v ግብዞችን አትምሰሉአቸው
ትርጉም በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
23/09/2004
ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባና መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው
አባትህ ጸልይ በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጽ ይከፍልሃል፡፡››(ማቴ.፮᎓፩−፮)
በዚህ ቦታ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻፎችንና ፈሪሳዊያንን ግብዞዎች ማለቱ አግባብነት ነበረው፡፡
ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ቤት ለጸሎት በሚመጡበት ጊዜ የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ሲሉ ከሥርዐት የወጣ አለባበስን ይለብሱ ነበር
እንጂ ለጸሎት ተስማሚ የሆነውን የትሕትና አለባበስን አይለብሱም ነበርና ነው፡
ለጸሎት ወደ አምላኩ የሚቀርብ ሰው ሌሎች ጉዳዮቹን ሁሉ ወደ ኋላ ትቶና
ከሰው ዘንድም ምስጋናንና ክብርን ሳይሻ ጸሎቱን ተቀብሎ ወደሚፈጽምለት አምላኩ ብቻ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ይህን መፈጸም
ትተህ አይኖችህን የትም የምታንከራትት ከሆነ ከእግዚአብሔር ቤት በባዶ
እጅህ ምንም ሳታገኝ እንድትመለስ እወቅ፡፡ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ዋጋ ማግኘትና ማጣት በእጅህ የተሰጠ የአንተ እድል ፈንታህ
ነው፡፡ ስለዚህ ከንቱ ውዳሴን የሚሹ ሰዎች ከእኔ ዘንድ አንዳች አያገኙም አላለም ፡፡ነገር ግን‹‹ ዋጋቸውን ተቀብላዋል››አለ፡፡
በእርግጥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሳይሆን እነርሱን ከመሰሉ ሰዎች ምስጋናና
አድናቆትን አግኝተው ይሆናል፡፡ ይህ ለእነርሱ ዋጋቸው ነው፡፡ ነገር ግን ከእግዚብሔር ዘንድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ለጸሎታቸው
ብድራትን የጠበቁት ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎችን ነውና፡፡ነገር ግን በዚህ ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላክ ማንኛውንም እንደ ፈቃዱ የሆነ ልመናና ጸሎት ብናቀርብ ልመናችንን
ሊሰማን ጸሎታችንን ሊቀበል ቃል ኪዳን መግባቱም እናስተውላለን፡፡ ጌታችን ጻፎችና ፈሪሳውያን ለጸሎታቸው የመረጡት ሥፍራ ለከንቱ ውዳሴ የሚያጋልጥ መሆኑን ካስረዳ በኋላ እኛ ስንጸልይ
ምን ማድረግ እንዳለብን አስከትሎ አስተምሮናል፡፡
እንዲህም አለን ‹‹ አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም
ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ›› ፡፡ምንድን ነው ታዲያ? እንዲህ ሲለን በቤተክርሰቲያን ጸሎትን አታድርጉ ሲለን ነውን? አይደለም
ነገር ግን እንዲህ ማለቱ በየትኛውም ቦታ ሆነን ጸሎትን ብናደርግ በፍጹም ተመስጦ ሆነን ማቅረብ እንዳለብን ሲያሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም
እግዚአብሔር በየትም ቦታ ማንኛውንም መልካም ሥራ ብንፈጽም ሁልጊዜም በማስተዋል ሆነን ብንፈጽማቸው የእርሱ ፈቃድ ነውና ፡፡ ምንም
እንኳ አንተ የእልፍኝህን በር ዘግተህ ብትጸልይ ይህን በማድረግህ ከሰው ዘንድ ምስጋናን ሽተህ ከሆነ የእልፍኝህን በር ዘግተህ በመጸለይህ
ከእግዚአብሔር ዘንድ አንዳች ዋጋን አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ፡፡
ይህንን ግልጽ ለማድረግም‹‹ ለሰው ትታዩ ዘንድ ›› የሚለውን ቃል
ጨመረበት ፡፡ ስለዚህም አንተን የእልፍኝህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ማዘዙ ልቡናህን ሰብስበህ ትጸልይ ዘንድ ነው እንጂ በርህን
ዘግተህ መጸለይ ዋጋ ያሰጥሃል እያለህ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ የቤትህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ሳይሆን የልብህን ደጆች
በመዝጋት ትጸልይ ዘንድ ነው፡፡
ማንኛውንም የትሩፋት ሥራዎችን ስትሠራ ከከንቱ ውዳሴ ነፃ መሆን መልካም
ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስትጸልይ ራስህን ከከንቱ ውዳሴ መጠበቅ ይገባሃል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በጸሎታችን ሰዓት የምንቅበዘበዝና የምንባክን
ከሆነና ከልባችን የማንጸልይ ከሆነ ለዚህ ክፉ ለሆነ በሽታ ማለትም ለከንቱ ውዳሴ እንጋለጣለን፡፡ እኛ በተመስጦ ሕሊናችንን ሰብስበን
ካልሆነ የምንጸልይው እንዴት ጸሎታችንን እግዚአብሔር እንደሚሰማን እርግጠኛ እንሆናለን?
እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ምዕመናን ከሥርዐት የወጣ ጩኸት በማሰማትና
ያልተገባ ባሕርይን በማሳየት የሌላውን ሰላም የሚያውኩ ከዚህም ባለፈ ራሳቸውን ለከንቱ ውዳሴ የሚያጋልጡ አሉ፡፡ በገበያ ቦታ እንኳ
አንድ የእኔ ቢጤ ባልተገባ ባሕርይ እና ለመስማት በማይመች ጩኸት
ለአንዱ ባለጸጋ ልመናን ቢያቀርብ ፈጥኖ ከፊቱ እንዲያባርረው በትሕትና በመሆን ቢለምነው ግን የባለጸጋውን ሆድ አባብቶ ያለውን እንዲሰጠው
እንደሚያደርገው አትመለከትምን?
እኛም ስንጸልይ በማይገባና ፈር በለቀቀ ከሥርዐት በወጣ መልኩ አብዝተን
በመጮኸ ሊሆን አይገባውም፡፡ ነገር ግን በውጭ የምናሰማው አንዳች ጩኸት ሳይኖር ለከንቱ ውዳሴ ከሚያጋልጡ ያልተገቡ ባሕርያት ርቀን
አጠገባችን ያሉትን ሰዎች ሳናውክ በፍጹም ትሕትና በውስጣዊ ማንነታችን ማለትም በነፍሳችን ወደ እግዚአብሔር ልንጮኽና ልመናችንን
ልናቀርብ ይገባል፡፡
እንዲህ
ስንል ሰው ከደረሰበት ታላቅ ሃዘን የተነሣ አምርሮ ሊጮኽ አይችልም ማለታችን ግን አይደለም ፡፡
ቢሆንም አንድ ሰው ምንም እንኳ እጅግ ያዘነና የተከዘ ቢሆንም ይህን ታላቅ ሃዘን በነፍሱ ወደ እግዚአብሔር በመጮኽ ሊገልጸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር አምላኩ በነፍሱ አብዝቶ ቃተተ ጮኸም
ጩኸቱም ከእግዚአብሔር ዘንድ ተሰማች በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ሙሴን‹‹ ለምን ትጮኽብኛለህ›› አለው፡፡ (ዘጸአ. ፲፬፡፲፭)የነቢዩ
ሳሙኤል እናት ሃና ከከንፈሩዋ የወጣ አንዳችም ድምጽ ሳይኖር በነፍሱዋ ግን የልቧን ሃዘን ወደ እግዚአብሔር ታመለክት ነበር፡፡ ልመናዋንም እግዚአብሔር ተቀበላት የልቧንም መሻት ሁሉ ፈጸመላት፡፡ አቤል
እንኳ በሞቱና በደሙ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድ ከመለከት ድምጽ ይልቅ ጠርታ የምትሰማ ጩኸትን ወደ እግዚአብሔር ጮኾ ነበር፡፡(ዘፍ.
፬፡፲)
ነቢዩ ኢዩኤልም በእግዚአብሔርም ፊት የልባችንን ሃዘን ለመግለጽ ልብሳችንን
ሳይሆን ልባችንን ለጸሎት ልናዋርድ እንዲገባን ሲያስረዳ ‹‹ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ ›› (ኢዩ.፪፡፲፫) ብሎናል፡፡
መዝሙረኛውም ‹‹ አቤቱ አንተን ከጥልቅ ጠራሁ›› (መዝ›፻፳፱፡፩)ብሏል፡፡
ከልባችን ጥግ ከጥልቁ የሚወጣው ጩኸታችን ድንቅ የሆነ ምላሽን ይዞልን
ይመጣል፡፡በምድራዊው ቤተመንግሥት ትንሽ የሆነ ኮሽታ ወይም ሹክሹከታ የጊቢውን ጸጥታ ምን ያህል እንደሚያውከው አትመለከትምን? እንዴት ታዲያ ምድራዊ ባልሆነው
እጅግ አስፈሪ በሆነው ሰማያዊው ቤተመንግሥት ስትገባ የበለጠ ፀጥታን ገንዘብህ ማድርግ ይጠበቅብህ ይሆን!!
አንተ አሁን በምስጋና ከትጉሃን መላእክት ጋር ተቆጥረሃል፡፡ ከሊቃነ
መላእክት ጋርም ማኅበርተኛ ሆነሃል፡፡ ከሱራፌል ጋር ዝማሬን ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ታድመሃል፡፡ በሰማያት ያሉ መላእክት ሁሉ በመልካም
ሥርዐት በመሆን ለእግዚአብሔር ይገዛሉ፡፡እርሱንም በመፍራት ሆነው ድንቅ የሆነ ዝማሬአቸውንና ቅዳሴአቸውን ለፍጥረት ሁሉ ገዢ ለሆነው
አምላክ ያለማቋረጥ ያቀርባሉ፡፡
አንተም ከእነርሱ ጋር እግዚአብሔርን በማመስገን ስሙን በመቀደስ እነርሱን
ትመስላቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋርም በጥምቀት ማኅበርተኛ ሆነሃል፡፡
ስለዚህም በምትጸልይበት ጊዜ ለሰዎች ትታይ ዘንድ አትጸልይ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡፡ እርሱ በሁሉ ቦታ ይገኛልና እይታን
ከፈለግህ በሁሉ ቦታ ያለ እርሱ ከሰው ይልቅ ያስተውልሃል፡፡ እርሱ በልብህ የታሰበውን እንኳ ያውቃል፡፡
‹‹በስውር የሚያይህ አባትህ በግልጥ ይከፍልሃል፡›› እንዲህ ሲል(shall
freely give thee “ but shall reward thee” በነጻ
ይሰጣሀል አላለም ነገር ግን እንደሚገባ ሆነህ በመጸለይህ ምክንያት በብድራት በግልጽ ይከፍልሃል ማለት ነው፡፡ አዎን እርሱ በአንተ ዘንድ እንደ ተበዳሪ
ሆኖ ታየ፡፡በዚህም አንተን ምን ያህል እንደወደደህና እንዳከበረህ አስተውል፡፡እርሱ የማይታይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን አንዲሁ እኛም ስንጸልይ በስውር ላለው አባት ብለን እንጂ
ከሰው ምስጋናን ለመቀበል ሽተን ሊሆን አይገባውም ፡፡ ይቀጥላል.....
ይህንን ግልጽ ለማድረግም‹‹ ለሰው ትታዩ ዘንድ ›› የሚለውን ቃል ጨመረበት ፡፡ ስለዚህም አንተን የእልፍኝህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ማዘዙ ልቡናህን ሰብስበህ ትጸልይ ዘንድ ነው እንጂ በርህን ዘግተህ መጸለይ ዋጋ ያሰጥሃል እያለህ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ የቤትህን ደጅ ዘግተህ ትጸልይ ዘንድ ሳይሆን የልብህን ደጆች በመዝጋት ትጸልይ ዘንድ ነው፡፡
ReplyDelete