱ የጸዳ ይሆናል፣
ደኅነትን ያገኛል ፣ የእግዚአብሔር ልጅነት ሥልጣን ያለውና የርስቱ ወራሽ ይሆናል ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ይሆናል፣ በጸጋ የክርሰቶስ
ወንድም ይባላል፡፡ እነዚህ በረከቶች ሳይሰጡት እግዚአብሔርን አባት ብሎ ሊጠራ የሚችል ከሰው ወገን የለም፡፡
አስከትሎም የእርሱን የክብሩን ከፍታን ለማስረዳትና እኛ የምናገኘውን
ታላቅ ክብር እንድንረዳ ለማድረግ እንዲሁም እኛ በላይ በሰማይ ያለውን እንድንሻ ‹‹በሰማይ የምትኖር›› ብለን እንድንጸልይ አዘዘን፡፡ እንዲህ ሲል ግን
እግዚአብሔር በሰማይ ብቻ የሚኖር በምድር የማይኖር መሆኑን እየተናገረ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ብሎ የሚጸልየውን ወገን ከምድራዊ
አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ሰማያዊ እሳቤ እንዲገባና በላይ ያለውን እንዲናፍቅ ልቡናውን ለማነሳሳት ፈልጎ የተናገረው ቃል ነው፡፡
እንዲሁም ስንጸልይ ለሁሉና ለወንድሞቻችን ተገብተን መጸለይ እንዳለብን
ሊያስተምረን ‹‹አባቴ ሆይ በሰማይ የምትኖር›› እንድንል አላስተማረንም ነገር ግን ‹‹ አባታችን ሆይ ››ብለን እንድንጸልይ አዘዘን፡፡ ይህም ጸሎታችን ለፍጥረት ሁሉ እንዲሆን ወደራሳችንም ጥቅም እንዳናደላ ይልቁኑ
ለፍጥረት ሁሉ መልካሙን ሁሉ መለመን እንዲገባን ሲያስተምረን ነው፡፡
በዚህ ኃይለ ቃል ለአንዴና ለመጨረሻ ጥላቻንና ትዕቢትን፣ አጥፍተን
የመልካም ነገር ሁሉ እናት ወደ ሆነች ፍቅር እንድናመራ መፍቀዱን እናስተውላለን፡፡ በክብር መበላለጥን አስወግዶ በንጉሥና በደሃው
ሰው መካከል ምንም እጅግ የሰፋ የምድራዊ ሀብት መለያየት ቢኖርም
ከዚህ በእጅጉ በሚልቀው ጸጋው አንድ እንዳደረጋቸው ጨምረን እንገነዘባለን፡፡ ይህ ኃይለ ቃል የሚያስረዳን ሁላችንም የእግዚአብሔር
ባሮች መሆናችንን ነው፡፡
ከማስተዋል ጉድለት የተነሣ በምድራችን ተፈጥሮ የነበረውን መለያየት በማስወገድ የእግዚአብሔር ልጆች በማድረግ አንድ ወገን
አደረገን፡፡ ከእንግዲህ አንዱ ከአንዱ የሚበለጥበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡ ሀብታም ከደሃው፣ ጌታው ከባሪያው፣ገዢም ከተገዢው፣ ንጉሥም ከሎሌው፣ ጠቢቡም ከአላዋቂው ፣
ሊቁም ከጨዋው፣ ምንም የሚበልጥበት ነገር የለም፡፡ "አባት" ብለው ለሚጠሩት ሁሉ አንድ የሆነ የልጅነትን ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡
ቀጥለን የምንማረውን ትምህርት ለጊዜው አቆይተን ይህን ያነሣነውን ትምህርት በጥልቀት የፈተሽነው እንደሆነ በራሱ በጎ ምግባራትን
ለመፈጸም በቂ የሆነ መመሪያን የሚሰጠን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔርን የሁላችን አምላክ ብሎ የሚጠራ ሰው ከተሰጠው ክብር ጋር ተመጣጣኝ
የሆነ በጎ ምግባራትን ሊፈጸም እንዲገባው የሚያሳስብ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ብቻ አላዘዘንም፡፡
v ‹‹ስምህ ይቀደስ››
ለእግዚአብሔር
ምስጋናን ማቅረብ እንደ ተቀዳሚ ተግባሩ የሚመለከት ነገር ግን ምድራዊ ፍላጎቶቹን እንደ ሁለተኛ ነገር የሚቆጥር እርሱ በእውነት እግዚአብሔር
አምላክን አባት ብሎ በጸሎት ለመጥራት የተገባው ሰው ነው፡‹‹
ስምህ ይቀደስ ማለት ስምህ በእኛ ይመስገን ማለት ነው፡፡ የእርሱ
ክብር ፍጹም ነው ሁል ጊዜም ሳይጓደልበት ይኖራል፡፡ነገር ግን ስምህ ይቀደስ ብሎ እንዲጸልይ የታዘዘው ያ ሰው እንዲህ ብሎ በመጸለዩ ጌታ በእኛ ሕይወት ይከብር
ዘንድ መጠየቁ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ትምህርትን አስቀድሞ ‹‹መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን
እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ››(ማቴ.፭᎓፲፮) በማለት አስተምሮ ነበር፡፡ አዎን ሱራፌልም ለእርሱ በዚህ መልክ ‹‹ ቅዱስ ቅዱስ
ቅዱስ ›› በማለት ያመሰግኑታል፡፡ ስለዚህ ስም ይቀደስ ስንል ስምህ በሰው ሁሉ ፊት በእኛ በጎ ምግባር ይክበር ይመስገን ማለታችን ነው፡፡ አንድም እንዲህ ማለታችንም ሕይወታችንን በአግባቡ እንመራና አንተም
በእኛ መልካም ምልልስ ስምህ ይከብር ዘንድ ጸጋህን አብዛለን ብለን እንድንጠይቅም ማስተማሩ ነው፡፡ በዚህም ታግዘን ፍጹም ወደ ሆነ ራስን ወደ መግዛት፣ በፈተናም ወደ መጽናት እንደርሳለን፡፡ የእኛን የሕይወት ምልልስ የተመለከቱ ሰዎች
ጌታ እንዲህ ስላደረገልን ስሙን ያከብሩታል፡፡ ይቀጥላል....
No comments:
Post a Comment