Wednesday, March 25, 2015

አንድ ዓለሙን ስላሸበረውና ብዙዎች ብዙ ስላሉለት የካቶሊክ ተረት ልንገራችሁ

በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

16/07/2007

ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን  በትርጓሜ አስታካ አንድ ተረት ጽፋ ዓለሙን እያመሰችው ትገኛለች፡፡ ይህን ትርጓሜ ይዘው ያልሆኑትን ሆነናል በማለት ደማችን የተቀዳው ከመላእክት ወገን ከሆኑት በድሮ ጊዜ ኃያላን ከተባሉት ኔፊሊም ወገን ነው የሚሉ ወገኖች ተነሥተዋል ፡፡ 
እነርሱም በአሁኑ ጊዜ ብዙ የሚባልላቸው ራሳቸውን ብሩሃነ አእምሮ የሚሉት ኢሉሚናቴዎች  ናቸው፡፡ የሚደንቀው ግን ይህ ልብ ወለድ እውነት መስሎአቸው የታወኩ ከእኛም ወገን አልጠፉም፡፡ የጸናው መሰረቱን ሳይለቅ ንፋስ እንደሚያላጋው ሸንበቆ በአፍጢሙ እየተደፋ አፈር ልሶ ሲነሣ ሌላ ጊዜ ደግሞ  የእንግልል ከመሬቱ እየተጣጋ መልሶ እየተነሣ ሲቆም እያየን ነው፡፡ ያልጸናው ግን ነፋሱ እንዳነፈሰው ሲነፍስና ከዚያም እልፍ ሲል የነፋሱ አገልጋይ በመሆን በሌሎች ዓይን ላይ አዋራውን እየሞጀረና እያሳወረ ይገኛል፡፡ ባናስተውለው ነው እንጂ ይህ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ የሚመጣው ሃሳዊው መሲህ ሰዎችን ሆን ብሎ ለማጥመድ የዘየደው ዘዴ መሆንኑ ማንም በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡ 
እንዴት በሉኝ? መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ ላይ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ የሚነሣው ተቃዋሚው እኔ ሰይጣን ነኝ እኔን አምልኩኝ እያለ እንደሚመጣ ተጽፎልን አናገኝም፡፡ እርሱም ሆነ ነቢያቱ የሚነሡት በክርስቶስ ስም ነው፡፡ ሲነሡም ራሳቸውን የጽድቅ አገልጋዮች በማድረግ እንጂ የሰይጣን አገልጋዮች ነን በማለት አይደለም፡፡